የማሊ ወቅታዊ ይዞታ፤ | አፍሪቃ | DW | 16.01.2013
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የማሊ ወቅታዊ ይዞታ፤

በማሊ የተሠማራው የፈረንሳይ ብረት-ለበስ ጦር አባላት በዛሬው ዕለት ወደሰሜን በመንቀሳቀስ ከእስላማውያን ታጣቂ ኅይሎች ጋር ፊት ለፊት መጋፈጣቸው እንደማይቀር ተነገረ። ፈረንሳውያኑ ወታደሮች፤ ከማሊ መንግሥት ወታደሮች ጋር በመተባበር፤ በማዕከላዊው

የሃገሪቱ ከፊል በምትገኘው ከተማ፣ በዲያባሊ የመሸጉትን አማጽያንን መክበባቸውን ወታደራዊ ዜና ምንጮች ጠቁመዋል። የጀርመን መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል፣ በርሊን ውስጥ ከወቅቱ የምዕራብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ማኅበረሰብ (ECOWAS)ሊቀመንበር የኮትዲቯሩ ፕሬዚዳንት፣ አላሳን ዋታራ ጋር ከመምከራቸውም፣ከዚሁ የምዕራብ አፍሪቃ ማኅበረሰብ የተውጣጡ ወታደሮችን ወደ ባማኮ፣ ማሊ ፣ ለማመላለስ 2 Transall የማጓጓዣ አኤሮፕላኖችን መንግሥታቸው እንደሚያቀርብ ቃል ገብተዋል።

የፈረንሳይ ብረት ለበስ እግረኛ ጦር፤ ወንዝ ዳር ከምትገኘው አቧራማዋ መዲና፣ ባማኮ ተነስተው፣ 300 ኪሎሜትር ወደሰሜን በመጓዝ፤ ኒዎኖ ከተሰኘችው ከተማ አቅራቢያ ይዞታቸውን አጠናክረዋል። በኒዎኖ ይዞታቸውን ማጠናከር የፈለጉትም ፤ እስላማውያኑ ታጣቂ ኃይሎች፣ ሴጉ ወደተባለችው ከተማ እንዳይገሠግሡ ለመግታት መሆኑ ተመልክቷል። የማሊ ጦር ሠራዊት በፊናው፤ ከሞሪታንያ ጋር የሚያዋስነውን የአገሪቱን ድንበር በመቆጣጠር ላይ ነው። የማሊና የፈረንሳይ ወታደሮች፤ ከተማይቱን መልሰው በቁጥጥራቸው ሥር ለማዋል ያቀዱ ሲሆን፤ ቀላል ውጊያ እንደማይጠብቃቸው የፈረንሳይ መከላከያ ሚንስትር ዣን ኢቭ ለ ድሪያን ጠቁመዋል።

«የምንጋፈጠው፤ በፍጥነት ከሚንቀሳቀስ፣ ቁርጠኝነት ካለው፣ በሚገባ ከታጠቀና በደንብ ከሠለጠነ የጠላት ኃይል ነው። ይህም ኃይል፤ በየቁጥቋጦውና በየኮረብታው መደበቅ የሚችል ነው።»

ሰሜን ማሊ በቱአሬጎችና እስላማዊ ታጣቂ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር መዋል የጀመረው ካለፈው ዓመት መጋቢት ወር አንስቶ ነው። የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ፍርንሷ ዖላንድ፤ ምዕራባዊቷ ሀገር ማሊ ፣ እስከትረጋጋ ድረስ የአገራቸው ወታደሮች፣ በዚያ እንደሚቆዩ ፤ ያም ሆኖ፣ የማረጋጋቱን ኀላፊነት ለምዕራብ አፍሪቃው ሰላም አስከባሪ ኃይል እንደሚያስረክቡ ነው የገለጡት።

