የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት
ዓርብ፣ ጥቅምት 1 2017በዛሬው የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርካታ አስተያየት ሰጪዎች የተሳተፉባቸውን 3 ርእሰ ጉዳዮች ላይ እናተኩራለን። የቀድሞው ፕረዚደንትሳሕለወርቅ ዘውዴ ከስልጣን መውረድና በአምባሳደር ታዬ አፅቀ ስላሴ መተካት፣ በአማራ ክልል በዘንድሮው የትምህርት ዘመን 7 ሚልዮን ተማሪዎችን ለመቀበል ተልሞ ከ2 ሚልዮን የማይበልጡ ተማሪዎች መቀበሉንና የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር የምርጫ ቦርድ ሕገወጥ ጉባኤ ያለውና ብዙ የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትና የቁጥጥር ኮሚሽን ያልተሳተፉበት ጉባኤ አካሄድኩ ያለው የህወሓት ቡድን መፈንቅለ መንግስት ሊያካሄድብኝ እያሴረ ነው ስለማለቱ የሚሉ ናቸው በዚሁ ቅደም ተከተል ይቀርባሉ። ጸጋዬ የተባሉ አስተያየት ሰጪ
"የሀገችን ህገመንግት መሬት ላይ የሚወርድ ቢሆን ፕሬዜዳንቶች 30% የገሪቱዋን ችግር ይቀርፉ ነበረ። ነገርግን አንዳንዶቹ ቀይመስመር እያሰመሩ ሲሄዱ ሲሂዱ ግዜያቸው ሊልቅ መሆኑን ሲያውቁ ታፍኜ ነበር የሚልድራማ ይሰራሉ።" የሚል አስተያየት በፌስቡክ ገጻችን አስፍሯል። ውቢቷ ወሎ ደግሞ "ሳሀለወርቅ ለኢትዮጵያ ወሳኝ ነበሩ፤ ግን ጥሩ ሰው እኛጋ አይቆይም " የሚል አጭር አስተያየት አስቀምጧል።
ሐብታሙ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ለአዲሱ ፕረዚደንትመልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል።
"መልካም የሥራ ዘመን እንድሆንላቸው እየተመኘሁ ለሀገር ሉዓላዊነትና አንድነት ተጽዕኖ ፈጣሪ በመሆን በቅንነትና በታማኝነት እንደሚሠሩ ተስፋ አደርጋለሁ ።"
"ለአንድ አመት ዝምታ የመረጡበት ዋናው ምክንያት ምንድን ነው? ያልተመቻቸው አካሄድ ምንድን ነው?" የሚሉ ጥያቄዎች ያሰፈሩት ደግሞ አሰፋ ደምሴ ናቸው።
"መንግስት የበርካታ ዓመታት የዲፕሎማሲ ልምድና አገልግሎት ያላቸውን አዲሱን ፕረዚደንት፣ ከዲፕሎማሲው መድረክ እይታና ከነበሩበት ሀላፊነት አግልሎአቸዋል። በተመሳሳይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ አምባሳደር መለስ ዓለም፣ አምባሳደር ሣህለ-ወርቅ ዘውዴ፣ አምባሳደር ስለሺ በቀለን የመሳሰሉ ባለሙያዎችን በማይገባቸው ቦታ በመሰየም፣ ከአገልግሎት ውጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
ምክንያቱም በየትኛውም የሥራ መስክና መንግስታዊ ኃላፊነቶች ላይ ሆነው በሥራቸው ግርዶሽ ሊሆኑ ይችላሉ የሚላቸውን ግለሰቦች በማይሆን ቦታ ያስቀምጣቸዋል። ነገሩ ይቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም ነው።" የሚል መልእክት የጻፉት ደግሞ ሎጎዳ ሃምባ በሚል መጠሪያ የሚጠሩ አስተያየት ሰጪ ናቸው።
