የማሌዥያው አውሮፕላን አደጋ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 18.07.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የማሌዥያው አውሮፕላን አደጋ

ትናንት ከሰዓት በኋላ በዩክሬን አየር ክልል ላይ ሲበር የወደቀው የማሌዥያ አየር መንገድ የመንገደኞች አውሮፕላን በሚሳይል ሳይመታ አልቀረም መባሉ ማነጋገሩን ቀጥሏል ። የዩክሬን ባለሥልጣናት አደጋው እንደደረሰ በሰጡት መግለጫ አውሮፕላኑ አካባቢውን በተቆጣጠሩት በዩክሬን አማፅያን ከምድር ወደ ሰማይ በተተኮሰ ሚሳይል ነው የተመታው ሲሉ አስታውቀዋል ።

አማፅያኑ ግን ይህን አስተባብለው ጥቃቱ በዩክሬን መንግሥት ኃይሎች ነው የተፈጸመው ብለዋል ። አንዳንድ ወገኖች ደግሞ ለአደጋው ሩስያን ተጠያቂ እያደረጉ ነው ። በሌላ በኩል አውሮፕላኑ ፀጥታው አስተማማኝ ባልሆነ በዚህ የአየር ክልል እንዲበር መደረጉም ጥያቄዎች እያስነሳ ነው ። ንብረትነቱ የማሌዥያ አየር መንገድ የሆነው ቦይንግ 777 አውሮፕላን 298 መንገደኞችን አሳፍሮ ትናንት ከአምስተርዳም ኔዘርላንድስ ተነስቶ ዩክሬን የአየር ክልል እስኪደርስ ድረስ ጉዞው ሰላማዊ ፣ ከበረራ ተቆጣጣሪዎች ጋር የነበረው ግንኙነትም የሰመረ ነበር ። አውሮፕላኑ ዩክሬን የአየር ክልል ከገባ በኋላ ግን ይህ አልቀጠለም ። የዩክሬን ባለሥልጣናት አውሮፕላኑ ምሥራቅ ዩክሬን ሲደርስ ግንኙነቱ መቋረጡን አስታውቀዋል ። ብዙም ሳይቆይ የዩክሬን ብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ አንድሬ ሊሴንኮ አውሮፕላኑ ተመቶ ሳይወድቅ እንዳልቀረ ተናገሩ ። ባለሥልጣኑ ይህን ያሳወቁት በቅርብ ቀናትም መሰል አደጋ ዩክሬን ውስጥ በአማፅያን መፈፀሙን በማስታወስ ነበር ።«ዛሬ 10:20 ላይ ንብረትነቱ የማሌዥያ አየር መንገድ የሆነ ቦይንግ 777 አውሮፕላን ከራዳር እይታ ጠፍቷል ።የበረራ ቁጥር MN 11 ከአምስተርዳም ወደ ኳላላምፑር ነበር የሚበረው ። ባለፉት ቀናት የዩክሬን ጦር ኃይሎች አውሮፕላኖች AN 26 እንዲሁም SU 25 በሩስያ ግዛት ተመተው የወደቁበት ዓይነት 3 ተኛ አሳዛኝ አደጋ ነው ። ይሄ አውሮፕላን ሳይመታ እንዳልቀረ ነው የምገምተው ። በአፅንኦት መታወቅ ያለበት የዩክሬን ጦር ኃይል አየር ላይ ያለን ነገር ዒላማ አለማድረጉ ነው ።»

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የዩክሬን አማፅያን የዩክሬን ወታደራዊ አውሮፕላንን ከምድር ወደ ሰማይ በሚተኮስ ሚሳይል መምታታቸውን ተናግረው ነበረ ። የዩክሬን መንግሥትም ከሩስያ ግዛት በተተኮሰ ሚሳይል አንድ ወታደራዊ የእቃ ማጓጓዣ አውሮፕላኑ መውደቁን አረጋግጧል ። ትናንት ደግሞ አንድ ሱክ ሆይ 25 የዩክሬን ተዋጊ አውሮፕላን እንዲሁ በሚሳይል ተመቶ መከስከሱን የዩክሬን ባለሥልጣናት ተናግረዋል ።ዩክሬን ትናንት ምስራቃዊ ግዛቷ ውስጥ የተከሰከሰውን አውሮፕላንም መጥተው የጣሉት አማፅያኑ ናቸው ስትል አማፅያኑ ደግሞ እኛ ሳንሆን የዩክሬን መንግስት ኃይሎች ናቸው የተኮሱበት ይላሉ። የዩክሬን አማፅያን መሪ አሌክሳንደር ቦሮዳይ እንዲያውም ዩክሬን የመንገደኞች አውሮፕላን ስትመታ አዲስ አይደለም ሲሉ ክሱን አጠናክረዋል።«በርግጥ የመንገደኞች አውሮፕላን ተመቷል ፤ በዩክሬን አየር ኃይል ።እውነቱን ለመናገር ሆን ተብሎ የተደረገ ትንኮሳ ነው ። በመሰረቱ እንደምታውቁት ዩክሬን የመንገደኞች አውሮፕላን ስትመታ የአሁኑ የመጀመሪያ አይደለም ። »ቦርዶይ ያስታወሱት እጎአ በ2001 በዩክሬን ጦር ኃይል ሚሳይል ተመቶ ጥቁር ባህር ውስጥ የወደቀውን ከቴላቪቭ እስራኤል ወደ ሩስያ በመብረር ላይ የነበረ የሳይቤሪያ የመንገደኞች አውሮፕላን ነው ።የዩክሬንን አማፅያን ትደግፋለች የምትባለው ሩስያ ደግሞ ለአደጋው ተጠያቂው የዩክሬን መንግሥት ነው ትላለች ። ሆኖም ዩክሬን አውሮፕላኑን መጥታ ጥላለች ግን አትልም ።

በጥቃቱ አማጽያኑን ታስታጥቃለች የምትባለው የሩስያ እጅ አለበት የሚሉም አልጠፉም ። በርካታ የእስያ አየር መንገዶች መንግሥትና አማፅያን ውጊያ በሚያካሂዱበት የዩክሬን ምስራቃዊ ክፍል በደህንነት ስጋት ምክንያት መብረር አቁመዋል ። የማሌዥያው አየር መንገድ በዚህ የአየር ክልል እንዲበር መደረጉ እያጠያየቀ ነው ። ማልዥያ እንደ ሌሎቹ አየር መንገዶች መሰል የጥንቃቄ እርምጃ ያልወሰደችበትን ምክንያት የተጠየቁት የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጃብ ራዛክ በሰጡት መልስ አውሮፕላኑ በዚህ የአየር ክልል የበረረው ዓለም ዓቀፍ የአየር በረራ ባለሥልጣናት የመስመሩን ደህንነት ስላረገጡልን ነው ብለዋል ።የአውሮፓ የበረራ ደህንነት መስሪያ ቤት አውሮፕላኑ አደጋው በደረሰበት ወቅት 10ሺህ ሜትር ከፍታ ላይ እንደነበር ያ ማለት 330 ተብሎ የሚታወቀው የበረራ ደረጃ እንደሆነ አስታውቋል ። መስሪያ ቤቱ እንዳለው በዚህ ደረጃ በአካባቢው አውሮፕላኖች እንዲበሩ ፈቅዷል ።አንዳንድ የበረራ አዋቂዎች ግን ማሌዥያ የፀጥታ ችግር ባለበት በዚህ የአየር ክልል ለመብረር መድፈር አልነበረባትም የሚሉ አስተያየቶችን ነው የሰጡት ከ5 ወር በፊት ደብዛው ከጠፋው አውሮፕላኗ ሃዘን ገና ይልተፅናናችው ማሌዥያ አሁን ድርብ ሃዘን ውስጥ ገብታለች ። በተለይ አውሮፕላኑ በሚሳይል ተመቶ ነው የወደቀው መባሉ ሃዘኑን መራር አድርጎታል ።አውሮፕላኑ ቢያንስ የ10 አገራት ዜጎችን አሳፍሮ ነበር ። አብዛኛዎቹ የሆላንድ ዜጎች ናቸው ።ከመቶ በላይ የሚሆኑት ደግሞ የኤድስ ተመራማሪዎች ነበሩ ።

ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic