የማላዊ ፀረ ሙስና እንቅስቃሴ | የጋዜጦች አምድ | DW | 28.02.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የማላዊ ፀረ ሙስና እንቅስቃሴ

የማላዊ የፓለቲካ ታዛቢዎች በአሁኑ ጊዜ የሚጠይቁት ጥያቄ አንድ ነዉ። በአመራሩ ህብረት ዉስጥ የሚገኙትና ተቃዋሚዎች አዲሱን የአገሪቱ የፓለቲካ ቡድን ዲሞክራሲያዊ እድገት ፓርቲ በእንግሊዝኛዉ ምህፃረ ቃል ዲፒፒን ይደግፋሉ ወይንስ አይደግፉም የሚል።

በዚህ መሃል የአዲሱ ፓርቲ መስራች የሆኑትና ከተባበሩት የዲሞክራሲያዊ ግንባር በምህፃረ ቃል ዩዲኤፍ ፓርቲ የተሰናበቱት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ቢንጉ ዋ ሙታሪካ የወደፊት እጣ ፈንታ ጥያቄ ላይ ወድቋል።
ዲፒፒ የተቋቋመዉ ሙስናን ለመዋጋት ነዉ በመባሉ ከመሪያቸዉ ጀምረዉ በሙስናና ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች ለአገሪቱ የልማት እድገት የተሰጣቸዉን በጀት በማባከን የሚጠረጠሩት የዩዲኤፍ ከፍተኛ ባለስልጣናት ያላሰቡት በመድረሱ የተደናገጡ ይመስላል።
ማንጎሺ ከሚገኙት የዩዲኤፍ አባላት አብዛኛዎቹ ፕሬዝዳንት ሙታሪካ እምነታቸዉን ስላጎደሉ ከስልጣናቸዉ ባስቸኳይ እንዲለቁ ጠይቀዋል።
እነዚህ የዩዲኤፍ አባላት የሚሉት ሙታሪካን ለፕሬዝደንትነት ወንበር ያበቃናቸዉ እኛ ስንሆን ለፓርቲዉ የነበራቸዉን ታማኝነት በማጉደላቸዉ በሁለት ሳምንት ጊዜ ዉስጥ ፅህፈት ቤታቸዉን መልቀቅ አለባቸዉ።
ይህን ባያደርጉ ግን እርምጃ እንወስዳለን የሚል ዛቻም ሰንዝረዋል። ሊወስዱ ያሰቡት እርምጃ ምን ሊሆን እንደሚችል ግን ይፋ አላደረጉም።
የማንጎሺ የፓርላማ አባል አርብ ዕለት በሰጡት መግለጫ ሙታሪካ በፈፀሙት ተግባር የፓርቲዉ አባላት ማሳዘናቸዉን በመግለፅ በዪዲኤፍ አባልነታቸዉ ስናምናቸዉ ጉድ አደረጉን ብለዋል።
ዩዲኤፍ በፓርላማ ዉስጥ ከሚገኘዉ 193 መቀመጫ 49ኙን የያዘ ሲሆን ከሌሎቹ ፓርቲዎችና መንግስታዊ ካልሆኑ ህግ አዉጪዎች ጋር በመተባበር ማላዊን እየመራ የሚገኝ አንጋፋ የፓለቲካ ፓርቲ ነዉ።
በቅርቡ ሙታሪካም በበኩላቸዉ ሊገድሉኝ አቅደዋል በሚል በርካታ የዩዲኤፍ ፓርቲ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ካሰሩ በኋላ ይቅርታ ጠይቀዉ ለቀዋቸዉ ነበር።
የፕሬዝዳንቱ ከዩዲኤፍ መሰናበት እንደተሰማ በርካታ የካቢኔ አባላት እሳቸዉን ተከትለዉ መሰናበታቸዉን አስመልክተዉ የአገሪቱ ሬዲዮና ጋዜጦች በተደጋጋሚ ዘግበዋል።
ጊዜያዊዉ የፓርቲዉ ቃል አቀባይ ሳም ማፓሶ ግን ከፓርቲዉ የለቀቁት እጅግ አናሳና በጣት የሚቆጠሩ ናቸዉ በማለት አጣጥለዉታል። ሆኖም በጣት የሚቆጠሩት ምን ያህል እንደሆኑ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።
ከዩዲኤፍ የለቀቁት የፓርቲዉ አባላት እንደገለፁት ከፓርቲዉ መልቀቅ የፈለጉበት ዋነኛ ምክንያት ሙስናን ያለምንም ፍርሃት ለመዋጋት ነዉ።
ሆኖም መንግስታዊ ባልሆነዉና የማላዊ አስተዳደር ሁኔታን የሚቆጣጠረዉ ድርጅት ባልደረባ ኮሊንስ ማጋላዚ በዩዲኤፍ ዉስጥ ያሉትን በሙስና የተዘፈቁ ባለስልጣናት ለመጋፈጥ ፓለቲካዊ መሰረት ያለዉ አዲስ ፓርቲ ማቋቋም አያስፈልግም ነበር ባይ ናቸዉ።
በተጨማሪም ዩዲኤፍና አንዳንድ የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች የዲፒፒ የገንዘብ ምንጭ ከየት እንደሆነ ሙታሪካ እንዲገልፁ ጠይቀዋል።
በርካታ የዩዲኤፍ የበላይ አካላት ፕሬዝዳንቱ ከሌሎች ከፓርቲዉ ከተሰናበቱ አባላት ጋር በመመሳጠር የመንግስትን ገንዘብ ያላግባብ ሊጠቀሙ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ አላቸዉ። ፕሬዝዳንት ሙታሪካ ግን ጥርጣሬና ክሱን ዉድቅ አድርገዉታል።
ከዚህም ሌላ የሙታሪካ ከዩዲኤፍ መልቀቅ በእሳቸዉና በቀድሞዉ የማላዊ ርዕሰ ብሄርና የአሁኑ የዩዲኤፍ ሊቀመንበር በሆኑት ባኪሊ ሙሉዚ መካከል ያልታሰበ ጥላቻን ፈጥሯል።
በተቃራኒዉ ሙታሪካ በሙሉዚ መራጭነት ቀጣይ ፕሬዝዳንት ሆነዉ መመረጣቸዉ እንደ ትንሽ አሻንጉሊት የተቆጠሩበትና ከጀርባቸዉ ሙሉዚ በእጅ አዙር ማላዊን ይመራሉ ተብሎ ተገምቶ የነበረበት ወቅት ነበር።
የቀድሞዉ ፕሬዝዳንት ሙሉዚ በትረ መንግስቱን ከመልቀቃቸዉ በፊትም ፓርላማዉ እሳቸዉን ለሁለተኛ ግዜ ወደ ስልጣን ሊመልሳቸዉ የሚያስችል ማሻሻያ በህገመንግስቱ ላይ እንዲያደርግ ሞክረዉ ነበር።
ሆኖም የሙታሪካ ባህርይ ፕሬዝዳንት ከሆኑበት ዕለት አንስቶ ያረጋገጠዉ አንድ ነገር ብቻ ነዉ ያሰቡትን የሚያደርጉ ቁርጠኛ። ዲፒፒ በፓርቲነት የሚመዘገበዉ ዛሬ ነዉ።