የምዕራብ አፍሪቃ ማኅበረሰብ፤ ወታደራዊ ኃላፊዎች፣ በዛሬው ዕለት ባማኮ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ተገናኝተው፤ የተባበሩት መንግሥታት ባጸደቀው ስምሪታቸው ዝርዝር ጉዳይ ላይ መክረዋል። ወደ ሰሜን ማሊ የሚዘምተውን ፤ የምዕራብ አፍሪቃን ሰላም አስከባሪ ኃይል የምትመራው ናይጀሪያ ስትሆን፤ ቤኒን ፤ ጋና፣ ኒዠር ፤ ሴኔጋል፤ ቡርኪና ፋሶና ቶጎም ተሳታፊ ወታደሮችን እንደሚመድቡ አረጋግጠዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የኮትዲቯርፕሬዚዳንትናየECOWAS ሊቀመንበርአላሳንዋታራ፣ማሊውስጥእስላማዊታጣቂዎችንወግቶበማስወጣቱእርምጃ፤አውሮፓውያን ተባባሪዎችሁሉ ድጋፍእንደሚሰጡያላቸውንተስፋአንጸባርቀዋል።ዋታራ፤ከጀርመንመራኂተ-መንግሥት አንጌላ ጋር ፣ በርሊን ውስጥ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፤ የጦሩን እርምጃ ፣ አውሮፓውያን ሁሉ እንዲደግፉ ቢጠይቁም፤ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ዖላንድ፣ የወሰዱትን እርምጃ ማለፊያ ነው ሲሉ አድንቀዋል።

የጀርመን የልማት ተራድዖ ሚንስትር ዲርክ ኒበል፤ ውጊያ ለሚካሄድባት ማሊ አስቸኳይ እርዳታ ሊቀርብ እንደሚገባ ተናግረዋል።

« በዚያች ሀገር ዴሞክራሲ ላይ ጥቃት የሠነዘሩና ሃይማኖታዊ መንግሥት ለማቋቋም የተነሣሡት ወገኖች፤ ስለ ህዝቡ ደንታ የላቸውም፤ በሰሙኑም ሆነ በደቡቡ የሀገሪቱ ክፍል ፈቅዶ የሚደግፋቸውም የለም። ከሊቢያው ጦርነት ተሳትፎ በኋላ፣ የእነርሱ ጥረት፤ ሽብርን በማዛመት ፤ በሥልጣን ረገድ የተፈጠረውን ክፍተት መሙላት ነው። በማሊ ህዝብ ላይ በየዕለቱ የሚፈጠር ሽብር መገታት ያለበት ነው።»

የማሊው ዘመቻ፣ በአየር ኃይል ብቻ ሳይሆን በብረት ለበስ ጦር እየታገዘ የሚካሄድበት ጊዜ ሲመጣ የሰሜን ማሊ ኑዋሪዎች ይዞታ ምን ይመስል ይሆን? ዲያባሊ የተባለችው ከትናንት በስቲያ በአማጽያኑ ቁጥጥር ሥር የዋለችው ከተማ አንድ ኑዋሪ ፣ ስለሁኔታው እንዲህ ነው ያስረዱት።

«አማጽያኑ፤ አካባቢውን ብቻ ሳይሆን ፣ አሁን ከተማይቱንም ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረዋል። እስካሁን በሰላም ነው ያለፉት። የቆሰለም የተገደለም የለም። ይሁን እንጂ፣ድንጋጤ የነገሠ ነው የሚመስለው። ህዝቡ ብርቱ ሥጋት ተደቅኖበታል። ሁላችንም የየቤታችን እሥረኞች ሆነናል። እኔ ራሴ በቀጥታ ከብሄራዊው ጎዳና ዳር ነው የምኖረው። 2 ተዋጊዎች በድብቅ ቤቴ ውስጥ ገብተው ነበር። ሰዎቹ አንዳች ፍርሃትም ኀፍረትም የላቸውም። ከቤቴ መስኮት በኩል በአንድ ሄሊኮፕተር ላይ ተኩሰው ነበር። ይሁንና ፤ «ተመሥገን!» ነው ማለት የሚቻለው። ሄሊኮፕተሩ አጸፋውን አልተኮሰም። አለበለዚያ እኔ ራሴ ዛሬ በህይወት ልገኝ ባልቻልሁ ነበር።»

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 16.01.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17L9Y
 • ቀን 16.01.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17L9Y