የማሊ ስልጠና እና ጀርመን | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 04.12.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የማሊ ስልጠና እና ጀርመን

በምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ማሊ የጸጥታ ሁኔታዉ የቱዋሬግ አማፅያን በሰሜን የተኩስ አቁም ካወጁ በኋላ እየተጠናከረ መሄዱ ነዉ የሚነገረዉ። አካባቢዉ ለእስላማዊ ታጣቂዎቹ ተታኩሰዉ የሚያፈገፍጉበት እንደመሆኑ በየጊዜዉ ከባድ ጥቃት ይደርስበታል።

የአዉሮጳ ኅብረት የሰሜን ማሊን የፀጥታ ይዞታ እንዲያጠናክር ለማሊ ጦር ወታደራዊ የስልጠና መርሃግብር ዘርግቷል። ለዚሁ ተግባር 195 አሰልጣኞች የተላኩ ሲሆን 35ቱ ጀርመናዉያን ናቸዉ።

ማሰልጠኛ ጣቢያዉ የሚገኝባት ኮሊኮሮ ከዋና ከተማዋ ባማኮ በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። ወደዚያ የሚያደርሰዉ መንገድ አስቸጋሪ ቢሆንም የአዉሮጳ ኅብረት የማሊ ስልጠና ተልዕኮ በእንግሊዝኛ ምህጻሩ EUTM ተግባሩን ባለፈዉ ሚያዝያ ወር ነዉ የጀመረዉ። ከስልጠና ጣቢያዉ በአንድ ወገን የአሰልጣኞቹ መኖሪያና ጽህፈት ቤት ይገኛል። በዚህ ስፍራም መመገቢያ፤ ወታደራዊ ሃኪም ቤት፤ መማሪያ ክፍሎች፤ ቡና ቤትና የፒዛ መጋገሪያ በጣሊያንና ጀርመን ወታደሮች ተገንብቷል። በመቶ ሜትር ርቀት ገደማ ደግሞ የማሊ ወታደሮች ድንኳኖች ይታያሉ፤ መኖሪያና ማብሰያቸዉ መሆኑ ነዉ።

በአዉሮጳ ኅብረት የስልጠና ተልዕኮ የሚሳተፉት ሃገራት የሥራ ድርሻ በግልፅ ተቀምጧል። የጀርመን ወታደራዊ የህክምና ባለሙያዎች የሃኪም ቤቱ ተጠሪዎች ናቸዉ። 30 የሚሆኑት ጀርመናዉያን ወታደሮች ደግሞ በጥቅሉ 600 ወንዶችን ለ15 ወራት የሚያሰለጥነዉ መርሃግብር ይሳተፋሉ። ሌፍተናንት ቶርሽተን ሌከርት የጀርመን ልዑክ መሪ ናቸዉ፤

«በሰሜን ማሊ የሚሰማሩ በጥቅሉ በአራት ተዋጊ ቡድን የተካተተዉን የማሊ ጦር እናሰለጥናለን። በሰሜን ያለዉ እጅግ መጠነኛ መሠረተ ልማት፣ በአብዛኛዉ የደረቀ የሳር ምድር ወይም በረሃማ የአየር ንብረት ነዉ፤ እናም እዚህ አካባቢ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለማደርግ የግድ ራስን መቻል ያስፈልጋል። ራስን መቻል ማለት፤ እንዲህ ባለዉ ሁኔታ ከመቶ ኪሎ ሜትሮች በላይ ረዥም ርቀት ላይ አስፈላጊ ነገሮችን ማቅረብ አይቻልም፤ ማለትም ሲመሽ ዉጭ መተኛት፣ ምግብ ከገበያ መግዛት የመሳሰሉት ሁሉ በግል የሚደረጉ ናቸዉ። እናም እነዚህ አቅርቦቶች ሁሉ ሊደራጁና ሊዘጋጁ ይገባል።»

ሰሜን ማሊ አደገኛ አካባቢ ተደርጎ ነዉ የሚታየዉ። ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2012ዓ,ም አንስቶ አብዛኛዉ ግዛት በቱዋሪግ አማፅያን ቁጥጥር ሥር ሲሆን አክራሪ ሙስሊሞቹ ኅብረተሰቡን ሲያተራምሱ እንደቆዩ ይነገራል። ባማኮ ዉስጥ በፕሬዝደንት አማዱ ቱማኒ ቱሬ ላይ የተካሄደዉ መፈንቅለ መንግስት ለሰሜኑ የጸጥታ ይዞታ መጓደል ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል። ገና ባለፈዉ ሳምንት ነዉ የመፈንቅለ መንግስቱ አቀናባሪ ሃያ ሳኖጎ በቁጥጥር ሥር የዋሉት። ባለፉት ወራት የማሊ የፀጥታ ሁኔታ በተሻለ መስመር ላይ እንደሚገኝ ሲገመት ቆይቷል። ለዚህም በሰሜኑ ግዛት የሚንቀሳቀሱት የቱዋሬግ አማፅያንና የአማሊ ወታደራዊ ኃይል የተኩስ አቁም ማወጃቸዉ ዋነኛ ምክንያት ነዉ። እንዲያም ሆኖ ገና በቋፍ የሚገኘዉ የሰላም ሁኔታም ከስድስት ወራት የዘለለ አይመስልም። ባለፈዉ ሳምንት ዓርብ ዕለት አማፅያኑ የተስማሙት የተኩስ አቁም እንዳከተመ እና ከጦሩ ጋ ለዉጊያ መዘጋጀታቸዉን አሳዉቀዋል። በዚህ ምክንያትም የሰሜን ማሊ የፀጥታ ይዞታ ዉጥረት አይሎበታል። EUTM የሚያሰለጥናቸዉ ኩሊኮሮ የሚገኙት የማሊ ወታደሮች ምን ሊያጋጥማቸዉ እንደሚችል ገና አለየለትም።

እያንዳንዱ ሠልጣኝ ባታሊዮን በአምስት ምድብ ለአስር ወራት ያህል ይሠለጥናል። ቅድሚያ የሙከራ ሳምንታት ይሆኑና፤ መሠረታዊ ሥልጠናዉ ይከተላል፤ ከዚያም ልዩ ስልጠናዉ ይቀጥላል። በዚህም የማሊ ወታደሮች የመጀመሪያ ተግባራቸዉ ምን እንደሚሆን ይማራሉ፤ በዚህም የመሳሪያዎቹን አጠቃቀምና በዉጊያ ወቅት በሰሜኑ ግዛት ምን ማድረግ እንደሚገባቸዉ ይሰለጥናሉ። ስልጠናዉ በቀን ሲሆን ሊከሰቱ በሚችሉ አጋጣሚዎች የተደገፈ ነዉ። ከሰልጣኞቹ አንዱ፤

«በጎዳናዉ መካከል አንዱ ባንዱ ላይ ተደጋግፈዉ የሚገኙት ድንጋዮች ይታዩሻል? ያ ተጠርጣሪ ነዉ። አሁን ተከላካዩ የጸጥታ ኃይል ድልድዩን መክበብን ጨምሮ ተገቢዉን ጥንቃቄ መዉሰድ ይኖርበታል። ፈንጂ አምካኞቹ ተግባራቸዉን አከናዉነዉ ማሳወቅ አለባቸዉ፤ ኦ ተኩስ ተከፈተ! ጠላት እየተኮሰ ነዉ። ይህ ማለት ፈንጂዎቹን ከማምከናችን በፊት ለጦርነት መዘጋጀት ይኖርብናል ማለት ነዉ።»

ለማሰልጠን ማሊ የገቡት የጀርመን ወታደሮች በመጀመሪያ ለስልጠናዉ የሚያስፈልጉ አንዳንድ ቁሳቁሶችን በአቅራቢያቸዉ ባለማግኘታቸዉ ግራ ተጋብተዉ እንደነበር ይገልጻሉ። ዉሎ አድረዉ ግን ከሚያሠለጥኗቸዉ የማሊ ወታደሮች ጋ ከአካባቢዉ ከሚገኙ ነገሮች ሊሠሯቸዉ በመቻላቸዉ ችግር መቅለሉን አስተዉለዋል። የአዉሮጳ ኅብረት በታህሳስ ወር አጋማሽ ላይ የማሊ ስልጠና ተልዕኮን ስለማራዘም ይመክራል። የጀርመን ወታደሮችም እዚያዉ የመቆየታቸዉ ነገርም እንዲሁ።

ዛንድሪን ብላንካርድ /ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic