የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎችና ግጭት በኢትዮጵያ | ኢትዮጵያ | DW | 20.12.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎችና ግጭት በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ የተለያዩ ሥፍራዎች በተደጋጋሚ የተከሰተው ግጭት እና ቁርቁስ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ላይም ጎልቶ ይታያል። ቁርቁሱ በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ያለዉ መቃቃር ነጸብራቅም ነው የሚሉ አሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:28

የመብት ተሟጋቾቹ ቁሩቁስ ማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች የሚቀርቡ ጽሑፎች ላይ የተለያዩ ወገኖች ቁርቁስ ይስተዋልባቸዋል፤የኢሕአዴግ ውስጣዊ ንትርክ እና ፍጭት ሌላኛው መንጸባረቂያ ናቸው የሚሉም አሉ።
አምስተርዳም ነዋሪ የኾኑት የኦሮሞ መብት አቀንቃኙ አቶ ገረሱ ቱፋ አዳዲስ የሚሏቸውን መረጃዎች በተከታታይ ለበርካታ ተከታዮቻቸው ያደርሳሉ። «እኔ በግሌ ያገኘኹትን በሙሉ አልለጥፍም» ያሉት አቶ ገረሱ ቱፋ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ዙሪያ ታይቷል ስላሉት ወታደራዊ እንቅስቃሴ እና በኦሕዴድ አመራር ላይ ግድያ ሊፈጽሙ ሲሉ ተያዙ ያሏቸውን ኹለት ሰዎች ፎቶግራፍ እና መታወቂያ በፌስቡክ ገጻቸው አሰራጭተዋል። አቶ ገረሱ ስለሚያሰራጩዋቸው መረጃዎች ተአማኒነት መኾናቸውን ይናገራሉ። «ምንጬ የማምነው ሰው መኾን አለበት። አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ አይነት መረጃዎችን  ወደ መደበኛው የመገናኛ ዘርፍ መልቀቅ  መረጃ የሚሰጠው ሰው ማብራሪያ መስጠት፤ ማንነቱን ማሳወቅ አለበት። እና በዚያ ምክንያት አንዳንድ ሰዎች እንደዚያ መስጠት አይፈልጉም፤ ስለዚህ በሌላ መንገድ እንዲወጣ ያደርጋሉ።  እኔ ለምሳሌ የነገረኝን ሰው አምናለሁ። ግን ያው በዐይኔ ወይንም  በኹለተኛ መንገድ ለማረጋገጥ የሚቻልበት አይደለም።»

አቶ ገረሱ ጥራቱ ከመደበኛው የመገናኛ ዘርፍ ጋር ባይወዳደርም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲኽ በመረጃ ልውውጡ ዘርፍ ፈጣን ኾነዋል ብለዋል። ፈጣን መረጃንም ለሳቸው በሚመቻቸው መንገድ እንደሚያሰራጩ አክለዋል። በማኅበራዊ የመገናኛ ዘርፎች ላይ በተለያዩ የመብት አቀንቃኞች ላይ የሚታየው ቁርቁስ የኢሕአዴግ መከፋፈል ነጸብራቅ «ነውም አይደለምም» ብለዋል። በተለያዩ የመረጃ ትስስሮች መረጃዎች እየወጡ ቢኾንም የፖለቲካ አቀንቃኞች ቁርቁስ «በሀገሪቱ ውስጥ የነበሩ የአመለካከት ግጭቶች ነጸብራቅ ናቸው» ሲሉ አክለዋል። «በኅብረተሰቡ መካከል ግጭት እንዳይስፋፋ ጥንቃቄ አደርጋለሁ» ብለዋል።

የኢሕአዴግ ደጋፊ እንደኾኑ የተናገሩት አቶ አንተነህ ረዳዔ በበኩላቸው በኢሕዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ያለው ሽኩቻ ነጽብራቊ በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች ላይም ይታያል ባይ ናቸው። 
«ኦሕዴድ አካባቢ ቀረብ የሚሉ የፌስቡክ አክቲቪስቶች የኦሕዴድን አቋም የሚመስሉ ወይንም ከባለሥልጣናቱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ከሚያገኟቸው መረጃዎች የሚመነጬ መረጃዎችን ገጻቸው ላይ  ሲለቁ ታያለህ። ከዛ ጋር ተያይዞ አኹን ኢሕአዴግ አካባቢ የሚታየው የጎራ መደበላለቅ ከነዚህ ከአክቲቪስቶች ጋርም የሚታይ አይነት መስሎ ይሰማኛል።»

ጋጤጠኛ እና ጦማሪ ፍጹም ብርሐኔ በኢሕአዲግ ውስጥ «ሽኩቻ እንዳለ እስማማለሁ» ብለዋል። የሽኩቻው ነጸብራቅ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮችም «ፓርቲው ውስጥ እናዳለው ሽኩቻ ጎራ ለይተው የሚንቀሳቀሱበት አጋጣሚ በብዛት ይስተዋላል»  ባይ ናቸው። በመረጃ ፍሰት ወቅት ጥንቃቄ ሊደረግባቸው ይገባል ያሏቸውን ነጥቦችም ገልጠዋል።
«ብዙ ጥንቃቄ የማይደረግባቸው ሕዝብን ከሕዝብ፤ ብሔርን ከብሔር ጋር የሚያጋጩ ጽሑፎች እሚጻፉት አብዛኛውን ጊዜ ሙሉ እና ግልጽ መረጃ   ባላቸው ሰዎች አይደለም። ብዙውን ጊዜ አኹን ኅብረተሰባችን በተለይም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚ ወጣቶች ይኽንን ዕያወቁ የመጡ ይመስለኛል። ልክ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጽፏል ብሎ ዝም ብሎ አይሰራጭም አኹን አኹን።»
በገዢው ኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል መቃቃር ተፈጥሯል ከተባለበት ጊዜ አንስቶ የማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ላይ የሚወጡ ጽሑፎች ከአንዱ ጥግ ወደ ሌላኛው ጥግ መጓተት ጎልቶ ይታይባቸዋል። የመረጃ ፍሰቱ ውስን ከመኾኑም አንጻር በርካቶች በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች የሚለቀቁ መረጃዎች ላይ ይበልጥ እንዲያተኩሩ አድርጓቸዋል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic