የማርሻል እቅድ እና አፍሪቃ | አፍሪቃ | DW | 20.01.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የማርሻል እቅድ እና አፍሪቃ

አፍሪቃን መርዳት ሞራላዊ ግዴታ ብቻ ሳይሆን አውሮጳንም የሚጠቅም መሆኑን  የጀርመን የኤኮኖሚ ትብብር ሚንስትር ጌርድ ሚውለር  አስታወቁ። ሚውለር ይህን ያሉት ለአፍሪቃ የተዘጋጀውን አዲስ የትብብር እቅድ ትናንት በበርሊን ለፌዴራዊው ምክር ቤት ቡንድስታግ የልማት ትብብር ኮሚቴ ባቀረቡበት ጊዜ ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:26

የልማት ትብብር ርዳታ

የጀርመን የኤኮኖሚ ትብብር ሚንስትር ጌርድ ሚውለር ባቀረቡት ወደ 30 የሚጠጉ ገፆች ባሉት እና «የማርሻል እቅድ» የሚል ስያሜ  በያዘው ሰነድ ከአፍሪቃ ጋር በትምህርት፣ በንግድ፣ በኤኮኖሚ ልማት እና በኃይል አቅርቦት ዘርፎች አዲስ የትብብር ደረጃ መፍጠር ያስችላሉ ያሏቸውን አሰራሮች ዘርዝረዋል። 
«ከአፍሪቃ ጋ በእሴቶች ላይ የተመሰረተ ትብብር እንዲኖር እፈልጋለሁ። የጋራ ጥቅም አለን። ጀርመን እና አውሮጳ በዚያ የሰዎች ሕልውናን ለማረጋገጥ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመገደብ፣ ፍልሰትን ለማስቀረት እና የአፍሪቃ ወጣቶችን የወደፊት ዕድል ለማስተካከል የጋራ ፍላጎት አላቸው።»
ገንዘብ  በሕገ ወጥ መንገድ ከአፍሪቃ በሚወጣበት እና ብሔራት አቀፍ ተቋማትም ግብር ከመክፈል በሚሸሹበት አሰራር አንፃር ጠንካራ ትግል ሊደረግ እንደሚገባም ሚውለር አክለው ጠቁሟል።  ሚንስትሩ ከአፍሪቃ ፣ በተለይ ሙስናን እና የተዛባ ኤኮኖሚያዊ አሰራርን በመታገሉ፣ መልካም አስተዳደር በሚዳብርበት እና የሴቶች እኩልነት በሚረጋገጥበት ረገድ ብዙ እንደሚጠብቁ አስረድተዋል። አሁን በወጣው እቅድ መሠረት፣ ይህን መሰሉን ተሀድሶ የሚያራምዱትን ሃገራት ጀርመን ወደፊት በይበልጥ በመርዳት፣ ለአፍሪቃ ከምትሰጠው የልማት ትብብር  ርዳታ መካከል ወደፊት 20 በመቶዉን በተጨማሪ ለነዚህ ሃገራት ልማት ለማዋል አቅዳለች።  መንግሥት የሚሰጠው የልማት ርዳታ የግል ብዑላን ገንዘባቸውን እንዲያሰሩ የሚያበረታታ ኃይል አድርገው የሚመለከቱት ጌርድ ሚውለር የጀርመንን ኤኮኒሚ ትብብር ሚንስቴር ያስቀመጣቸውን ዓላማዎች ከግብ ለማድረስ የግሉ ዘርፍም ጠንክሮ እንዲንቀሳቀስ  ጥሪ አቅርበዋል።

እስከዛሬ ወደ 1,000 የሚጠጉ የጀርመን ተቋማት ናቸው አፍሪቃ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱት። ሙስና፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት ወይም የተንዛዛ ቢሮክራሲ ብዙዎችን ገንዘባቸውን ከማሰራት ቆጥቧቸዋል። 
መንግሥት የግል ብዑላንን ለማበረታታት ለምሳሌ ገንዘባቸውን በአፍሪቃ  ለማሰራት ለሚፈልጉ የጀርመን ባለተቋማት ብድር የሚያገኙበትን አሰራር  እንደሚያቃልል ሚንስትሩ አስታውቀዋል። በጀርመን ኤኮኖሚ ውስጥ የአፍሪቃን ጉዳይ የሚከታተለው ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ክርስቶፍ ካነንጊሰር ሀሳቡ የሚደገፍ መሆኑን ቢገልጹም፣ የማርሻል እቅዱ በተግባር የሚተረጎምበት አሰራር ግልጽነት ይጎድለዋል ሲሉ ትችት ሰንዝረዋል።
« ይህ ሚንስትሩ ያሉት ሁሉ ትክክለኛ ነው። በተለይም በአህጉሩ የግል ወረትን የማነቃቃቱ እና የግል ብዑላንን ታታሪነት የማቃለሉ ሀሳብ።  እያንዳንዱ በተጨባጭ ምን ማድረግ እንደሚፈልግ ሰፊ ውይይት ሊደረግበት ይገባል ብዬ አምናለሁ። የማርሻል እቅዱ አሁንም ግልፅ አይደለም። ስለዚህ የኤኮኖሚው ዘርፍ እቅዱን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ተጨባጭ ዘዴዎች እንዲቀርቡለት ይጠብቃል። »

ብዙ የዘርፉ ባለሙያዎች የማርሻል እቅዱ ተግባራዊ መሆኑን ተጠራጥረውታል። ጌርድ ሚውለር ያቀረቡዋቸውን በርካታ ሀሳቦች ብቻቸውን ሥራ ላይ ሊያውሉ አይችሉም፣ እንደ ባለሙያዎቹ። በንግዱ ጉዳይ ላይ ብዙው ኃላፊነት ያለው በአውሮጳ ኅብረት እጅ ነው። ለምሳሌ በአፍሪቃ ምርቶች ላይ የሚሰራበትን የንግድ ማከላከያ ርምጃ ማንሳት የሚችለው ኅብረቱ ነው።  ሌሎቹ የጀርመን ሚንስቴሮች እስካሁን በሚውለር እቅድ ላይ አስተያየት አልሰጡም። አንዳንዶች የራሳቸውን የአፍሪቃ ስልት በማዘጋጀት ላይ ናቸው። ጀርመን የቡድን 20 ፕሬዚደንትነትን ስልጣን በያዘችበት ባሁኑ ጊዜ አፍሪቃን በቡድኑ ዋነኛ የመወያያ አጀንዳ  የማድረግ ፍላጎት መኖሩን የገለጹት ሀምበርግ የሚገኘው በምህፃሩ «ጊጋ» የሚባለው የፖለቲካ ጥናት ተቋም ተንታኝ ሮበርት ካፐል፣ ሚንስቴሮቹ ባንድነት እስካልሰሩ ድረስ የማርሻል እቅዱ መሳካት አጠራጣሪ ነው።
« የሚመለከታቸው ሚንስቴሮች ሁሉ በመራሒተ መንግሥቷ ጽሕፈት ቤት አመራር ሥር እንዲውሉ እና አንድ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መመሪያ እንዲያወጡ፣ ከዚያም  የቡድን 20 ን ስምምነትን እንደሚያፈላልጉ ተስፋ አደርጋለሁ። ሁላችንም በተናጠል የምንሰራ ከሆነ ግን፣ እቅዱ አይሳካም። »

ዳንዬል ፔልስ/አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ

 


 

Audios and videos on the topic