ካሳሁን ስንቅነህ "አምባሳደር ታዬ በሰሜኑ የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅትና በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የአለም አቀፉ ጫና በኢትዮጵያ ላይ ባየለበት ወቅት ብቃታቸውን ያስመሰከሩ ብልህ ዲፕሎማት ነበሩ። አምባሳደሩ ብዙ ሊሰሩበት ከሚችሉበት የውጭ ገዳይ መስሪያ ቤት አንስቶ አስተዋጽአቸው በጣም ውስን ወደሆነበት የፕሬዜደንትነት ቤተ መንግስት ማስገባት እኔ በበኩሌ አልተመቸኝም። ማን ደሞ በእሳቸው ቦታ እንደሚሾም የምናየው ይሆናል።" ብለዋል።
ሰላም ተሰማም እንደ ካሳሁን ሁሉ ሹመቱ የተመቻቸው አይመስልም፤ተመሳሳይ ሐሳብ ሰንዝረዋል።"ደህና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሆነው አየሰሩ ከነበሩበት ወደ እንግዳ ተቀባይነት እና የጦር ጄኔራሎች መሾም እና መሸለም? ይሉና 6 ጥያቄ ምልክቶች አስቀምጠው ይቀጥላሉ፤ በእውነት ትክክል አይደለም" በማለት ሃሳባቸውን ቋጭቷል።
እንድሪስ መኮንን "የዚህ ሹመት አሰጣጥ ትክክል ነው ብየ አላምንም። ምክንያቱም አምባሳደሩ የውጭ ጉዳዩን ቢሰሩ የተሻለ የሀገርን ጥቅም ያስከብራሉ ባይ ነኝ። ኘረዘዳንት ላይ ማስቀመጥ የሰውየውን እውቀት እንደመደበቅ ይቆጠራል"
አያ ማሩ ግን ቀደም ሲል ከተደመጡ አስተያየቶች ለየት ያለ ሐሳብ አስቀምጠዋል
"ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ስላሴ እንኳን ለታላቅ ማዕረግ አበቃዎት። ምንም ጊዜው የከፋ፣ ሴሬኞች እንደ አሽን የፈሉበት ኢትዮጵያዊነት፣ አንድነት የማይፈለግበት ውስጠ ወይራ የሆነ ዘመን ቢሆንም ይሄ ሁሉ ያልፋል። ልክ እንደአባቶቻችን ኢትዮጵያዊነት ይቀጥላል እውነት ያሽንፋል የኢትዮጵያ ዓምላክም ተንኮልን እያጠፋ እውነትን ያነግሳል። እግዚአብሔር ከእርስዎ ጋር ይሁን።"
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በቅርቡ እንዳስታወቀው በ2017 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን 7 ሚሊዮን ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለማስገባት አቅዶ የነበረ የተመዘገቡት ግን ከ2 ሚሊዮን አይበልጡም። በጦርነቱ ሳቢያ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸው ከሚያሳድረው የሥነ-ልቡና ጫና ባሻገር ትውልድ ተሻጋሪ ቀውስ እንዳያስከትል አስግቷል። የመማር ተስፋን ያጨለመውትውልድ ተሻጋሪ ቀውስ፤ እንዴት ይታከም? በሚል ርእስ ዶይቼቨለ በፌስቡክ ገጹ አወያይቶ ነበር። በዚህ ከሰፈሩ ሐሳቦች ካለን ጊዜ አንጻር የተወሰኑትን እናቀርባለን።
በዚህ አልስማማም በሚል ሐሳባቸውን የጀመሩት ጌታቸው ፋንታሁን የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው።
"በዚህ ሃሳብ አልስማማም፤ ምክንያቱም አገሪቱ ለትምህርትና የተማረ ሰው የሠጠችው ተስፋ ባዶ ስለሆነ። ባለመማር የሚቀር ነገር የለም። መማሩ ማንበብና መጻፍ ለመቻል፣ ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጅዎችን ለመጠቀም ይሆናል። ይህንን ደግሞ ይደርሱበታል። ዛሬ ዛሬ መማር ራስን የመቻል፣ ሌሎችን የማገዝ፣ በልቶ የማደር ተስፋ መሆኑ ቀርቶ የድህነት፣ የርሃብና የውርደት መገለጫ ሆኗል። ዛሬ ላይ 12ኛ ክፍል ጥሩ ውጤት አምጥቶ ዩኒቨርስቲ በማዕረግ ከተመረቀው 10ኛ ክፍል ያቋረጠው የተሻለ ኑሮ ይኖራል። አገሪቱ ለትምህርትና ለተማረ ሰው የሰጠችው ቦታ ነገ ከነገ በኋላ ዋጋ የሚያስከፍላት ቢሆንም ዛሬ ላይ የተማሩትን በችግርና በርሃብ እያስገረፈች ነው። ማደግ፣ መለወጥ፣ መዘመን ወዘተ ከትምህርት ውጭ አይታሰቡም። አገሪቱ ግን እነዚህ እንዳይመጡ ተግታ እየሰራች ነው። እናም ባይማሩም የሚቀርባቸው የለም።" ብለዋል። አዚዝ መሐመድ ደግሞ "ሰላም ሲኖር እኮነው ትምህርት መማር ሚቻለው። ከአመት አመት ጦርነት ሆኖ እንዴት ይማሩ?" የሚል ጥያቄ አዘል አስተያየታቸውን አስፍሯል።
ኤደን ነጋ ደግሞ "የድሮን ቦምብ ትምህርትቤት ላይ እየተጣለ ማን ይማራል? ማንስ ያስተምራል? ማንስ ልጁን ትምርህት ቤት ይልካል?" በማለት ይጠይቃሉ። ወደ ሌላ አስተያየት አለፍን።
"የተማሪን መጽሓፍ ድሃው ሕብረተሰብ ይግዛ፤ መንግስት የጦር መሳሪያ እንጂ መጽሃፍ የማሳተም ግዴታ የለበትም ተብሏል። ጦርነት በሌለባቸው አከባቢዎችም ቢሆን ተማሪው መጽሓፍ የለውም፤ መምህራን ደመወዝ በአግባቡ ስለማይከፈላቸው በተገቢው አይሰሩም። ካድሬ ግን አበል ለመቃረም እየተሰበሰበ የትምህርት ስብራት ምናምን እያለ ይደሰኩራል። ፋኖና ሸኔ ደግሞ ጭራሽ ገደል ከተቱት።" የሚል አስተያየት የጻፉት ታደሰ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው።
ኑር አሕመድ ደግሞ "እየተማሩ ያሉ ተማሪወች ያለበቂ መጽሀፍ ነው፤ 4 መፀሀፍ ለ3 ተማሪ። ይህን ለመቅረፍ እንኳን ተነሳሽነት ለምን እንደተሳነው ይገርማል" ብሏል።
"የመጀመሪያው በአማራ ሕዝብ ስም ተመርጠው በሕዝብ ተወካዮች፣ በፌደሬሽን ምክርቤት የሚገኙ ሹማምንት፣ በተለያዩ የፌዴራል ሚኒስቴር መ/ቤቶች እና በልዩ ልዩ የመንግስት ተቋማት ውስጥ በኃለፊነት የሚገኙ ግለሰቦች፣ ከተቸራቸው የሹመት ወንበር ባሻገር የሕዝባቸውንና የአገራቸውን ሠላምና አንድነት ከማስከበር ይልቅ፣ የግል ጥቅማቸውን ብቻ በሚያስጠብቅ መንገድ መጓዛቸው ነው።
ሁለተኛው ነጥብ የክልሉ ተመራጮች ለመረጣቸው ማህበረሰብ የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት በለመቻላቸው በአማራ ሕዝብ ላይ ጦርነት እያሳወጁ፣ አዋጅ እያስደነገጉ፣ ሕዝባቸውን በሰው አልባ አውሮፕላንና በሌሎች የጦርመሣሪያ እንዲወድም ለአገዛዙ መንግስት አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆናቸው ነው።
በመሆኑም የክልሉ ወኪሎች የሚተዳደሩበትን ሕገ-መንግስት ተመርኩዘው፣ መንግስትን በመሞገት ለሕዝብ ደጀንነታቸውንና አንድነታቸውን በማሳየት፣ የተጣለባቸውን ግዴታ ሊወጡ ይገባል።"
በምርጫ ቦርድ ሕገወጥ የተባለውን ጉባኤ ያካሄደው የህወሓትክፋይ መፈንቅለ ስልጣን አደረገብኝ ሲል የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ገልጾ ነበር።
በዶክተር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው ህወሓት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 13 የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ባለስልጣናትን ከስልጣናቸው እንዲወርዱ መወሰኑን ካሳወቀ በኋላ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር፣ የህወሓቱ ቡድን በግልፅ "መፈንቅለ ስልጣን እንዲደረግብኝ አውጇል" ሲል ባሰራጨው መግለጫ አስታውቋል። ይህም "ስርዓተ አልበኝነት እንዲሰፍን ፍላጎት እንዳለው ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው ሲል በመግለጫው አመልክቷል። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በዚህ «የጥፋት ኃይል» ባለው ቡድን ላይ ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ እንደሚጀምር ፤በዚህ ሰበብም ለሚፈጠር ማንኛውም ጥፋትም ተጠያቂዎቹ ቡድኑ እና አመራሩ ይሆናሉ ብሏል። ይህን ዜና ተከትሎ በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርካታ ሐሳቦች ተንሸራሽረዋል። የተወሰኑትን እንመልከት
"እንደ ሀገር ያሉ ቀውሶች ያሳስባሉ ።ነገር ግን ልዩነቶች በውይይት መፈታት አለባቸው። የተጠያቂነት ኩነቶች ሲኖሩ ወደ ሀይል መገባቱ አይቀርም። ህዝብ ግን በገለልተኝነት ከቆመ ልዩነቶች እጅ ይሰጣሉ።" አብዱራህማን ማህመድ ናቸው ይህን ሐሳብ ያሰፈሩት።
ወዲ ፍትዊ ደግሞ "ፍጥጫው የስልጣን እንጂ ምንም የሚፈጠር ነገር የለም። ክልሉ ሰላም ነው። በቅርቡ እልባት ያገኛል።" ብሏል።
ማንዴላ ሪል ሄሮ በሚል መጠሪያ የሚጠሩት አስተያየት ሰጪ፤ "ሁለቱም መሪዎች ማፈርያዎች ናቸው። የህዝብን ስቃይ ወደ ጎን ብለው ለወንበር የሚራኮቱ ጥቅሞኞች! ያ ደግ፣ ሰው አክባሪ ማህበረሰብ ይህ አይገባውም ነበር፤ ያሳዝናል። ሰላም ለዛ ደግ ህዝብ ሰላም ያምጣለት።" የሚል ሐሳብ ሰንዝሯል።
በረከት ብርሃኑ ደግሞ "በፕሪቶርያው ስምምነት መሰረት በክልሉ የተካሄደው ምርጫ ውድቅ ተደርጎ ምርጫ እስኪካሄድ ክልሉ በፌዴራል መንግስቱ ቅቡልነት ባለው ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚመራ ያስቀምጣል። የአመራር ምደባም ሆነ ሹም ሽር የሚያደርገው በፌዴራሉ መንግስት ቅቡልነት ባለው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ብቻና ብቻ ነው። ምርጫ እስኪካሄድ በክልሉ ህውሃት ፓርቲ ብቻ ነው። ሌላው በደብረፂየን የሚመራው ህውሀት የኦዲትና ኢንስፔክሽን ሙሉ አባላትና 14 ዋና አመራሮቹ በሌሉበት የተካሄደው ድርጅታዊ ጉባኤ በምርጫ ቦርድ ውድቅ መደረጉን ሰምተናል። የዚህን ትርጉም ሁላችንም የምናውቀው ይመስለኛል። ታድያ በየትኛው መሰረት ላይ ተሁኖ ነው ፕረዚደንቱንና ሌሎች አነሳለው የሚለው ምኞትየመጣው? ሆኖም የትግራዋይ ህዝብ ሰላም ያስፈልገዋል፣ ይገባዋልም። የጦርነትና ነውጥ መጨረሻው ሁሉም የሚያውቀው ነው። ያው ከ ዜሮ መነሳት እንዳይሆን"
ጃራ ቦሩ ደግሞ የስልጣን ጥማት ክፉ ነው በማለት ሐሳባቸውን ይጀምራሉ፤ "የስልጣን ጥማት ክፉ ነው። ከዚያ ሁሉ እልቂት እና መስዋዕትነት በኋላ ተስማምተው የህዝቡን ቁስል እንደማከም እና ማጽናናት ሁለቱም ቡድን ለስልጣን ጥማት መልሰው ይህንኑ ህዝብ ወዳልተገባ ሁኔታ ይመራሉ። ተያይዘውና አብረው ቆመው ለዚህ ህዝብ የወደቁ ነብሳት ቀና ብለው ይህንን ቢያዩ ምን ይሉ ይሆን? ያሳዝናሉ።"
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ኂሩት መለሰ