የማሊ ውዝግብ እና የኤኮዋስ ዕቅድ | አፍሪቃ | DW | 04.07.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የማሊ ውዝግብ እና የኤኮዋስ ዕቅድ

በሰሜን ማሊ የቲምቡክቱ ከተማ ባለፈው ሣምንት አክራሪ ሙሥሊሞች ዓማፅያን የጥንት እስላማዊ የመቃብር ሀውልቶች ካወደሙ በኋላ ወደዚችው ሀገር ዓለም አቀፍ አጥቂ ጓድ እንዲላክ ጥሪው እየተበራከተ መጣ። የምዕራብ አፍሪቃ መንግሥታት የኤኮኖሚ ማህበረሰብ፡ በምሕፃሩ ኤኮዋስ እንዳስታወቀው፡ በወቅቱ ወደ ማሊ ሊላኩ የሚችሉ

3300 ወታደሮች በተጠንቀቅ ይገኛሉ። በዚሁ ጉዳይ ላይ የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በቅርቡ ይህን ሀሳብ የሚደግፍ ውሳኔ ሊያሳልፍ እንደሚችል የፈረንሣይ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሎውሮ ፋቢዩስ ተስፋቸውን ገልፀዋል።
አጥቂውን ጓድ ወደ ማሊ የመላኩ ዕቅድ ገሀድ ከመሆኑ በፊት ግን በባማኮ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት እንዲቋቋም ኤኮዋስ ጥረቱን እንደሚያጠናክር በዋጋዱጉ ከፈረንሣይ የሳህል ዞን ተጠሪ ፌሊክስ ፓጋኖ’ ጋ የመከሩት የቡርኪና ፋሶ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጂብሪል ባሶሌ አስታውቀዋል። ቡርኪና ፋሶ ኤኮዋስን በመወከል የማሊ ተቀናቃኝ ወገኖችን ለማቀራረብ የሽምግልናውን ሚና ይዛለች። ይኸው ጥረት በማሊ መረጋጋት ለሚሰፍንበት ድርጊት ወሳኝ ሚና ሊጫወት እንደሚችል ፌሊክስ ፓጋኖ’ ገልጸዋል።


« በማሊ መዲና ባማኮ የፖለቲካውን ሁኔታ ማረጋጋቱ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። ይህም ኤኮዋስ ያቀረበውን እና በሀገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ኃይላትን በጠቅላላ የሚያቅፍ በሽግግር መንግሥትነትን የሚያገለግል የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ምሥረታን ገሀድ በማድረግ ሊደረስበት ይችላል። የቡርኪና ፋሶ የሽምግልና ጥረት በዚህ ዓይነቱ የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳርፍ ሙሉ እምነት አለን። »
በዚሁ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ምሥረት ላይ የማሊ መንግሥት እና የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች የፊታችን ቅዳሜ በዋጋዱጉ ተገናኝተው ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ማሊ በወቅቱ በሼክ ሞዲቦ ዲያራ በሚመራ የሽግግር መንግሥት ትተዳደራለች፤ ግን፡ ይኸው መንግሥት ደቡባዊውን ማሊ ብቻ ነው የሚቆጣጠረው። ሰሜናዊውን፡ ብሎም፡ ሁለት ሦስተኛውን የሀገሪቱን አካባቢ ካለፈው ሚያዝያ ወዲህ በቱዋሬግ ዓማፅያን እና በአክራሪ ሙሥሊሞች ቁጥጥር ሥር ይገኛል። የቱዋሬግ ዓማፅያን ዓላማ በሰሜን ማሊ የራሳቸውን መንግሥት ማቋቋም ሲሆን፡ ከአል ቓይዳ ጋ ቅርበት ያላው የአንሳር ዲን ቡድን በመላ ማሊ ሸሪዓን መሠረት ያደረገ እሥላማዊ መንግሥት ማቋቋም ነው። በዚህም የተነሳ ሁለቱ ቡድኖች አሁን እርስ በርስ መዋጋት ጀምረዋል። የቱዋሬግ ዓማፅያን በዚያው በሰሜን ማሊ የምትገኘውን የጋው ከተማ እንደገና እንዳይቆጣጠሩ ለማከላከል የአንሳር ዲን ተዋጊዎች ፈንጂ ቀብረዋል። የአንሳር ዲን ቡድን በማሊ ከብዙ ምዕተ ዓመት ወዲህ ቅዱሳን የተባሉ እና ባህላዊ ቦታዎች ተጠብቀው የቆዩበት አሰራር የእሥልምና ሀይማኖትን ሀይማኖትን ይፃረራል በሚል ባለፈው የሣምንት መጨረሻ በቲምቡክቱ ከተማ የሚገኙ እና በተመ የባህል፡ የሳይንስ እና የትምህርት ድርጅት በቅርስነት የሚጠበቁ የቅዱሳን መቃብሮች ሙሥሊም የሀይማኖት አባቶች የሚከበሩባቸው መስጊዶች ን አውድመዋል። በሀገሪቱ ያሉ 16 ቅርሶችን በጠቅላላ እንደሚያወድሙ ዝተዋል። የዩኔስኮ ዋና ፀሐፊ ኢሪና ቦኮቫ አስከፊ ያሉት ውድመት አሁኑኑ እንዲያበቃ አሳስበዋል።


« በማሊ እየሆነ ያለው በጣም አሳስቦናል። የዓለም ህዝብ ቅርሶች የመቃብር ሀውልቶች፡ መስጊዶች እና ለዓለም ሕሕብ ከፍተኛ ትርጉም ያላቸው ጽሑፎች መውደማቸው ድርጊት እጅግ በጣም አሳስቦናል። »
ዩኔስኮ እአአ በ1988ዓም በዓለም ህዝብ ቅርሶች ዕውቅና የሰጣት የቲምቡክቱ ጥንታውያን የመቃብር ሀውልቶች አሁን አደጋ ባንዣበባቸው የድርጅቱ መዘርዝር ውስጥ እንዲገቡ ሰሞኑን ያወጀ ሲሆን፡ በወቅቱ ይኸው ውድመት እንዲያበቃ ማሳሰብ ብቻ እንደሚችል ቦኮቫ አስታውቀዋል። ግን፡ ድርጅታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ የፖለቲካ እና የሀይማኖት መሪዎችይህን ለመላው የሰው ልጅ ትልቅ ጥፋት የሆነው አሳዛኝ ውድመት እንዲያስቆሙ በመቀስቀስ ላይ መሆኑን አመልክተዋል። ጉዳቱን የሚገመግም አንድ ቡድን በቅርቡ ወደ ማሊ እንደሚልኩም አስታውቀዋል።
የዓለም ህዝብ ቅርሶች ለማስጠበቅ ከውጭ ብዙም ሊሰራ እንደማይችል መንበሩ በደቡብ አፍሪቃ የሚገኘው የአፍሪቃ የዓለም ህዝብ ቅርሶች ተቋም አባልደረባ ኢንገ ኸርበርት አስታውቀዋል። ውድመቱ ብሎም የማሊ ውዝግብ እንዲያቆም በሀገሪቱ ያሉ ተቀናቃኝ ወገኖችን ማቀራረብ እንደሚገባ የሽምግልናውን ሚና የያዙት የኤኮዋስ ተወካይ የቡርኪና ፋሶ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጂብሪል ባሶሌ ገልጸዋል።
« ታሪካዊዎቹ ባህላዊ መታሰቢያዎች፡ መቃብሮች መውደማቸው ቅዱሳኑን ቦታዎች የሚያውቁትን የማሊ ዜጎች ልብ አሳምሞዋል። ተቀናቃኞቹ ወገኖች ማንኛውንም ግጭት እንዲያስወግዱ፡ በገንቢ ውይይት መተማመን እንዲፈጥሩ ሀገሪቱ እንዲያረጋጉ ለማግባባት አሁን ጥረታችንን በእጥፍ ማሳደግ ይኖርብናል። »

ፔተር ሂለ
አርያም ተክሌ

ሒሩት መለሠ

Audios and videos on the topic