የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 27.08.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ምስራቅ ወለጋ ኪራሙ ወረዳ «የሸኔ ታጣቂ» የተባሉ ከ200 በላይ የአማራ ተወላጆችን  ገደሉ፣40 ሺሕ ግድም አፈናቀሉ ሥለመባሉና የኦሮሚያ መስተዳድር መልስን ባጠናቀርንበት ዘገባችን ላይ የተሰጠዉ አስተያየት በጣም ብዙ ነዉ።አስተያየቱ ያዉ እንደተለመደዉ በስድብ፣ቅጥፈት፣ከዘገባዉ በራቀ ስሜት «ያደፈ» ነዉ።ጥቂቱን እናሰማችሁ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:40

የኑሮ ዉድነት፣የምሥራቅ ወለጋ ግድያ፣ የአሜሪካ ማዕቀብ

ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።በዛሬዉ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ሳምንቱን በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከተዘገቡ ጉዳዮች የብዙዎችን አስተያየት የሳቡ ሶስት ርዕሶችን መርጠናል።የኑሮ ዉድነት፣ ምሥራቅ ወለጋ ዉስጥ ሰላማዊ ሰዎች ተገደሉ መባሉና ዩናይትድ ስቴትስ በኤርትራ ጄኔራል ላይ የጣለችዉ ማዕቀብ ናቸዉ።በዚሁ ቅደም ተከተል ይቀርባሉ።አስተያየት ሰጪዎቹን በሙሉ  በአንቱታ ነዉ የጠራነዉ።

ኢትዮጵያ ዉስጥ የምግብ ሸቀጥ፣የቤት ኪራይና የትራንስፖርት አገልጎሎት ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣቱ፣የብር የምንዛሪ አቅም ደግሞ ሲበዛ ማሽቆልቆሉ በተደጋጋሚ ተዘግቧል።የዋጋ ንረቱ፣ በተለይ አነስተኛ ገቢ ባለዉ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ችግር ማሳደሩንም ባለሙያዎች በየጊዜዉ አስታዉቀዋል።በያዝነዉ ሳምንት ከባሕርዳር የደረሰን ዘገባ እንደሚያመለክተዉ አምና 3500 ብር ይሸጥ የነበረዉ አንድ ኩንታል ጤፍ ዘንድሮ 5300 ደርሷል።12 ብር የነበረ ሳሙና ወደ 28 ብር አሻቅቧል።

ሑሴን ዓሊ በፌስ ቡክ ባሰፈሩት አስተያየት ለዋጋ ንረቱ የመንግስት ባለስልጣናትን ተጠያቂ ያደርጋሉ።

«ተቋሙን ከላይኛዉ እስከ ታችኛዉ መዋቅር ድረስ የሚመሩት ተሿሚዎችና ባለሙያዎች አላግባብ የዋጋ ጭማሬ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እንወስዳለን ብለዉ በሚዲያ ያወራሉ እንጅ አንጀታቸዉ እንደማይጨክን ካሁን በፊት ከተነገረዉ ተመሣሣይ ፉከራ የተለዬ እንደማይሆን ህዝብ ጠንቅቆ ያዉቃል፡፡»

ፋሕሚ ጋልሞ ግን ለዋጋዉ ንረት ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚደረገዉን ጦርነትና ግጭት «የቆሰቆሱ» ያሏቸዉን ወገኖች ይወቅሳል።«ጥይትና እንጀራ ፣ ፉከራና ሽብሸባ ፣ ጦርነትና ልማት አብረው የማይሄዱ ነገሮች ናቸው!!» ይላሉ-ፋሕሚ በፌስ ቡክ።ቃል አጋኖም ጨምረዉበታል።«ምን ለማለት ነው»፣ ቀጠሉ፣«ያልዘራችሁትን አታጭዱም ግፋ በለው ብላችሁ የጦርነት ነጋሪት ጎሽማችሁ----» ይሉና በርግማን ያሳርጋሉ «ጎፍታ ሜጫ የስራችሁን ይስጣችሁ።» ብለዉ

ብሌን አስፋዉ

በፌስ ቡክ፣ «ጊዜው ያመጣብን ነው። ጊዜ ይመልሰው።» ብለዉ እርፍ።ኤሏን እስማኤል ደግሞ «ያባይን ልጅ ዉኃ ጠማዉ»ን ተርተዋል።የጤፍ ሐገር በሚባለዉ ጎጃም አንድ ኩንታል ጤፍ 5300 ብር ማዉጣቱን ነዉ-መሰል።

ማክስሚላያን ታፓር-፣በፌስ ቡክ።«ከወሬ በዘለለ መሬት ላይ የወረደ ተግባር መንግስት ሊሰራ ይገባል---» ይላሉ።

ወደ ሌለኛዉ ርዕሥ ዕንለፍ።ምስራቅ ወለጋ ኪራሙ ወረዳ «የሸኔ ታጣቂ» የተባሉ ከ200 በላይ የአማራ ተወላጆችን  ገደሉ፣40 ሺሕ ግድም አፈናቀሉ ሥለመባሉና የኦሮሚያ መስተዳድር መልስን ባጠናቀርንበት ዘገባችን ላይ የተሰጠዉ አስተያየት በጣም ብዙ ነዉ።አስተያየቱ ያዉ እንደተለመደዉ በስድብ፣ቅጥፈት፣ከዘገባዉ በራቀ ስሜት «ያደፈ» ነዉ።ጥቂቱን እናሰማችሁ።

መንገሻ ፈንታዉ፣ በፌስ ቡክ በእንግሊዝኛ ያሰፈሩት አስተያየት በጥያቄ ይጀምራል «አሜሪካ፣ አምንስቲ ኢንተርናሽናል፣ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት የታሉ?» ይላል ጥያቄዉ።እራሳቸዉ መለሱ፣ «ለዓማራ ሕዝብ ድምፅ የሚሆን ማንም የለም?»

አያንቱ በዳዳ፣በፌስ ቡክ « ይሄ ሸኔ ኦሮሞን አይወክልም!!!» ይላሉ በቃለ-አጋኖ  ባሳረገ ዓረፍተ ነገር።ቀጠሉ « ይሄ የወያኔ እጅ ስራ፣ የሆነ ቆሻሻ ቡድን፣ ከአማራ በላይ ኦሮሞን ነው ያዋረደው።» እያሉ-አያንቱ ናቸዉ።

ሌንጮ ጃል፣-ለዶቸ ቬለ በእንግሊዝኛ በፃፉት ኢሜየል ዶቸ ቬለ በቲዊተር ያሰራጨዉን ዘገባ ያስተካክል ይላሉ።ሌንጮ እንደሚሉት፣ «ሸኔ» ማለት የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ጦር (ኦነጦ) ነዉ።ዶቸ ቬለ «ኦነጦ የዋሕ አማሮችን ገደለ» ብሎ ዘግቧል ባይናቸዉ።«ይሕ ኦነጦ በተደጋጋሚ ያስተባበለዉ፣ ምርመራ እንዲደረግ የጠየቀበት ጉዳይም ስለሆነ ዜናዉ «ዉሸት ነዉ።» ብለዉት አረፉ ሰዉዬዉ።

ሌንጮ የዶቸ ቬለን ዜና በቅጡ አላነበቡትም ወይም አዉቀዉ አጣመዉታል።ምክንያት አንድ፤ ዶቸ ቬለ  ዶቸ ቬለ፣ ሸኔ ማለት የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ጦር ነዉ አላለም።ምክንያት ሁለት፣-«ሸኔ»  ገደለ አላለም።ያለዉ የሸኔ ታጣቂዎች የተባሉ ነዉ።«የተባለ» እና «ነዉ» ሁለት የተለያዩ ነገሮች መሆናቸዉን ሌንጮ ቢገባቸዉ ጥሩ ነበር።ምክንያት ሶስት፣-ዘገበዉ የዓይን ምስክሮችን፣ከግድያዉ ያመለጡና ሟቾችን ቀበርን ያሉ ሰዎችን አስተያየት መሰረት አድርጎ፣ ኃላ ላይ ደግሞ የኦሮሚያ መስተዳድር ባለስልጣንን  አስተያየት አካትቶ የተዘገበ ነዉ። ሌንጮ ለምን ካዱት።ምክንያት አራት፣ የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ጦር ዜናዉን ደጋግሞ የሚያስተባብለዉ ዜናዉ ከመሰራጨቱ በፊት ይሆን?

በነገራችን ላይ አቶ ሌንጮ እርስዎ የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ጦርን የሚወክሉ ከሆነ፣ በቀጥታ ማስተባበያ መስጠት ይችላሉ።ሁለት ነገሮችን ብቻ ያሟሉ-ኃላፊነትዎትን የሚገልፅ መረጃና ሙሉ አድራሻዎትን።ለትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃ አሁንም ዶቸ ቬለን ይከታተሉ ግን በትክክል።

ሊሙ ጂንቶ በትዊተር፣ በጥያቄ የተሸፈነ አስተያየት ሰጥተዋል።«ለመሆኑ ሸኔ ማነው?» የመጀመሪያዉ ጥያቄ ነዉ። «የሆነው ሆኖ ዜናው ግን የአንድ ወገን ወሬ ላለመሆኑ፣ ወይም ተገደሉ የተባሉትን ማንነትና ሚና ለማጣራት ጥረት አድርጋችኋል?» ሁለት።«የአማራ ክልል ሠርጎ ገብ አለመሆናቸውን ምን ማረጋገጫ አላችሁ?» ሶስት።

ዶክተር ጣሰዉ በቲዊተር ገፅ፣ በእንግሊዝኛ በፃፉት መልዕክት፣ ብዙ የኦሮሞ ቡድናት ይሕንን (የዶቸ ቬለን) መረጃ ለመካድ ይሞክራሉ።እኛ መረጃ አለን።የክልሉ መንግስትም ጭፍጨፋዉን በድብቅ ይደግፋል።» ይሉና ይጠይቃሉ «የኦሮሞ አክቲቪስቶች እዉነታዉን ለመካድ የሚሞክሩት ለምንድነዉ? አማራን መግደል ለኦሮሞ ጥሩ ኑሮ ያመጣል ብላችሁ ታስባላችሁ?» የዶክተር ጣሰዉ ጥያቄ ነዉ።

መስፍን ደርቤ፣ በፌስ ቡክ «ዘር ማፅዳቱ እደቀጠለ ነው። ከሚያስገድሉዋቸው በሰላም ቢያሰናብቱዋቸው ይሻላል። እባካችሁ ሰውን ባትፈሩ የፈጠራቺሁን ፍሩ።» በማለት ይማፀናሉ።

መሠረት ንጉሴ በትዊተር ባሰፈሩት ፅሁፍ፣ «ሸኔ የሚባል ቡድን የለም።እነሽመልስ የሚመሩት ኦነግ እንጂ።ሸኔ

የዳቦ ስም ነዉ----» እያሉ ቀጠሉ መሠረት-እንስት ናቸዉ።

አወል ኸይር፣ በፌስ ቡክ ኸይሩን ተመኙ።ፈጣሪን ተማፁም።«ከእንደዚሕ ዓይነቱ ፈተና አላሕ ይጠብቀን።የኢትዮጵያ ልጆች ማሰብ አቃተን እንዴ? ጥለነዉ ለምንሔደዉ ዓለም።»

ሶስተኛዉ ርዕሥ ዩናይትድ ስቴትስ ባለፈዉ ሰኞ በኤርትራ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም በጄኔራል ፊሊጶስ ወልደዮሐንስ ላይ የምጣኔ ሐብት ማዕቀብ መጣልዋን በቃኘዉ ዘገባ ላይ ያተኩራል።ዩናይትድ ስቴትስ ማዕቀቡን የጣለችዉ ጄኔራሉ የሚያዙት ጦር ትግራይ ዉስጥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ግፍ ዉሏል በሚል ነዉ።

ጎሊያድ ሽታይዲንገር፣ በፌስ ቡክ፣ ማዕቀቡ ኤርትራን አይጎዳም ዓይነት ይላሉ።የትግራይ ባለሃብቶች እንጂ ኤርትራውያን አሚሪካ ቤትም ንብረትም፣ ገንዘብም የላቸውም ፤ ክድሮም ካሜሪካ ጋር ችግር ስላለባቸው፡፡ የትግራይ ባለሃብቶች ግን በጣም ብዙ ገንዘብ እና ቤቶች፣ ፎቆች አሜሪካ እንዳላቸው ይታውቃል ፤ ይህ ለነሱ ማስጠንቀቅያ እንደሆነ በርግጠኝነት እናቃልን።» ይላሉ ጎሊያድ።

ሶል ሶል  «አሜሪካ ኤርትራ ላይ ማቀብ ለመጣል መሯሯጧ ምን ያህል የወረደች ሀገር እንደሆነች ነው የሚያሳየው።» ይላሉ በፌስቡክ።ገዛኸኝ ገብሬ ግን «ዋናው ሽማግሌ ካልተወገደ አካባቢው መታመሱ ይቀጥላል።» ባይ ነዉ።ቅኝታችን አበቃ።መልካም የሳምንት መጨረሻ።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic