የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | ዓለም | DW | 02.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የዶክተር መረራ ጉዲና ከአውሮጳ መልስ ኢትዮጵያ ውስጥ መታሰር እና የኩባው አብዮታዊ መሪ የፊደል ካስትሮ ከዚህ ዓለም መለየት ዜና በሳምንቱ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ጎልተው ወጥተዋል። የኩባው አብዮተኛ የቀድሞ መሪ ፊደል ካስትሮ ዜና ረፍት ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ አነጋግሯል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:12
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:12 ደቂቃ

የሳምንቱ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀ መንበር እና የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መድረክ (መድረክ) ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር መረራ ጉዲና የመታሰራቸው ዜና  በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ዋነኛ መነጋገሪያ ሆኗል።

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ሊቀ-መንበር ዶክተር መረራ ጉዲና ከአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና የሪዮ ኦሎምፒክ ባለድሉ አትሌት ሌሊሳ ፈይሳ ጋር ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ኹኔታ ለማሰማት ብራስልስ አውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ተገኝተው ነበር። 

ዶክተር መረራ ጉዲና ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ከአትሌት ሌሊሳ ፈይሳ መሀል ተቀምጠው የሚታዩበትን ምስል ብዙዎች በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች በስፋት ይዘው ታይቷል። ይኽ ምስል ከታየበት ጊዜ አንስቶም ለመንግስት ቅርበት አላቸው የሚባሉ ሰዎች ዶክተር መረራ ጉዲና እንዲታሰሩ በተለያየ መንገድ ሲወተውቱ ተደምጠዋል። 

ዶክተር መረራ ጉዲና ኢትዮጵያ ሲመለሱ መታሰራቸውን በተመለከተ የአውሮጳ ፓርላማ አባል ፖርቹጋላዊቷ አና ጎሜሽ በትዊተር ገፃቸው የሚከተለውን አስፍረዋል። «ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግሩ ምንድን ነው? ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ጋር ለአውሮጳ ኅብረት መልስ ሰጡ። አውሮጳ ኅብረት ስለመጡ መታሰር!» ሲሉ መደነቃቸውን በሚገልጥ ምልክት ንግግራቸውን አስረዋል። 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያት  ባወጣው መግለጫ መሰረት፣ ዶክተር መረራ የታሰሩት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን  መመሪያ  በመተላለፍ በሽብር ከተሰየሙ ድርጅቶችና ጋር  በመገናኘታቸው ነው።

አያንቱ ኒውስ የተሰኘው ድረ-ገጽ «ከፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ጋር አራት ዘመዶቻቸው በኮማንድ ፖስቱ ተይዘው እንደታሰሩ ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል» ሲል ረቡዕ ኅዳር 21 ቀን፣ 2009 ዓ.ም. በእንግሊዝኛ ቋንቋ ባሰፈረው ጽሑፍ አስነብቧል። 

ስለ ዶክተር መረራ ጉዲና መታሰር አብዱልባሲጥ አብዱሰመድ «ሰበር ዜና» ሲል የሚከተለውን በፌስቡክ ገጹ ጽፏል። «የኦፌኮ/መድረክ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ሰሞኑ በውጭ ሀገር ቆይታቸው ወቅት የጸረ-ሽብር ሕጉን እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሰው በመገኘት ከጥቂት ደቂቃ በፊት በቦሌ አየር ማረፊያ ኮማንድ ፖስቱ በሕግ ቁጥጥር ስር አውሏቸዋል» ብሏል። erera

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ገብሩ ገብረ ማሪያም ከዶይቸ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ዶክተር መረራ የታሰሩት (ትናንት) ረቡዕ ኅዳር 21 ቀን፣ 2009 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ጠዋት ገብተው ማታ ከቤታቸው በኮማንድ ፖስቱ መሆኑን ገልጠዋል። 

አብዱልባሲጥ አብዱሰመድ በፌስቡክ ካቀረበው ጽሑፍ ጋር ዶክተር መረራ ጉዲና ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና አትሌት ሌሊሳ ፈይሳ መሀል ተቀምጠው የሚታዩበትን የፎቶ ምስል አያይዞ አቅርቧል።   

የፖለቲካ ተንታኝ እና  የሕግ ባለሙያው አሰፋ ጫቦ በፌስቡክ ባቀረቡት የእንግሊዝኛ ጽሑፍ፦ «አወይ ጓዴ መረራ! ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ መረራርን ለሦስት አለያም ለአራት ጊዜያት አነጋግሬዋለሁ። ያ መቼም በዕጅ አዙር ተባባሪ ያስብለኝ እንደሁ እንጃ። ወይንም ደግሞ ከኑግ የተገኘ ሰሊጥ። በደርግ ጊዜ መረራ ከርቸሌ ነበር። በእስር ቤት ራሱን የያዘበት ኹኔታ ለብቻው ልዩ ታሪክ ነው። እጅግ ደኅንነት ይሰማህ ጓዴ! ከምናስበው በፈጠነ  መልኩ እዚያ ካስቀመጡህ ሰዎች ጋር ቦታ ትቀያየራለህ» ሲሉ አስነብበዋል። 

ኢትዮ ኦብዘርቫቶሪ የተሰኘ የትዊተር ተጠቃሚ ደግሞ «ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ከብራሰልስ ሲመለሱ እሥር ቤት ተላኩ – የሕወሃቱ ፓርላማ አስገባሪው አስመላሽ ወልደሥላሴ የፋና አነጋጋሪው ስብሰባ ላይ የዛቱት ሆነላቸው!» ሲል ጽፏል።  

በዶይቸቬለ የአማርኛ ቋንቋ ዝግጅት የፌስቡክ ገጽ ላይ ካሰፈርነው የዶክተር መረራን መታሰር የሚገልጥ ጽሑፍ ስር ከተሰጡ አስተያየት ሰጪዎች መካከል አጠር ያሉትን  አንድ ሁለቱን እንመልከት።  ሰለሞን ሰለሞን፦ «ለአሸባረ ምህረት የለም» ሲሉ ጸጋዬ ሀፍቱ በእንግሊዝኛ «ናይስ» የሚል ጽፈዋል።  ሰለሞን አበበም «ደስ ሲል» ብለዋል።

የሕግ ባለሙያው እና በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በንቃት ተሳታፊው እሸቱ ሆማ ቀኖ  የዶክተር መረራ መታሰርን በተመለከተ እሱን ጨምሮ በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ ሰዎች የሰጧቸው አስተያየቶች ድባብ በቁጣ የተሞላሉ መኾናቸውን ጠቅሷል። «አብዛኛው በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የዐየሁዋቸው አስተያየቶች ከፍተኛ ቁጣን ያዘሉ ናቸው» ያለው እሸቱ ብዙ ሰዎች ዶክተር መረራ ጉዲናን «የኢህአዴግ መንግሥት ያስሩዋቸዋል ብለው» አልገመቱም ሲል አክሏል። የዶክተር መረራ «መታሰር ለእኔ አዲስ ነገር አይደለም። ምክንያቱም ኢህአዲግ ማሰር የለመደው ነው» ብሏል።

ስለዶክተር መረራ ጉዲና መታሰር በማኅበራዊ መገኛ አውታሮች የቀረቡ አስተያየቶች በርካታ ናቸው። በቀጣዩ የትዊተር መልእክት አሳርገን ወደሌሎች ጉዳዮች እንሻገራለን። 

ጠያቂ፡ «ዶ/ር መረራ በሕግ ጥላ ስር ውለዋል ተብሏል፤ ምን ይላሉ?»
ኮሙኒኬሽን ሚ/ር፡ «መረጃ የለኝም!»
ጠያቂ፡ «የጠ/ሚ/ሩ የኢኮኖሚ አማካሪ ጡረታ ስለመውጣታቸውስ?» 
ኮሚኒኬሽን ሚ/ር፡ «መረጃ የለኝም!»

ጽሑፉ በሳቅ ምልክት ይጠናቀቃል። ኢሳያስ ግርማይ በትዊተር ገጹ ካሰፈረው ጽሑፉ የተወሰደ ነው።

የኩባው አብዮታዊ መሪ ፊደል ካስትሮ ኅልፈተ-ዜና መሰማት በማኅበራዊ የመገናኛ አውታር ብዙዎችን ያነጋገረ ሌላው ርእሰ-ጉዳይ ነበር። በእርግጥ ኩባውያን እና ዓለም የፊደል ካስትሮን ሞት ሲጠባበቅ 10 ዓመት አልፎታል። ከዚህ ቀደም ስለ ፊደል ካስትሮ ሞት በተደጋጋሚ ጭምጭምታ መሰማቱም የተለመደ ነበር።

አብዮተኛው መሪ በ90 ዓመታቸው ያረፉት በኩባ መዲና ሐቫና ነው። ካስትሮ በጉብዝና ወራቸው የኩባን አብዮት ከመምራት አንስቶ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ጦርነት ወቅት ለኢትዮጵያ በማገዝ ወታደሮቻቸውን ጭምር የላኩ መሪ ነበሩ። ፊደል ካስትሮ በብዙዎች ዘንድ ኢ-ፍትኃዊነትን የታገሉ ጀግና ተደርገው ይወደሳሉ።

በምዕራባውያን ግን ስማቸው ጎልቶ የሚነሳው በአምባገነንነት ነው። ለእርስዎስ? በሚል የፌስቡክ ተከታታዮቻችን አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ጋብዘን ነበር። እስኪ ከአስተያየቶቹ የተወሰኑትን አብረን እንመልከት። 

ሙሐመድ አበረ « ጀግና መሪ ነበር፤ በተለይ አሜሪካን በጣምምምምም ስለሚጠላት እወደው ነበር ! ጀግና የሚባለው የዚህ አይነቱ መሪ እንጂ ደንግጦ ለሞተ የማይረባ መሪ ጀግና ብሎ በየቀኑ በEbc እንደሚለፈልፉለት አይነት ሰው አይደለም» የሚል ጽሑፍ አስፍሯል።  

ካህሳይ ባራኪ የተባለ አስተያየት ሰጪ ከሙሐመድ አበረ አስተያየት ስር ቀጣዩን መልእክት አስነብቧል። «ምዕራባውያን ሁሌም ሲጠሩት ኣቤት ሲልኩት ወዴት የሚል ኣሻንጉሊት መንግስት ይወዳሉ። ፊደል ካስትሮም የምዕራባውያን ተላላኪ የሆነው የባቲስታ መንግስት አሽቀንጥሮ ጥሎ ወደ ፕረዚዳንትነት የወጣ ሰው ስለ ሆነ ኣይወዱትም ስለማይወዱትም ነው ኣምባገነን የሚሉት። ልዩነቱ እዚህ ጋ ነው ያለው። ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያንን ደግሞ ባለውለታችን ነው ፊደል ካስትሮ። Rip ፊደል ካስትሮ»

ስለፊደል ካስትሮ በ90 ዓመት በሞት መለየት በትዊተርም በሌሎችም ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ብዙዎች ብዙ ብለዋል። ስለ ኢትዮጵያ ጉብኝታቸው፣ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ጦርነት ወቅት ለኢትዮጵያ ስላደረጉት እገዛ የሚያወሱ አስተያየቶች ጎላ ብለው ታይተዋል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ
 

Audios and videos on the topic