የማርሻል የግንባታ አቅድ የተፈረመበት 60ኛ ዓመት፧ | ዓለም | DW | 03.04.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የማርሻል የግንባታ አቅድ የተፈረመበት 60ኛ ዓመት፧

እ ጎ አ ሚያዝያ 3 ቀን 1948 ዓ ም፧ (ከ 60 ዓመት በፊት በዛሬዋ ዕለት መሆኑ ነው)የያኔው የዩናይትድ እስቴትስ ፕሬዚዳንት Harry S. Truman ፧ “Foreign Assistance Act” (የውጭ እርዳታ ደንብ) በተሰኘው የህግ ሰነድ ላይ ፊርማቸውን አስቀመጡ።

ጆርጅ ካትሌት ማርሻል፧ ለምዕራብ አውሮፓ መልሶ ግንባታ፧ በስማቸው የሚጠራውን አቅድ ያወጡት የቀድሞው የአሜሪካ ው. ጉ.ሚ.

ጆርጅ ካትሌት ማርሻል፧ ለምዕራብ አውሮፓ መልሶ ግንባታ፧ በስማቸው የሚጠራውን አቅድ ያወጡት የቀድሞው የአሜሪካ ው. ጉ.ሚ.

እቅዱ ከዚያ በኋላ ተግባራዊ ሆነ። ለነገሩ፧ በስማቸው እንዲጠራ የተደረገውን አቅድ፧ የዚያው ዘመን የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር George Catlet Marshall ይፋ ያሳወቁት፧ አያሌ ወራት ቀደም ብሎ፧ ሰኔ 5 ቀን 1947 ዓ ም፧ በዕውቁ የሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ባሰሙት ንግግር ላይ ነበር። ከስድሳ ዓመት በፊት የአሜሪካ ምክር ቤት ያጸደቀው «ማርሻል ፕላን« እየተባለ የሚጠቀሰው፧ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ በኋላ፧ ምዕራብ አውሮፓን መልሶ ለመገንባት የወጣው እቅድ፧ በ 20ኛው ክፍለ ዘመን በዓይነቱ ወደር የማይገኝለት..እስከመባልም ደርሷል።.... የዶይቸ ቨለ ባልደረባ የነበረውና በቅርቡ፧ በህመም ሳቢያ፧ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው Thomas Kirschning ቀደም አድርጎ አሰናድቶት የነበረውን ጽሑፍ ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው ሰብሰብ አድርጎ አጠናቅሮታል።
«ዩናይትድ እስቴትስ አሜሪካ፧ በተቻላት አቅም ሁሉ፧ በዓለም ዙሪያ ኤኮኖሚ እንዲያንሠራራ አስተዋጽዖ ታደርጋለች። የፖለቲካ አመረር ዘይቤአችን፧ በማንኛውም ሀገር ወይም ርዕዮት ላይ ያነጣጠረ አይደለም። የሚያተኩረው፧ በረሃብ፧ ድኅነት፧ ቀቢጸ-ተስፋና ቀውስ ላይ ነው«። የያኔው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጆርጅ ካትሌት ማርሻል ነበሩ፧ ይህን ያሉት። ማርሻል፧ ባወጡት አቅድ መሠረት፧ በጦርለት ለደቀቁት የምዕራብ አውሮፓ አገሮች፧ የገንዘብ እርዳታ ተሰጠ፧ ምግብ በሰፊው እንዲቀርብላቸው ተደረገ። እንዲሁም የዴሞክራሲ መዋቅሮች ተዘረጉላቸው። ከሁሉም፧ በጦርነቱ ወቅት በጠላት ጎራ ተሰልፈው የወጓቸውንና፧ በመጨረሻ ድል የሆኑትን፧ አሜሪካውያን የበቀል እርምጃ አልወሰዱባቸውም።
ከዚህም ሌላ፧ እርዳታ ተቀባዮቹ አውሮፓውያን፧ የኀዘን ቀስቃሽ፧ የምሬትና የበቀል አስታዋሽ ከሆኑት የመቃብር መካናት ባሻገር፧ ለአዲስ ጅምር ለአዲስ ዘመን፧ በኅብረት እንዲንቀሳቀሱ አሜሪካ ምክሯን መለገሥና ድጋፏንም መስጠቱን ገፋችበት። እ ጎ አ ከ 1948-1952 ዓ ም፧ 16 የአውሮፓ አገሮች፧ በዚያው ዘመን የገንዘብ ጥንካሬ፧ 14 ቢልዮን ዶላር ነበረ የፈሰሰላቸው። እ ጎ አ በ 1949 ዓ ም ለተመሠረተችው የጀርመን ፌደራል ሪፓብሊክ(ምዕራብ ጀርመን)በዚያው ዓመት 1.3 ቢልዮን ዶላር እርዳታ ነበረ ያገኘች።
ለመለዋወጫ ዕቃዎች በመጀመሪያ፧ በዶላር እንጂ ደካማ በነበረው በጀርመን ማርክ አይከፈልም ነበረ። የአውሮፓ የገንዘብ ማዕከል፧ በዝቅተኛ ወለድ ብድር እየተሰጠ ገንዘብ ሥራ ላይ የሚውልበትን የረጅም ጊዜ አቅድ ሲወጣ፧ የአውሮፓ የማገገሚያ መርኀ ግብር (European Recovery Programme )ተዘረጋ። ከዚህ የገንዘብ ማዕከል ወለድ በመጨመር፧ በመጨረሻ የማርሻል ፕላን፧ የገንዘብ ብድር ተመልሶ የሚከፈልበት ሁኔታ እንዲመቻች ተደረገ። የማርሻል ፕላን ሦስት ዐበይት ጉዳዮች እንዲከሠቱ አበቃ። የአውሮፓ አገሮች፧ ተባብረው፧ አንድ ላይ እንዲሠሩ፧ የፖለቲካና የኤኮኖሚ የአሠራር ልውውጥ እንዲያደርጉና ከዓለም ኤኮኖሚ ጋር እንዲቆራኙ አስቻለ። ሁለተኛ፧ የገንዘብ ተቋም እንዲኖራቸው፧ ገንዘብ ሥራ ላይ የሚውልበትን ሁኔታ የሚያመቻቹበት መንገድ ተፈጠረ።
ሦስተኛ፧ የማርሻል ፕላን፧ በምዕራብ አውሮጳ የሶሺያሊስት ፍልሥፍናም ሆና ርዕዮት ቦታ እንዳይኖረው የሚታገል ሥርዓት እንዲቋቋም አደረገ።
ጀርመን፧ የማርሻል ፕላን ይፋ ተባባሪ ሀገር መሆኗ የተገለጠው፧ እ ጎ አ ታኅሳስ 15 ቀን 1949 ዓ ም፧ ቦን፧ ውስጥ በ Alexander König ቤተ-መዘክር በሚገኝ አንድ አዳራሽ፧ የያኔው መራኄ-መንግሥት፧ ዶክተር ኮንራድ አደናዎር በጊዜያዊው ጽህፈት ቤታቸው፧ ከአሜሪካ መንግሥት ተወካይ McCloy ጋር ውል እንደተፈራረሙ ነው።
አደናዎር ያኔ እንዲህ የሚል ንግግር አሰምተው ነበር።
«የምዕራብ አውሮፓ ኤኮኖሚ፧ በተለይ የጀርመን፧ ላገገመበት ሁኔታ፧ ዩናይትድ እስቴትስ፧ በማርሻል ፕላን በኩልና ከዚያም ውጭ፧ እጅግ ከፍ ያለ ወሳኝ ድርሻ አበርክታለች። በዝች ቅጽብ፧ እንደገና የጀርመንን ህዝብ ልባዊ ምሥጋና እንዳቀርብ ይፈቀድልኝ።! አሁን በቀረበው ውል መሠረት፧ በርሊንንም በሚገባ መርዳት የምንችል በመሆናችን ደስ ይለናል።«
ዩናይትድ እስቴትስ፧ ኮሙኒስታዊም ሆነ ሾሲያሊስታዊ ፍልስፍና በምዕራብ አውሮፓ እንዳይሠርፅ ለማድረግም ነው በማርሻል ፕላን በኩል ተጋድሎ ያደረገችው። ከጦርነቱ በኋላ፧ የምዕራብ አውሮፓ ህዝብ ለረጅም ጊዜ በረሃብ ከማቀቀ፧ በድህነት ከተጎሳቆለ፧ በቀላሉ በ ሾያሊስትም ሆነ ኮሙዩኒስት ርዕዮት ይማረካል የሚል ሥጋት፧ በዩናይትድ እስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ውስጥ እንደነበረ አልታበለም። ምንም እንኳ ሶቭየት ኅብረትና ዩናይትድ እስቴትስ፧ ፋሺስት ወይም ናዚ ጀርመንን ለማንበርከክ የጦር ተጓዳኞች እንደነበሩ ቢታወቅም፧ የፖለቲካ ሥርዓት በማስፋፋት ረገድ፧ ዋሽንግተን፧ ሞስኮን፧ አደገኛ ተቀናቃኝ አድርጋ ነበረ የምትመለከታት።
ማርሻል ፕላን፧ ለምዕራብ ብቻ ሳይሆን ለምሥራቅ አውሮፓም የታሰበ እንደነበረ ይነገርለታል። ሆኖም፧ ፓሪስ ላይ በተካሄደ ጉባዔ፧ በጦርነቱ ይበልጥ የተጎዱ አገሮች ላቅ ያለ ድርሻ ያግኙ በሚለው ነጥብ፧ የሀሳብ ልዩነት ተፈጥሮ፧ በዚያ ዘመን የሶቭየት ውጭ ጉዳይ ሚንስትር የነበሩት ቪያትሸስላቭ ማኻኢሎቪች ሞሎቶቭ ስብሰባውን አቋርጠው መመለሳቸውና ጉዳዩ በዚሁ እንዳበቃለት ነው የሚነገረው። በመሆኑም፧ ማርሻል ፕላን፧ የምዕራብ አውሮፓ የመልሶ ማቋቋሚያ አቅድ ሆኖ ቀረ። የዚህ ግንባታ ማዕከል የጀርመን ፌደራል ሪፓብሊክ ነበረች። ማርሻል ፕላን፧ ምዕራብ አውሮፓን መልሶ ቢገነባም፧ ምዕራቡና ምሥራቁ ዓለም ይበልጥ እንዲለያይ፧ አስተዋጽዖ አድርጎ ነው ያለፈው።