የማሊ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ አሸናፊ ቡባከር ኬይታ | አፍሪቃ | DW | 13.08.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የማሊ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ አሸናፊ ቡባከር ኬይታ

የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ኢብራሂም ቡባከር ኬይታ የማሊ ፪ኛ ዙር ፕሬዚደንታዊ ምርጫ አሸናፊ ሆኑ። ምንም እንኳን የምርጫው ውጤት በይፋ ባይወጣም በኬይታ አንፃር የተወዳደሩት የቀድሞው የገንዘብ ሚንስትር ሱማይላ ሲሴ ሽንፈታቸውን በመቀበል ትናንት ከተፊካካሪያቸው ኬይታ ጋ በመገናኘት የእንኳን ደስ ያልዎት ምኞታቸውን መግለጻቸውን አስታውቀዋል።

ቀደም ሲል የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን እንዳስታወቁት፣ በከፊል በወጣው ውጤት ላይ ኬይታ ሲሴን በጉልህ የድምፅ ብልጫ በመምራት ላይ ናቸው። ፕሬዚደንታዊወ ምርጫ በሀገሪቱ ሥርዓተ ዴሞክራሲን እና መረጋጋትን መልሶ ያስገኛል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል። እንደሚታወቀው እአአ መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓም በሀገሪቱ መፈንቅለ መንግሥት ከተካሄደ እና ያኔ በሻለቃ አማዱ ሳኖጎ የተመሩ ወታደሮች 10 ዓመታት የሀገሪቱን ፕሬዚደንትነት ሥልጣን ይዘው የቆዩትን አማዱ ቱማኒ ቱሬን ከሥልጣን ካነሱ በኋላ ሰሜናዊ ማሊ በዚያ በሚንቀሳቀሱ ሙሥሊም ቡድኖች ቁጥጥር ስር የዋለበት ድርጊት የሀገሪቱን ፀጥታ ስጋት ላይ ጥሎት ነበር። እንደሚታወቀው፡ ይኸው አካባቢ በመጀመሪያየአዛዋድ ነፃ አውጪ ንቅናቄ በሚባለው ኤምኤን ኤልኤ በኋላም በተለያዬ እሥላማዊ ቡድኖች ተይዞ ነበር የቆየው። ይህ ሁኔታ ከሞላ ጎደል ሊያበቃ የቻለው ጥር 2005 ዓም ፈረንሣይ 4000 ወታደሮች ባጠቃለለ ጦር ጣልቃ ከገባች እና ከአፍሪቃውያን ጦር ጋ ባንድነት ዓማፅያኑን ከሞላ ጎደል ከብዙው አካባቢ ካስወጣች በኋላ ነው። ያም ቢሆን ግን አሁንም ያካባቢው ፀጥታ ስጋት ይታይበታል።


የምርጫ ኮሚሽን በይፋ ባወጣው የመጀመሪያ ዙር ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ውጤት መሰረት፡ ኢብራሂም ቡባከር ኬይታ 39.2% -ሲሴ ሱማይላ ደግሞ 19.4% የመራጭ ድምፅ አግኝተዋል።
በምርጫው ዘመቻ ወቅት ጎልተው የታዩት « ራሊ ፎር ማሊ » የተሰኘው ፓርቲ ዕጩ እና « አይ ቢ ኬ » በሚል ምሕፃር የሚታወቁት ኢብራሂም ቡባካር ኬክታ ከ1994 - 2000 ድረስ ጠቅላይ ሚንስትር እና የምክር ቤት ፕሬዚደንት ነበሩ። ጠንካራ የሚባሉት የ69ዓመቱ ኬይታ በምርጫው ዘመቻ ወቅት ለደጋፊዎቻቸው ባሰሙት ንግግር በተደጋጋሚ ያነሱት ሀሳብ ማሊ የማትከፋፈል ሀገር መሆንዋን እና የሀገሪቱን አንድነት ጠብቆ ማቆየት የተሰኘውን ነው። ይህ በሁለተኛውም ዙር ምርጫ ብዙ መራጮችን ድምፅ አስገኝቶላቸው ለድል አብቅቶዋቸዋል።

አርያም ተክሌ
አዜብ ታደሰ