የማራቶን ድል በዘላቂነት ወደ ኢትዮጵያ ይመለስ ይሆን? | ስፖርት | DW | 07.04.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የማራቶን ድል በዘላቂነት ወደ ኢትዮጵያ ይመለስ ይሆን?

ፓሪስ ውስጥ በተካሄደው የማራቶን ሩጫ ውድድር አሸናፊ የሆነው ቀነኒሣ በቀለ ጡንቻው ላይ ህመም ባይሰማው ኖሮ የበለጠ ፈጣን ሠዓት ሊያስመዘግብ ይችል እንደነበር ለዶቸቬለ ገለፀ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል የዋንጫ ግስጋሴውን እያሳመረ ነው። ቸልሲ እና ማንቸስተር ሲቲ ዋነኞቹ የሊቨርፑል ተፎካካሪዎች ሆነዋል።

ማንቸስተር ዩናይትድ ስጋት ውስጥ ነው ያለው። የሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ነገ እና ከነገ በስትያ ይከናወናሉ። በዋናነት ጀርመኖች ከስፔኖች ጋር ተፋጠዋል። ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ፣ ፕሬሚየር ሊግ እና ቡንደስ ሊጋ ውጤቶች ከማለፋችን በፊት ቀዳሚው አትሌቲክስ ነው። በኦሎምፒክ የሩጫ ውድድር የሦስት ጊዜያት ባለድሉ አትሌት ቀነኒሣ በቀለ የመጀመሪያው በሆነው የማራቶን ሩጫ ፉክክር ትናንት ፓሪስ ውስጥ አሸናፊ በመሆን ክብርወሰን አስመዝግቧል። በሁለተኛነት ተከትሎት የገባው ልመንህ ጌታቸው ውድድሩ ከመጠናቀቁ በፊት በስህተት በመቆሙ ጥቂት ቢዘገይም፤ ከቀነኒሣ በ1 ደቂቃ ከ45 ሠከንዶች ልዩነት ለማጠናቀቅ ችሏል። በሴቶች የሩጫ ውድድርም የብርጓል መለሠ እና ዘምዘም አህመድ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ለመውጣት ችለዋል።

ቀነኒሣ በቀለ በፓሪስ ከኢትዮጵያውያን አድናቂዎቹ ጋር

ቀነኒሣ በቀለ በፓሪስ ከኢትዮጵያውያን አድናቂዎቹ ጋር

ባለፈው ሣምንት የግማሽ ማራቶን ውድድር ኬንያውያን አይለው ከፍተኛ ሽንፈት ቢደርስብንም፤ በትናንቱ የ42 ኪሎ ሜትር የማራቶን ሩጫ እነ ቀነኒሣ ድል በመቀዳጀት ክሰውናል። እንዲያም ሆኖ ግን የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን በማራቶን ሩጫ ዘርፍ ዘላቂ ውጤት ለማስጠበቅ ከፍተኛ የቤት ስራ ይጠብቀዋል።

የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ

ሊቨርፑል ቀሪ አምስት ጨዋታዎቹን በማሸነፍ ዘንድሮ ከ24 ዓመታት በኋላ በድጋሚ ዋንጫውን በማንሳት የቀድሞ ኃያልነቱን ሊመልስ ይችል ይሆናል የሚል ግምት ተሰጥቶታል።

ሊቨርፑል እጎአ ከ1980 አንስቶ ለመጨረሻ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት እስከሆነበት 1990 ዓም ድረስ ባሉት አስር ዓመታት ውስጥ ለ7 ጊዜያት ዋንጫውን በእጁ ለማስገባት የቻለ ጠንካራ ቡድን ነበር። ይሁንና ግን የዋንጫ ምኞቱ ከሁለት ዓስርት ዓመት በላይ ህልም ብቻ ሆኖ ቆይቷል። ዘንድሮ ግን ሊቨርፑል የቀድሞ ኃያልነቱን እያስመለሰ ይመስላል።

በትናንትናው ጨዋታ ሊቨርፑል ዌስትሐምን 2 ለ1 በማሸነፍ ነጥቡን ወደ 74 አሳድጎ በደረጃው ሠንጠረዥ አንደኝነቱን አሁንም ለማስጠበቅ ችሏል። በሁለተኛ ደረጃ የሚከተለው ቸልሲ በሁለት ነጥብ ተበልጧል። ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት ማንቸስተር ሲቲ በአራት ነጥብ ዝቅ ብሎ ሦስተኛ ነው። ሁለቱን ጨዋታዎች ካሸነፈ ማንቸስተር ሲቲ አንደኛነቱን ከሊቨርፑል ለመንጠቅ ይቻለዋል። ሊቨርፑል ግን ዘንድሮ የሚቀመስ አይመስልም።

የሊቨርፑል ስራ አስኪያጅ ብሬንዳን ሮጀርስ የፊታችን እሁድ ከዋነኛ የዋንጫ ተቀናቃኛችን ማንቸስተር ሲቲ ጋር ለምናደርገው ጨዋታ ፈጽሞ ጭንቀት የለብንም ብለዋል። ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ድል ከቀናው የዋንጫው ባለቤት የመሆን ምኞቱ ስኬታማ ለመሆን የቀለለ ይሆናል።

ማንቸስተር ዩናይትድ እና ባየርን ሙንሽን

ማንቸስተር ዩናይትድ እና ባየርን ሙንሽን

«ትልቅ ጨዋታ እንደሆነ አውቃለሁ።» አሉ፤ የሊቨርፑሉ ስራ አስኪያጅ፤ እሁድ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ስለሚያደርጉት ጨዋታ ሲያብራሩ። ቀጠሉ። «ሆኖም በእዚህ የውድድር ዘመን ከባድ ጨዋታዎችን በጥሩ ሁናቴ አከናውነናል። እናም እነሱ» ማንቸስተር ሲቲዎችን ማለታቸው ነው « የፕሬሚየር ሊጉ እና የሻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫ በእጃቸው ለማድረግ ከፍተኛ ገንዘብ አፍስሰዋል። ስለእዚህ በሚቀጥለው እሁድ የግድ ውጤት ለማስመዝገብ መጠበቃቸው አይቀርም። እኛ ግን፤ ወደ ሜዳ የምንሄደው ለመዝናናት ነው።» ሲሉ ቡድናቸው ከተቀናቃኛቸው የበለጠ የማሸነፍ ዕድል እንዳለው ገልፀዋል። ማንቸስተር ሲቲ ከትናንት በስትያ ሣውዝሐምፕተንን 4 ለ1 ድል አድርጓል።

ትናንት አርሰናል በኤቨርተን 3 ለ ባዶ በሆነ ከባድ ሽንፈት ተቀጥቷል። እናም በደረጃ ሠንጠረዡ ከመሪው ሊቨርፑል በ10 ነጥቦች ርቆ ዋንጫ የመጨበጥ ዕድሉን ሲበዛ አጥብቧል። ቀጣዮቹን አምስት ጨዋታዎች በአጠቃላይ ቢያሸንፍ እንኳ በአሁኑ ወቅት ሊቨርፑል ከሰበሰበው ነጥብ ሊበልጥ የሚችለው በ5 ብቻ ይሆናል።

ማንቸስተር ዩናይትድ ከትናንት በስትያ ኒውካስልን 4 ለባዶ ቢያንኮታኩትም ከሊቨርፑል በ17 ነጥቦች ዝቅ ብሎ በ6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ኤቨርተን አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ከአርሰናል በ1 ነጥብ ዝቅ ብሎ 63 ነጥቦችን ሰብስቧል።

እናም ከእንግዲህ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የዋንጫ ፍልሚያው የሚያጠነጥነው በሊቨርፑል፣ ቸልሲ እና በዋናነት ማንቸስተር ሲቲ መካከል ይሆናል ማለት ነው።

ከነገ በስትያ በሻምፒዮንስ ሊግ ማንቸስተር ዩናይትድን በሜዳው የሚገጥመው ባየርን ሙንሽን በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ግስጋሴው ለ53 ተከታታይ ጨዋታዎች ሳይሸነፍ ከትናንት በስትያ ለመጀመሪያ ጊዜ በአውስቡርግ 1 ለባዶ ተቀጥቷል። ሆኖም ባየርን ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ከነገ በስትያ ምሽት ለአምስት ሩብ ጉዳይ ላይ ለሚያደርገው የሻምፒዮንስ ሊግ ወሳኝ ፍልሚያ ምርጥ ምርጥ ተጫዋቾቹን ባለማሰለፉ ትችት ቀርቦበታል።

ሊቨርፑል ዘንድሮ ዋንጫውን ወደ ወደቧ ታመጣ ይሆን?

ሊቨርፑል ዘንድሮ ዋንጫውን ወደ ወደቧ ታመጣ ይሆን?

ስፔናዊው የቡድኑ አሰልጣኝ ፔፔ ጉዋርዲዮላ ትኩረታቸው ማንቸስተር ዩናይትድ ላይ መሆኑን በመግለፅ ትችቱን አጣጥለዋል። «በቡንደንደስ ሊጋው የነበረን የቤት ስራ እኮ ተጠናቋል። አክትሞለታል። አሸናፊነታችንን ሙዚየም ውስጥ አስቀምጠነዋል» ሲሉ ውድድሩ ሳይጠናቀቅ በፊት የዋንጫ ባለቤት መሆናቸውን አስታውሰዋል።

በሻምፒዮንስ ሊግ ነገ ማታ የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከስፔኑ ኃያል ሪያል ማድሪድ ጋር ሲገጥም፤ የእንግሊዙ ቸልሲ ከፈረንሣዩ ፓሪስ ሳንዠርማን ጋር ይገናኛል። ከነገ በስትያ ምሽት ለአምስት ሩብ ጉዳይ ላይ የስፔኖቹ አትሌቲኮ ማድሪድ እና ባርሴሎና ይፋለማሉ። የሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች በአጠቃላይ የሚከናወኑት በተመሳሳይ ሠዓት ነው።

በባህሬኑ የፎርሙላ አንድ የመኪናሽቅድምድም የታላቋ ብሪታንያ ተወላጅ ሌዊስ ሐሚልተን በመርሴዲስ መኪናው አሸናፊ ሆኗል። ጀርመናዊው ሌላኛው የመርሴዲስ መኪና አሽከርካሪ ኒኮ ሮዘንበርግ ሁለተኛ ወጥቷል። የዓለም ባለድሉ ጀርመናዊው የሬድ ቡል አሽከርካሪው ሠባስቲያን ፌትል በ6ኛነት አጠናቋል።

ጀርመናዊው የፎርሙላ አንድ የሰባት ጊዜያት ባለድሉ ሚካኤል ሹማኸር በደረሰበት አደጋ ለሦስት ወራት ግድም እራሱን ከሳተ በኋላ መጠነኛ መሻሻል እንደታየበት ተገለፀ። ሹማኸር ታኅሣሥ 20 ቀን 2006 ዓም ነበር ፈረንሣይ ውስጥ በረዶ ላይ እየተንሸራተተ ሲዝናና በጭንቅላቱ ከድንጋይ ጋር የመጋጨት አደጋ የደረሰበት። ከእዛን ጊዜ አንስቶ ሹማኸር ራሱን ስቶ ቆይቶ ነበር። አሁን ከገባበት ሠመመን በመጠኑ የመንቃት ሁናቴ እያሳየ እንደሆነ በወኪሉ ይፋ ሆኗል።

የሊቨርፑሉ ግብ አዳኝ ሉዊስ ሱዋሬዝን ለመውሰድ ማንቸስተር ሲቲ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑ ተዘግቧል። ሆኖም ሉዊስ ሱዋሬዝ ሊቨርፑል ውስጥ እንደሚቆይ የሊቨርፑሉ ስራ አስኪያጅ ኢያን አይሬ እርግጠኛ እንደሆኑ ተናግረዋል።

የቸልሲው አሠልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆ

የቸልሲው አሠልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆ

የቤልጂየም ተወላጁ የቸልሲው አማካኝ ኤደን ሐዛርድ ወደ ፈረንሣዩ የእግር ኳስ ቡድን ፓሪስ ሳንዤርማን መዘዋወር አለመዘዋወሩን ባለቤቱ እንድምትወስንለት አስታወቀ።

የቸልሲ አሰልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆ በበኩላቸው የአትሌቲኮ ማድሪዱ አጥቂ ዲዬጎ ኮስታን በ35 ሚሊዮን ፓውንድ ማስመጣት እንደሚፈልጉ መናራቸውን ሠንደይ ኤክስፕሬስ የተባለው ጋዜጣ ዛሬ አስነብቧል።

ባርሴሎና ላይ የተጫዋች ዝውውር ማዕቀብ መጣሉን ተከትሎ ማንቸስተር ይናይትድ በጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ የቦሩስያ ዶርትሙንዱ አማካይ ኢልካይ ገንዶጋንን በእጁ እንደሚያስገባ እርግጠኛ ሆኖ ተናገረ።

ማንቸስተር ሲቲ የ23 ዓመቱ ተከላካይ ኤሊኩዌም ማንጋላን እና የ26 ዓመቱ የመሀል ተከላካይ ፈርናንዶን ከፖርቶ በ41 ሚሊዮን ሊያስመጣ ነው። በአንፃሩ የመሀል ተከላካይ የ31 ዓመቱ ጆሌኖ ሌስኮት እና የ33 ዓመቱ ማርቲን ዴሚቼሊስ ቡድኑን እንደሚለቁ ተዘግቧል።

የሪያል ማድሪዱ የ26 ዓመቱ የግራ ተመላላሽ ፋቢዮ ኮዌንታሮን በእጅ ለማስገባት ሊቨርፑል፣ ማንቸስተር ሲቲ እና ሞናኮ ተናንቀዋል። ሊቨርፑል የሚያሸንፋቸው ይመስላል ሲል ሠንደይ ፒፕል አትቷል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic