የማልታ ፕሬዝዳንትነት እና የአውሮጳ ህብረት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 03.01.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የማልታ ፕሬዝዳንትነት እና የአውሮጳ ህብረት

የአውሮጳን 500 ሚሊዮን ዜጎች መምራት ለማልታ ብዙ አቅም እንደሚጠይቅና እና ፖለቲካዊ ተግዳሮቶቹም ቀላል እንደማይሆኑ ነው የሚገመተው ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:29
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:29 ደቂቃ

የማልታ ፕሬዝዳንትነት እና የአውሮጳ ህብረት

ማልታ  በዙር የሚደርሰውን የአውሮጳ ህብረት የመሪዎች ምክር ቤት ፕሬዝዳንትነት ከትናንት በስተያ እሁድ ተረክባለች ። የማልታ የፕሬዝዳንትነት ጊዜ እቅድ እና ተግዳሮቶቹ የዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው ።   ለዝግጅቱ ኂሩት መለሰ
ትንሽትዋ ደሴት ማልታ ካለፈው እሁድ አንስቶ ትልቅ ሃላፊነት ተሸክማለች ። ለሚቀጥሉት 6 ወራት የአውሮጳ ህብረት የመሪዎች ምክር ቤት የፕሬዝዳንትን ሥልጣን ከስሎቬንያ ተረክባለች ።ለ6 ወራት በሚዘልቀው በዚህ የሃላፊነት ጊዜም ማልታ አውሮጳን ያስጨነቀውን የስደተኞች ቀውስ ለመፍታት የሚያስችል እገዛ ለማድረግ አቅዳለች ።  ይህን እቅድዋን ለማሳካት ታዲያ የራስዋን ልምድ ትጠቀም ይሆን ሲል ይጠይቃል የዶቼቬለው ቤርንት ሪገርት ።
ሜዴትራንያን ባህር ላይ የምትገኘው ማልታ መልከዐ ምድራዊ አቀማመጧ እና የተዋቡት መንደሮቿ የዓለም ዓቀፉ የፊልም ኢንዱስትሪ  መስህብ ናቸው ። ።የማልታ ህዝብ ቁጥር 420 ሺህ ነው  ። ሀገሪቱ ከአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት በስፋትም ትንሽዋ ሀገር ናት ። በጎርጎሮሳዊው 1964 ከብሪታንያ ነጻነትዋን ያገኘችው ማልታ ጥሩ የአየር ንብረት ያላት እና እንግሊዘኛም ሁለተኛ የመነጋገሪያ ቋንቋዋ መሆኑ ለታዋቂ ፊልሞች መሥሪያነት ተመራጭ ሀገር አድርጓታል ። ምናልባት ፊልም አፍቃሪዎች በተከታተሉዋቸው ታዋቂ ፊልሞች ማልታን ማየታቸውን ልብ ላይሉ ይችሉ ይሆናል ይላል የዶቼቬለው ቤርንት ። ባለፈው እሁድ የአውሮጳ ህብረትን የግማሽ ዓመት የፕሬዝዳንትነትን ሥልጣን የተረከበችው የማልታ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆሴፍ ሙስካት የፕሬዝዳንትነቱን ጊዜ ሀገራቸውን ይበልጥ ለማስተዋወቅ ሊጠቀሙበት አስበዋል ። ሙስካት ማልታን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት ለሦስት ዓመታት ነው ። የ42 ዓመቱ የማልታ ሠራተኞች ፓርቲ ሊቀ መንበር

ሶሻል ዴሞክራቱ ሙስካት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ መመረጥ  ከማልታ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጋር የቅርብ ቁርኝት የነበረውን እና ለአሥርት ዓመታት ሀገሪቱን ሲያስተዳድር የቆየውን የብሔረተኛውን ወግ አጥባቂ ፓርቲ የዓመታት በላይነት አስቀርቷል ። ሶሻል ዴሞክራቶች አሁን እንደ ቀድሞው ማልታ የአውሮጳ ህብረት አባል መሆኗን መቃወማቸው አቁመዋል ። ሙስካትም በዚህ ተግባር ራሳቸውን  አርአያ አድርገው ያቀርባሉ ። ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስካት በሀገራቸው የፕሬዝዳንትነት ጊዜ ትኩረት ከሚሰጧቸው ጉዳዮች አንዱ የአውሮጳ የስደተኞች ቀውስ ነው ። በዚህ ረገድ ሀገሪቱ በሚቀጥሉት 6 ወራት ተግባራዊ ለማድረግ በአጀንዳነት የያዘቻቸው ጉዳዮች የትኛዎቹ እንደሆኑ የብራሰልሱ ዘጋቢያችን ገበያው ንጉሴ ያብራራልናል ። 
የማልታ እቅድ ይህ ቢሆንም ከአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት አብዛኛዎቹ  ስደተኞችን እና ተገን ጠያቂዎችን አናስገባም በሚለው አቋማቸው እንደጸኑ ነው ። በርካታ ስደተኞች የሚገቡባቸው የአውሮጳ ህብረት ደቡባዊ ድንበር የሆኑት ግሪክ ኢጣልያ እና ማልታ በየቀኑ በየባህር ዳርቻዎቻች ለሚገቡት ስደተኞች ማስተናገጃ እርዳታ እንዲሰጣቸው እና የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራትም ስደተኞች ን እንዲከፋፈሉ አሁንም ጥሪ ማቅረባቸው ቀጥሏል ። ሙስካት በ6 ወሩ ሃላፊነታቸው በስደተኞች ቀውስ ላይ አባል ሀገራት የያዙትን የተለያየ አቋም ቢያንስ ለማቀራረብ ቢቻል ደግሞ አንድ ለማድረግ አቅደዋል ። 
«በተቻለ መጠን ሁሉንም አቋሞች የማቀራረብ ፍላጎት ያለ ይመስለኛል ። በማልታ የፕሬዝዳንትነት ጊዜ ይህ ከባድ ሥራ ነው የሚሆነው ። እነዚህን አቋሞች ወደ አንድ ለማምጣት የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን ።»
ሙስካት ይህን ተስፋቸውን የገለጹት ታህሳስ አጋማሽ ላይ በተካሄደው በ2016 የመጨረሻው የአውሮጳ ህብረት ጉባኤ ላይ ነበር ። በየካቲት ወር  በክፍለ ዓለሙ አንገብጋቢ ጉዳይ ላይ ያተኮረ የመሪዎች ጉባኤ በርዕሰ ከተማ ቫሌታ ይካሄዳል ። ጉባኤው ከሚያተኩርባቸው ጉዳዮች ውስጥ የስደተኞች ቀውስ  አንዱ ነው ።  የሙስካት ምኞት ከአፍሪቃ በሜዴትራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮፓ የሚደረገው ስደት ታሪክ ሆኖ እንዲቀር ነው ።   
« አዲሱ ነገር በማዕከላዊ ሜዲቴራንያን የሚያልፈው የስደተኞች መሸጋገሪያ መስመር ጉዳይ ላይ ቁልፍ መፍትሄ ላይ መድረስ ያሻል ። በርግጥ ይህ አጠቃላይ ማዕቀፍ ነው ። ይህ አጠቃላይ ማዕቀፍ ደግሞ ህብረትን ደህንነትን እና የድንበር ቁጥጥርንም ማካተት አለበት ። በዛም ሆነ በዚህ እንደሚመስለኝ  ከቱርክ ጋር የደረስንበትን ዓይነት ውል በሜዴትራንያንም ተግባራዊ ልናደርገው ይገባል ።»
የአውሮጳ ህብረት የመሪዎች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የሚሆነው ሀገር ሃላፊነት የህብረቱን የመሪዎች ምክር ቤት ሥራ በአግባቡ  ማካሄድ ነው  ። ሃላፊነቶቹም የመሪዎቹን የምክር ቤት ስብሰባዎች መምራት የሚነጋገሩባቸውን አጀንዳዎች ማዘጋጀት ፣ የስራ መርሃ ግብር ማውጣት እንዲሁም የመሪዎቹ ምክር ቤት እንዲሁም ምክር ቤቱ ከሌሎች የህብረቱ ተቋማት ጋር የሚያካሂዳቸውን ውይይቶች ማመቻቸትም ነው ።  ከሰሜን አፍሪቃዊቷ አገር ሊቢያ እስከ ኢጣልያ ባለው የስደተኞች የጉዞ መስመር ላይ የምትገኘው ማልታ በተሸኘው በ2016 ፣ 1700 ተገን ጠያቂዎችን ተቀብላለች ።ወደ ኋላ ተኬዶ ከ2012 አንስቶ ማልታ የገቡት ስደተኞች ቁጥር ከ20 ሺህ ይበልጣል ። ይሁን እና ከመካከላቸው ማልታ የቆዩት አንድ ሦስተኛው ብቻ ናቸው ። አብዛኛዎቹ

ከማልታ ወደ ኢጣልያ ተወስደዋል ። ማልታ ከዚህ ቀደሙ በስደተኞች አያያዝ የምትተች ሀገር ነበረች ። እስከ ጎርጎሮሳዊው 2016  ማልታ የሚገቡ  ስደተኞች መውጣት በማይችሉበት መጠለያ ውስጥ እንዲቆዩ ነበር የሚደረገው ።ሆኖም ከተደጋጋሚ ዓለም ዓቀፍ ወቀሳ በኋላ በአውሮፓ ህብረት እርዳታ ስደተኞች እንደልባቸው መውጣት እና መግባት የሚችሉባቸው መጠለያዎች ለመገንባት በቃታለች። ስደት ለማልታ እና ለማልታውያን አዲስ ነገር አይደለም ። በሜዴትራንያን ባህር ላይ የምትገኘው ስልታዊቷ ደሴት ማልታ ለብዙ ጊዜያት የተዋጊዎች እና የሰፋሪዎች መተላለፊያ ሀገር ሆና ቆይታለች ።  በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የማልታ ዜጎችም ሀገራቸውን ጥለው ወደ ተለያየ የዓለም ክፍል ተሰደዋል ።ማልታ በ6 ወሩ የአውሮጳ ህብረት ፕሬዝዳንትነት ጊዜዋ ሌሎች ከፍፃሜ ልታደርሳቸው ያቀደቻቸው ጉዳዮችም አሉ ።ገበያው 
ከስደተኞች ጉዳይ በተጨማሪ ማልታ በህብረቱ የመሪዎች ምክር ቤት ፕሬዝዳንትነት ጊዜዋ ከምትጠመድባቸው ጉዳዮች  አንዱ ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት አባልነት የምትወጣበት ሂደት ነው ። ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስካት ብሪታንያ ከህብረቱ ለመውጣት የምታካሂዳቸውን ድርድሮች የማዘጋጀት  ሀላፊነት ተጥሎባቸዋል ።ለቀድሞ የማልታ ቅኝ ገዥ ብሪታንያ ርህራሄ የሌላቸው ሙስካት ድርድሩ በጣም ከባድ እንደሚሆን ነበር በቅርቡ በሰጡት ቃለ ምልልስ የተናገሩት ። በርሳቸው አባባል የብሬክዚት ድርድር ልክ ከግሪክ ጋር በብድር እ እርዳታ አሰጣጥ ላይ ሲካሄድ እንደነበረው ድርድር ጠንካራ ነው የሚሆነው ።እናም የአውሮጳን 500 ሚሊዮን ዜጎች መምራት ለማልታ ብዙ አቅም የሚጠይቅና እና ፖለቲካዊ ተግዳሮቶቹም ቀላል እንደማይሆኑ ነው የሚገመተው ። እንደገና ገበያው  
በቀደመው እቅድ መሠረት የማልታ የሥልጣን ጊዜ ሲያበቃ ማልታን ተክታ የፕሬዝዳንትነቱን ሃላፊነት የምትረከበር ብሪታንያ ነበረች ። ብሪታንያ ባለፈው ዓመት ከህብረቱ አባልነት ለመውጣት በመወሰኗ  ከሐምሌ እስከ ታህሳስ ያለውን የፕሬዝዳንትነት ሥልጣን  ኤስቶንያ ትረከባለች ። ማልታ ሥልጣኑን ለኤስቶንያ ከማስተላልፈዋ በፊት የትኛዎቹ አጀንዳዎች እንደሚሰምሩላት የትኛዎቹ እንደሚከሽፉባት በመጪዎቹ 6 ወራት የምናየው ይሆናል ። 

ኂሩት  መለሰ

ነጋሽ መሐመድ
 

Audios and videos on the topic