የማር እንጀራ | ኤኮኖሚ | DW | 09.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የማር እንጀራ

በኢትዮጵያ የተመረተ አንድ ኪሎ ማር በዓለም ገበያ እስከ ሶስት ዶላር ከ50 ይሸጣል። ኢትዮጵያ በዓመት እስከ 500,000 ቶን ማር እና 50,000 ቶን ሰም የማምረት አቅም እንዳላት ይነገራል። ይሁንና በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚመረተው አላት ከሚባለው አቅም ከአንድ በመቶ አይበልጥም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:59

የማር እንጀራ

የ19 አመቷ ወጣት ሰውነት ከብቴ ትምህርቷን ከስድስተኛ ክፍል አቋርጣ ትዳር መስርታለች። ኑሮዋን በግብርና ስራ የምትመራው ሰውነት የአንድ ልጅ እናትም ናት። ቤተሰቧን ከምትደጉምበት የእርሻ ሥራ ጎን ለጎን የንብ ማነብ ስራ ብትጀምርም ዘንድሮ ማር አልቆረጠችም። ሰውነት ስራውን የጀመረችው በአካባቢው ንብ ማነብን ለማዘመን የሚሰራው ንብ ለልማት በኢትዮጵያ የተሰኘ የግብረ-ሰናይ ድርጅት በሰጣት ሁለት ቀፎ ንቦች እና ራሷ በገዛቻቸው ሶስት ቀፎ ንቦች ነበር። ይሁንና ከአምስቱ ቀፎዎች መካከል ሁለቱ ወደ ዘመናዊ ቀፎ ለማዘዋወር ስትሞክር የተሰደዱ ሲሆን ሶስቱ ግን አሁንም አሉ። በዚህ ዓመት ማር ያልቆረጠችው ሰውነት «ንቦቹ እንዲለምዱ ብለን» ነበር ስትል ትናገራለች።

በኢትዮጵያ በማር አምራችነቱ በሚታወቀው ጎጃም አካባቢ በጣና ምስሊ ቀበሌ ገበሬ ማህበር የሚኖረው ወለላው መሬ እንደ ሰውነት ሁሉ አዲስ የንብ አናቢ ነው። በግብርና ሥራ ኑሮውን የሚገፋው ወለላው ንብ ማነብን የጀመረው የተሻለ ገቢ ለማግኘት አቅዶ ነበር። አሁን ለንቦቹ ዘመናዊ ቀፎዎች ያዘጋጀው ወለላው አዲስ በጀመረው ሙያው ከፍተኛ ጥራት እና ብዛት ያለው ማር እና ሰም ለማምረት እቅድ አለው።

የተለያየ ሥነ-ምህዳር እና የእጽዋት ዝርያ ያላት ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥራት እና መጠን ያለው ማር እና ሰም የማምረት እምቅ አቅም እንዳላት ይነገራል። ዘርፍ የእድሜውን ያክል ለውጥ አላሳየም እየተባለ ይወቀስ እንጂ ከአስር ሚሊዮን በላይ ህብረ-ንብ (Bee Coloney) እንዳላት ይገመታል። ግምቱ እውነት ከሆነ ከአፍሪቃ አገራት በንብ ሐብት ቀዳሚ ያደርጋታል። የኢትዮጵያ ንብ ሐብት ቦርድ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ነጋሽ በቃና በአገሪቱ 1.8 ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች በንብ ማነብ ስራ መሰማራታቸውን ይናገራሉ።

«የኢትዮጵያ ማር የማምረት አቅም 500,000 ቶን ይገመታል። ሰም የማምረት አቅማችን ደግሞ ደግሞ ወደ 50,000 ቶን ይገመታል» ሲሉ የሚናገሩት ኃላፊው አገሪቱ የምታመርተው ግን 55,000 ቶን አካባቢ ማር እና 5,000 ቶን ሰም ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ አንድ አጥቅ ሆኖ ለዘመናት የቆየው የንብ ማነብ ሥራ በዋናነት አነስተኛ የእርሻ ማሳ ባላቸው ገበሬዎች ዘንድ ይዘወተራል። የቤት እንስሳት ጥናት ለገጠር ልማት (Livestock Research for Rural Development) የተሰኘ ተቋም ይፋ ያደረጋቸው ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በመላ አገሪቱ ጠንካራ መሰረት ካለው የንብ ማነብ ስራ የሚገኘው ገቢም ይሁን ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽዖ ግን አመርቂ አይደለም። ሰውነት ከብቴ እና ወለላው ማሬ በሚኖሩበት የደራ ወረዳ 15,000 ገበሬዎች ከእርሻ ስራ በተጓዳኝ የንብ ማነብ ስራ ይከውናሉ።በወረዳው ከእርሻ ሥራ በተጓዳኝ ንብ የሚያንቡ 15,000 ሰዎች የሚገኙ ሲሆን በዓመት ከ96-150 ቶን የሚደርስ ማር እንደሚመረት በአማራ ክልል በደራ ወረዳ የንብ ሐብት ባለሙያ የሆኑት አቶ አለነ ሁናቸው ተናግረዋል

በኢትዮጵያ ከሚመረተው የንብ እና የሰም ምርት ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ከ1% እንደማይልቅ የሚናገሩት አቶ አቶ ነጋሽ በቃና አንድ ኪሎ ማር በ3.5 ዶላር እንደሚሸጥም አስረድተዋል። አገሪቱ ከ500-600 ቶን ወደ ውጭ የምትልክ ሲሆን አንድ ኪሎ ሰም ከ8-10 ዶላር እንደሚሸጥም ጨምረው ተናግረዋል።።

የንብ አረባብ ባለሙያው አቶ ጥላሁን ገበይ ንቦች ለልማት በኢትዮጵያ የተሰኘ የግብረ-ሰናይ ድርጅት መስራችና ኃላፊ ናቸው። ድርጅታቸው በንብ ማነብ ሥራ ለተሰማሩ አነስተኛ ገበሬዎች በማር እና ሰም አመራረት እና ግብይት ላይ ስልጠና ይሰጣል። በደራ ወረዳ የአቶ ጥላሁን ገበይ ንብ ለልማት ለልማት ኢትዮጵያ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን ሰውነት ከብቴ እና ወለላው መሬን ጨምሮ ለ 20 ወጣቶች እቅርቧል። የወረዳው የንብ ሐብት ባለሙያ አቶ አለነ ሁናቸው ከነባሩ የንብ ቀፎ ይልቅ የተሻሻሉት የተሻለ ምርት ለማግኘት እንደሚያግዙ ይናገራሉ። ንብ የማነብ ስራውን አነስተኛ መሬት ላላቸው ገበሬዎች እና ወጣቶች በመምረጥ ማስፋፋት የተጀመረ ሲሆን የውጤታማ ገበሬዎችን ተሞክሮ ወደ ሌሎች ገበሬዎች ዘንድ በማስፋፋት ላይም ይገኛል።

ለበርካታ ሺህ ዓመታት ሲተገበር የቆየው የኢትዮጵያ ባህላዊ የንብ ማነብ ሥራ የተሻለ የደን ይዞታ ባላቸው የደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች የተለመደ ነው። በመኖሪያ ቤቶች ጓሮ በተንጠለጠለሉ የንብ ቀፎዎች የሚያካሄደው ሌላኛው የማነብ ሥራ ግን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የተለመደ ነው። የንብ ማርቢያ ቀፎዎች እና የማር መቁረጫ ቁሳቁሶች እንደ የአካካባቢው ባህል የተለያዩ ቢሆኑም ኋላ ቀርነታቸው ግን ያመሳስላቸዋል። አቶ ነጋሽ በቃና ዘርፉ ኋላ ቀር ቢሆንም ስራ አጥነትን ለመቀነስ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ላቅ ያለ ሚና ሊጫወት ይችላል የሚል እምነት አላቸው።

በኢትዮጵያ ከሚገኙ ህብረ-ንቦች 97% አሁንም በባህላዊ ቀፎ ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ለንቦችም ይሁን ለማር እና ሰም አመራረት አመቺ የሚባሉ የንብ ቀፎዎች (framed hive) በአገሪቱ ቢገኙም ለአብዛኛው ንብ አናቢ አልተዳረሱም። ዘመናዊዎቹ የንብ ቀፎዎች ውድ ከመሆናቸውም ባሻገር በገጠራማው የአገሪቱ ክፍል የሚገኘው ገበሬ ስለመኖራቸው ጭምር ግንዛቤ የለውም። አቶ ጥላሁን ገበይ ዘመናዊዎቹ የንብ ቀፎዎች ንቦችን ከሞት ለመታደግ ጭምር ጠቀሜታ እንዳላቸው ያስረዳሉ።

ከጎርጎሮሳዊው 1999 ዓ.ም. ጀምሮ የህብረ-ንብ መቀነስ መላው ዓለምን ያሳሰበ ክስተት ነው። ክስተቱ በሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ፤አውሮጳ እና ህንድ እጅጉን አሳሳቢ ከሆነ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ከሁለት አመት በፊት የበርክሌ ዩኒቨርሲቲ ይፋ ያደረገው ጥናታዊ ጽሑፍ ጠቁሟል። ኢትዮጵያ ለአሁኑ ይህ አደጋ የገጠማት አይመስልም። ይሁንና አለ የሚባለው እምቅ ሐብት የተሻለ ጠቀሜታ መስጠት የሚችለው «የእውቀትና የክህሎት ችግሮችን በመለወጥ፤ዘመናዊ የማምረቻ ቁሳቁሶች በማቅረብ፤የገበያ ሰንሰለቱን በማሻሻል እና የምርት ጥራት መመዘኛ መሳሪያዎች በማሟላት»መሆኑን የኢትዮጵያ ንብ ሐብት ቦርድ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ነጋሽ በቃና ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic