የማራካሹ የአየር ንብረት ለዉጥ ጉባኤ | ጤና እና አካባቢ | DW | 08.11.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

የማራካሹ የአየር ንብረት ለዉጥ ጉባኤ

የተመድ የአየር ንብረት ለዉጥን ለመግታት የደረሰበት ስምምነት 97 የድርጅቱ አባል ሃገራት መቀበላቸዉን ካረጋገጡ በኋላ ሥራ ላይ ዉሏል። ለዉጡን ያስከተሉ መዘዞች ላይ ተገቢዉ ርምጃ ተወስዶም የዓለም የሙቀት መጠን በያዝነዉ ምዕተ ዓመት ማለቂያ ላይ ከ2,4 ዲግሪ ወደ 2,7 ዲግሪ ከፍ ሊል እንደሚችል አንድ ጥናት አመልክቷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:35
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:35 ደቂቃ

ብክለትን ቅነሳ

 

22ኛዉ በተለያዩ ቡድኖች መካከል የሚካሄደዉ የአየር ንብረት ጉባኤ ወይም COP 22 ከትናንት ጀምሮ ለቀጣይ 10 ቀናት ማራካሽ ሞሮኮ ላይ ተጀምሯል። በዚሁ ጊዜም የኪዮቶ ስምምነት እንዲቀጥል የሚሹት ቡድኖች 12ኛዉ ስብሰባም ይካሄዳል። ባለፈዉ ዓመት ፓሪስ ላይ በተመድ የአየር ንብረት ለዉጥ ተከታታይ ጉባኤ አማካኝነት የተላለፈዉ ዉሳኔ በአጭር ጊዜ ዉስጥ የዓለማችን ቀንደኛ ሙቀት አማቂ ጋዝ ለቃቂዎች ዩናትድ ስቴትስ፣ ቻይና እና ሕንድ እንዲሁም የአዉሮጳ ኅብረት አባል ሃገራትን ጨምሮ በ97 ሃገራት መጽደቁ ታሪካዊ ተብሏል።

ለመሆኑ የዚህ ስምምነት ዓላማ ምንድነዉ?

ከዓላማዎቹ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰዉ የዓለምን የሙቀት መጠን ከሁለት ዲግሪ እንዳይበልጥ፤ ቢቻልም በ1,5 ዲግሪ እንዲወሰን ማድረግ የሚለዉ ነዉ። ይህን ለማሳካት ደግሞ የሙቀት አማቂ ከባቢ አየር በካይ ጋዞች ልቀት በአስቸኳይ መቀነስ ይኖርበታል። ወደ ከባቢ አየር በመግባት ሙቀትን ከሚያምቁ ጋዞች ከቅሪተ አፅም የሚገኘዉ ነዳጅ ዘይት ሲቃጠል የሚወጣዉ CO2 72 በመቶዉን ይይዛል። በዚያ ላይ በፍጥነት የሚታየዉ የደኖች መራቆት ችግሩን አባብሷል። እየጨመረ የሚሄደዉን የዓለም የሙቀት መጠን ለመገደብም የድንጋይ ከሰል፤ ቤንዚን እና ጋዝን ኃይል ምንጭነት እስከ ጎርጎሪዮሳዊዉ 2050ዓ,ም ድረስ በሌላ መተካትን አልሟል። ከCO2 በተጨማሪ ከእርሻዉ ኢንዱስትሪ የሚወጡት ሜቴን እና ናይትሪየስ ኦክሳይድም ከዓለም የሙቀት መጠን ሩብ ለሚሆነዉ ተጠያቂዎች ናቸዉ። የደን ልማትን ማስፋፋቱ በዛፎች አማካኝነት CO2ን ከከባቢ አየር ለማጽዳት እንደሚረዳ ይታመናል። እንዲያም ሆኖ ግን ዓለም አቀፉ የአየር በረራ አገልግሎቱ  በዚህ ስምምነት ቦታ የተሰጠዉ አይመስልም። እስካሁን ባለዉ መረጃ መሠረት የበረራዉ መጓጓዣ ዘርፍ አምስት በመቶዉን ሙቀት አማቂ ጋዝ ይለቃል። እንደ መርከብና ጀልባዎች ያሉ የባህር ላይ መጓጓዣዎችም ከብክለቱ የ3 በመቶዉን ድርሻ ይወስዳሉ።

እንዲያም ሆኖ የተመድ የአየር ንብረት ለዉጥ የስምምነት ማዕቀፍ እንደሚያመለክተዉ ሃገራቱ እንቀንሳለን ያሉት የብክለት መጠን የዓለምን ሙቀት እንደታሰበዉ ከ2 ዲግሪ ወይም ከ1,5 ዲግሪ እንዳይበልጥ ለማድረግ በቂ አይደለም። በአየር ንብረት ተፅዕኖ ላይ ምርምር የሚያካሂደዉ የጀርመኑ ፖስታድም ተቋም እንደሚለዉ ከሆነ የተባሉት ዕቅዶች ሁሉ ተግባራዊ ቢሆኑም እንኳን የዓለም የሙቀት መጠን በ21ኛዉ ምዕተ ዓመት ማለቂያ ላይ ከ 2,4 እስከ 2,7 ዲግሪ መጨመሩ አይቀርም።

«ሁሉም ሃገራት እናደርጋለን ያሉትን እንኳ ተግባራዊ ቢያደርጉ በቂ አይደለም። ሁሉም ሃገራት ካቀዱት የበለጠ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ይህንንም ሃገራት ያሉት ተግባራዊ ማድረግ አለማድረጋቸዉ ደግሞ የሚመረመርበት ጊዜ ይኖራል። ከዚያም የበለጠ ማድረግ ይኖርባቸዋል።»

ይላሉ የጀርመኑ የተንታኞች ቡድን የኒዉ ክላይሜት ተቋም መሥራች ኒክላስ ኾህነ። እንዲያም ሆኖ ይላሉ ኾህነ የፓሪሱ ስምምነት በአጠቃላይ ሲታይ ሁሉም መንግሥታት የአየር ንብረት ለዉጥን የምር መመልከታቸዉ እና አንዳች ርምጃ ለመዉሰድ ዝግጁ መሆናቸዉን ለዓለም ጠንካራ መልዕክት ያስተላለፈ ነዉ።

አሁን ያለዉ የዓለም የሙቀት መጠን እንደተፈራዉ እየጨመረ ቢሄድም እንኳን ግን የባህር ዉስጥ እፅዋት ይኖራሉ፤ የባህር ወለል ከፍታም 40 ሴንቲ ሜትር ብቻ ነዉ እስከ 2100ዓ,ም ድረስ የሚጨምረዉ። በአሁኑ ወቅት 46 ሚሊየን የሚሆነዉ የዓለም ሕዝብ ከባህር ወለል በግማሽ ሜትር ከፍታ ላይ ነዉ የሚገኘዉ። ከ2 ዲግሪ በላይ የዓለም ሙቀት ከበለጠ ግን የባህር ዉስጥ ተክሎቹ አይኖሩም፤ ድርቅ፣ ከባድ ማዕበሎችና የሰብል መምከን በቀጣይ የሚመጡ መዘዞች ይሆናሉ። በባህር ዳርቻ አካባቢ ለሚገኙ ሃገራት እና ለደሴት ሃገራት ደግሞ እጅግ የከፋ ጥፋት ሊያስከትል እንደሚችል የተቋሙ ጥናት ያመለክታል። በምሳሌነትም ኔዘርላንድስ፣ ባንግላዴሽ፣ ቬኒሲያ፣ ኒዉዮርክ፣ ቶክዮ፣ ሲድኒ፣ ሜልበርን እና ለንደን የጉዳቱ ሰለባዎች ሊሆኑ እንደሚችሉም ተንብዩዋል።

የሃገራቱ ቁርጠኝነት እስከምን ድረስ ነዉ?

በፓሪሱ ጉባኤ ላይ እንደ ትልቅ ዉጤት ከታዩት ጉዳዮች አንደኛዉ ሃገራት በየበኩላቸዉ ወደ ከባቢ አየር የሚለቁትን የብክለት መጠን ለመቀነስ መወሰናቸዉና መጠኑንና ጊዜዉንም መጠቆማቸዉ ነዉ።ምንም እንኳን እንደየ ሃገራቱ እና የእድገት ሁኔታቸዉ ቢለያይም። ለምሳሌ የአዉሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት እስከ ጎርጎሪዮሳዊዉ 2030 ዓ,ም ድረስ በ40 በመቶ የብክለት መጠን ለመቀነስ ቃል ገብተዋል። ዩናይትድ ስቴትስ ጸመጪዉ 9 ዓመታት ከ26 እስከ 28 በመቶ እቀንሳለሁ ብላለች። ታዳሽ የኃይል ምንጮችን ለማስፋፋት ከፍተኛ ሥራ እያከናወኑ መሆኑ የተነገረላቸዉ ሞሮኮ እና ቻይናም ብክለትን ለመቀነስ ቃላቸዉን ሰጥተዋል። የአሁኑ ጉባኤ አስተናጋጅ ሞሮኮ በመጪዉ 14ዓመታት ዉስጥ ለኤሌክትሪክ አቅርቦቷ 52 በመቶዉ በታዳሽ የኃይል ምንጭ እንዲተካ ትፈልጋለች። ቻይና በበኩሏ ከፍተኛ የሙቀት አማቂ ጋዞች ቅነሳ በተጠቀሰዉ ጊዜ ለማድረግ ነዉ ያሰበችዉ። ጀርመን ማድረግ ይገባታል ያሉትን ኒክላስ ኾህነ ይናገራሉ።

«ለምሳሌ ጀርመን የፓሪስን ስምምነት እዉን ለማድረግ ከተነሳች ከድንጋይ ከሰል ኃይል የሚያመነጩ ተቋማቷን በቀጣይ ከ10 እስከ 15 ዓመት መዝጋት ይኖርባታል። ከቅሪተ አፅም በሚገኝ ነዳጅ የሚዘወሩ የመጨረያ መኪናዎቿንም እስከ 2030 ዓ,ም ድረስ ወይም ከዚያ በፊት ሸጣ መጨረስ ይኖርባታል።»

 

ለአየር ንብረት ለዉጥ መንስኤ የሆነዉ መሠረታዊ ጉዳይ በኢንዱስትሪ የበለፀጉትን ሃገራት በቀጥታ ይመለከታል። በዚህም ምክንያት ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2020ዓ,ም ጀምረዉ ለድሀ  እና በአየር ንብረት ለዉጡ ምክንያት ለጉዳት ለተጋሉት ሃገራት በየዓመቱ መቶ ቢሊየን ዶላር ከስምምነት ተደርሷል። ገንዘቡ ለተጠቀሱት ሃገራት የአረንጓዴ አየር ንብረት ድጋፍ በሚል ጽዱ የኃይል ምንጮችን ለማስፋፋት የሚሰጥ ነዉ።

ከተመድ የአየር ንብረት ተመልክች ጉባኤ የወጡ መረጃዎች የሚያመለክቱት ፓሪስ ላይ የተደረሰዉ ስምምነት ተግባራዊ ሆኖ ኤኮኖሚዉ ከካርቦን የፀዳ እንዲሆን ጥረቱ እየጨመረ መሄዱን ነዉ። በአሁኑ ወቅትም በመላዉ ዓለም ሰዎች የድንጋይ ከሰል እና የነዳጅ ዘይትን ወደ ጎን በማለት ከፀሐይ እና ነፋስ ኃይል የሚያመነጩ ስልቶችን ለመጠቀም እየጣሩ ነዉ። ለደኖች የሚደረገዉ ክብካቤም ከፍ ብሏል። እንደ ድርጅቱ ዕምነትም ፓሪስ ላይ አምና የተሰባሰቡት የመንግሥታት መሪዎች የአየር ንብረት ለዉጥን ለመግታት የሚያስችል ማዕቀፍ አዘጋጁ፤ ከትናንት አንስተዉ ማራካሽ ላይ በሚያደርጉት ድርድር ደግሞ ፓሪስ ላይ የተስማሙበትን ለማሳካት መመሪያ ያወጡለታል። ይህን እዉን ለማድረግ ደግሞ አምስት ነጥቦች የማራካሹ ጉባኤ ዋነኛ መነጋገሪያ ጉዳዮች መሆን ይኖርባቸዋል።

1ኛ ተግባራዊ አስቸኳይ እና ቀጣይ የብክለት ቅነሳ ርምጃ፤ ይህም ማለት ሃገራት እንቀንሳለን ብለዉ ያቀረቡት የብክለት መጠን በቂ እንዳልሆነ ይፋ በመሆኑ ያንን መንግሥታቱ ዳግም ከሁለት ዓመት በኋላ ተመልክተዉ ለማሻሻል ቃል ገብተዋል። በማራካሹ ጉባኤ ታዲያ ይህን በተግባር ማሳየት ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ርምጃዎችንም አሁን መዉሰድ መቻላቸዉን ማረጋገጥl፤

በሁለተኛ ደረጃ፤ የፓሪሱ ስምምነት ተግባራዊነት ከሁለት ዓመት በኋላ መጠናቀቅ ይኖርበታል። ይህ ደግሞ ሃገራት  እንዴት በጋራ ለአካባቢያቸዉ ብክለት ተጠያቂ እንደሚሆኑ ማብራሪያ ይሰጣል፤ በተጨማሪም ከሁለት ዓመታት በኋላ እንቀንሳለን ያሉት ብክለት ምን ያህል በቂ ነዉ የሚለዉንም ይገመግማሉ፤

ሶስተኛዉ ነጥብ፤ ድሀ እና በአየር ንብረት ለዉጡ ምክንያት የተጉዱእ ንዲሁምና ለዚህ የተጋለጡ ሃገራት በሚደረግላቸዉ ድጋፍ የራሳቸዉን ከለዉጡ ጋር ተላምዶ የመኖርም ሆነ የራሳቸዉን የአየር ንብረት የሚጠብቁበትን ዕቅድ መመርመር፤ በአራተኛ ደረጃ ደግሞ፤ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2050ዓ,ም በኋላ ብክለትን እየቀነሱ መሄድ ለሚያስችል የረዥም ጊዜ ዕቅድ አመላካች ሃሳብ ማጠናቀር፤ አምስተኛ እና የመጨረሻ የተባለዉ ደግሞ በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት ለተከተለዉ ጉዳትና ጥፋት ግልፅ እና ተዓማኒ የመፍትሄ ሃሳብ ማመላከት ይጠበቅበታል።  የመንግሥታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለዉጥ ተመልካች ጉባኤ ዋና ፀሐፊ ፓትሪሲያ ኤስፒኖሳ ከፓሪሱ ጉባኤ ቀጥሎ የሚካሄዱት ጉባኤዎች በተለይም በማራካሹ ስብሰባ የሚጠበቁ በርካታ ተግባርን የሚጠይቁ ሥራዎች መኖራቸዉን ጠቁመዋል።

 

«የገንዘብ ድጋፍን፤ የቴክኒዎሎጂ ሽግግርን እንዲሁም አቅምን በመገንባቱ ረገድም ሆነ ተላምዶ መኖርን በሚመለከት መመሪዎችን ማዘጋጀት ይኖርብናል።»

ዛሬ ይፋ የሆነ አንድ ጥናት እንዳሳየዉ በማደግ ላይ ያሉ ሃገራት ከአየር ጠባይ ጋር በተያያዙ ጥፋቶች በኢንዱስትሪ ካደጉት ሃገራት የበለጠ ተጎጂ ሆነዋል። ጀርመን ዋች የተሰኘዉ ተቋም እንደሚለዉ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1996 እስከ 2015ዓ,ም ባሉት ጊዜያት ብቻም ሁንዱራስ፣ ማይናማር፣ እና ሄይቲ በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት ክፉና የተጎዱ ሃገራት ግንባር ቀደምቶቹ ናቸዉ። በ2015 ብቻ ክፉኛ ከተጎዱት ሃገራት መካከል ደግሞ ሞዛምቢህ፣ ዶሜኒካን ሪፑብሊክ እና ማላዊ ዋነኞች መሆናቸዉን ጥናቱ አሳይቷል። ተመራማሪዎቹ እንደሚሉትም የሙቀት መጠኑ እየጨመረ በሄደ መጠንም የሚደርሰዉ የተፈጥሮ ቁጣ እና ደጋዉ እየባሰና እየከፋ የሚሄድ ነዉ የሚሆነዉ። ይህን ለመከላከል ታዲያ መንግሥታ ማራካሽ ሞሮኮ ላይ በቃል የተናገሩትን ወደተግባር የሚለዉጡበትን ስልት ይቀይሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

 

 

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic