የማሊ ወቅታዊ ይዞታ | አፍሪቃ | DW | 19.07.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የማሊ ወቅታዊ ይዞታ

በሰሜን ማሊ ተጠናክሮ የሚገኘው ፣ ከኧል ቓኢዳ ጋር ተጣማሪ መሆኑ የሚነገርለት ጂሃዳዊ ቡድን፣ ባለፈው ጥቅምት በምዕራባዊው አልጀሪያ አፍኖ የወሰዳቸውን ሦስት አውሮፓውያን የአንድነት ንቅናቄና ጂሃድ በምዕራብ አፍሪቃ የተሰኘው ቡድን መሪ ሙሐመድ

ዑልድ ሂቻም ለ AFP ገለጡ። በሌላ በኩል ፤ የቱዓሬግ አማጽያንን ከሰሜን ማሊ ያባረረው አንሣር ዲኔ ፤ የአገሪቱን ከሁለት መከፈል እንዲጸና ነው የሚፈልገው። ይህ በእንዲህ እንዳለ የማሊን ውዝግብ፣ በዲፕሎማሲ ለመፍታት፣ ጥረት ይደረጋል ቢባልም፣ ከበስተጀርባ፤ ወታደራዊ መፍትኄ፤ በአማራጭነት በሰፊው እየተመከረበት መሆኑ ነው የሚነገረው። ከምዕራብ አፍሪቃ ጋዜጠኛ አሌክሳንደር ገኧበል የላከውን  ሐተታ ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የማሊ ሰንደቅ ዓላማ፣ በቲምቡክቱ መስተዳድር ጽ/ቤት ፊት ለፊት ይውለበለብ ነበር። አሁን ግን፣ በህንጻው የሚውለበለበው፤ አንሣር ዲኔ የተባለው እስላማዊ ንቅናቄ ጥቁር ሰንደቅ ዓላማ ነው። ተቆጣጣሪው ኃይልም ራሱን እስላማዊ ፖሊስ ኃይል እያለ የሚጠራው ኃይል ነው።

ቲምቡክቱ ፣ በእስልምና የተቆረቆረች ናትና ፤ እስላማዊው ህግ (ሸሪያ) መተዳደሪያዋ ይሆናል ሲሉ የአንሳር ዲኔ ቃል አቀባይ፣ ዑመር ዑልድ ሃማሃ አስታውቀዋል።

1«በመላዋ ማሊ፣ በመላው አፍሪቃ፣ ሸሪያን ከጧት እስከ ማታ እንዲሠራበት እናደርጋለን። እንደ ጥሩ ሙስሊሞች ኑሮን መምራት፣ ሞታችንም እንደ ሰማእታትእንዲሆን ነው የምንፈልገው። አብዛኞቹ የማሊ ተወላጆችም፣ ሙስሊሞች ናቸው፤ ስለዚህም አመራር ያስፈልጋቸዋል። እንዴት መኖር እንደሚገባቸው አመራር እንሰጣቸዋለን። »

በአንሣር ዲኔ አስተዳድር ሥር ሁኔታው አሰቃቂ መሆኑን የሰሜን ማሊ ተወላጆች ይናገራሉ። ሰውነታቸውን ሙሉ በሙሉ ሸፍነው የማያሄዱ ሴቶች በአደባባይ ይገረፋሉ። የመባልእት እጥረት አለ። በሽታም አገርሽቷል። የአርዳታ ድርጅቶች እንደገለጹት፣ ሴቶችን አስገድዶ መድፈር፣ ልጆችን ለውትድርና መመልመል ተሳፋፍቷል። በቲምቡክቱ የጥንት መካነ መቃብር ሃውልቶችን ማፈራረሱ ቀጥሏል። እስላማውያኑ የአንቅሥቃሴው አባላት የመካነ መቃብሮቹ ሃውልቶች የአስላማዊነት ምልክት የለባቸውም ነው የሚሉት፤ የሳንከሬ መሥጊድ ኢማም አብዱረህማን ቤን ኢሳዩቴ--

3,«ቲምቡክቱ የኅልውና መንፈሷን ልታጣ  ነው። ሊታገሡት በማይገባ ዝርፊያ በመመዝበር ላይ ናት። የቲምቡክቱ ኑዋሪዎችም፣ በጨካኝ ነፍሰ-ገዳዮች ስለት አንገታቸው ሊቆረጥ ተስሎባቸዋል።»

የማሊ የሽግግር ጠ/ሚንስትር  ዲያራ ሰሜናውያኑን  የአክራሪ እስልምና ንቅናቄ አባላት ለማባረርና የተገነጠለውን የቱአሬግ ክፍለ ሀገር አዛዋድን መልሶ ለመቆጣጠር ዐቢይ አፀፋዊ ዘመቻ እንዲካሄድ አሳስበዋል። የምዕራብ አፍሪቃው የኤኮኖሚ ማኅበረሰብ(ኤኮዋስ) በተ መ ድ ላይ ግፊት በማድረግ ላይ ሲሆን ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም፣ ከአንድ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ ነው የሚጠበቀው። በናይጀሪያ አመራር 3,300 ወታደሮች ወደሰሜን ማሊ እንዲዘምቱ ፣ ምልክት ብቻ መስጠት ነው የሚፈለገው።

የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ማኅበር የሳሔል አካባቢ ተጠሪ ፍሎሬንት ጅል በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ላይ የተቆናጠጠ ቡድን እስካለ ድረስ፣ ጣልቃ መግባቱ አደገኛ ነው፣ነው የሚሉት።

«ይህ እንዲሆን አንመኝም ። ያን መሰሉ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት፣ ኀላፊነት የጎደለው እርምጃ ነው የሚሆነው። በመጀመሪያ፣ ከሰሜን ማሊ እንቅሥቃሴ ወገኖች  ጋር ድርድሩን መቀጠል ይበጃል። ያ ሳይሳካ ከቀረ ብቻ  ነው ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ቀጣይ እርምጃ ቢሆን የሚመረጠው።»

ድርድሩ የሚያዝ የሚጨበጥ አልሆነም። የ «ኢኮዋስ» ወታደሮች፣ የበረሃ ውጊያ ልምድ የላቸውም። የቀድሞ ቅኝ ገዥ ፈረንሳይ፤ በማሊ ዜጎች ዘንድ ሐቀኛ ሸምጋይ ሆና አትታይም። ወሳኝ ሚና እንዳላት የሚነገርላት ፤ አልጀሪያ፤ ጓሮዋ አጠገብ ጦርነት እንዲካሄድ አትሻም፤ የአልጀሪያ የስለላ ድርጅት በአስላማዊው ማግሬብ ለተጠላው ኧል ቓኢዳና በምዕራብ አፍሪቃ ለጂሃድ የአንድነት ድርጅት ለተሰኘው ቡድን፤ አማራጭ  ይሆን ዘንድ የአንሳር ዲኔን መሪ ኢያድ አግ ጋሊን ነው የሚያቀርበው።

ግራም ነፈሰ ቀኝ፤ በዲፕሎማሲም ሆነ በጦር ውዝግቡን መፍታት  እልህ አስጨራሽ እንደሆነ ነው የሚታሰበው። በሰሜን ማሊ፣ አክራሪዎች፤ የሚቆጣጠሩት የሳሔል ግዛት (ሳሔልስታን)እንዲመሠረትም ሆነ፣ አያያዙም ፤ ፍጻሜውም የማይታወቅ የምድረ-በዳ ጦርነት እንዲካሄድ ማንም አይፈልግም። ታዲያ ውዝግቡ ፣እንዴት ይፈታል? ለሚለው ጥያቄ ፣  አሁንም፣ መልሱ ፣ እንቆቅልሽ ነው።

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 19.07.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15b5z
 • ቀን 19.07.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15b5z