የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 24.07.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ከሰሞኑ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ትኩረት ስበው ከነበሩ ኢትዮጵያ ተኮር ርዕሶች መካከል የህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት የፈጠረው ስሜት እና የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፂዎን ገብረሚካኤል መግለጫ ይገኙበታል። ከድምፃዊ ሀጫሉ ግድያ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የጠፋው የሰዎች ህይወት እና ንብረትም የመነጋገሪያ ርዕስ እንደሆነ ቀጥሏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:14

የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

በዋናነት የብዙኃንን ትኩረት የሳበው የህዳሴው ግድብ ጉዳይ ነው። በአፍሪቃ ህብረት ሸምጋይነት አለመግባባቶን ለማስወገድ ሲደራደሩ የሰነበቱት ሶስቱ ሀገራት ፤ ኢትዮጵያ ፣ሱዳን እና ግብፅን ውጤት ሲጠባበቁ የነበሩት ኢትዮጵያውን  ዕሮብ ዕለት የግድቡ የመጀመርያው ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ መንግሥት ይፋ ሲያደርግ ብዙዎች ደስታቸውን ገልጸዋል። ጉዳዮም ባለፉት ሳምንታት በብሔር እና በአመለካከት ተከፋፍሎ የተስተዋለውን ህዝብ በመጠኑ አንድ ያደረገ ይመስል ነበር።  በትዊተር፤
የትምወርቅ ጃገማ «እንኳን ተወለድኩኝ እንኳንም ኖርኩኝ የአባይን ግድብ በማየቴ በዘመኔ ደስተኛ ነኝ።» ሲሉ አለማየሁ ገመዳ «የህዳሴው ግድብ ስኬት በመለስ ዜናዊ የተጀመረ፣ በሀይለማርያም ደሳለኝ የቀጠለ፣ በዐቢይ አህመድ ከግብ በመድረስ ላይ የሚገኝ፣ የአመታት እልህ አስጨራሽ ኢትዮጵያዊ ዱላ ቅብብሎሽ ውጤት ነው።» ብለዋል። መቅደስ አበበ ደግሞ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ለነበሩት እና በጥይት ተመተው ሞተው ለተገኙት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ « በሕይወት ኖረሕ ይሄን ደስታ ለማየት ባትታደልም ጥረህ የደከምክለት ፤ ሂወትህን ላጣህበት አባይ፤ ሕልምሕ ተሳክቷል ! ሲሉ ገልፀዋል።
ኤሊያስ መሰረት ደግሞ « በህዳሴ ግድብ ዙርያ መልካም ነገር ሲነገር እንደሚከፋው ኢትዮጵያዊ ግራ አጋቢ ሰው የለም» ነው ያሉት።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከኢትዮጵያ አንዳንድ ባለስልጣናትም የህዳሴው ግድብ የመጀመርያው ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አወድሰዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ  በትዊተር ባሰራጩት መልዕክት፤ «ዕለቱን ታሪካዊ ቀን በማለት እንኳን ደስ አለን። ህልማችን እውን እየሆነ ነው። በርካታ ኢትዮጵያውያን እና መሪዎቻችን አባይን ለማልማት ከፍተኛ ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም እቅዳቸው በተለያዩ መሰናክሎች ተስተጓጉሏል። ነገር ግን  «እኛ አሁን ባይሳካልንም መጪው ትውልድ ይገነባዋል» የሚል ታላቅ እምነት ነበራቸው። ይህ ትውልድ ያንን አደራ ጠብቋል» ብለዋል።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ «የዘመናችን የታሪክ ስኬት የሆነው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከወሳኝ ምእራፍ ላይ ደርሶ የመጀመሪያ ዙር የውሀ ሙሌት በስኬት ተጠናቋል።ሀገራችን ለዚህ ስኬት በመብቃቷ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ ያለን ለማለት እወዳለሁ።» ነው ያሉት።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ  በእንግሊዘኛ ባሰራጩት መልዕክት «  ውኃው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲሞላ ተፈጥሮ ሳይቀር በተዓምራዊ ሁኔታ ከጎናችን ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሬ፣ ገዱ ፣ ዶክተር ስለሺ እና መላው ቡድኑ እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ደስ ያላችሁ » የሚል መልዕክት ነው ያሰራጩት። 

ሌላው የመገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ የነበረው የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል በክልሉ የመገናኛ ብዙኃን ያስተላለፉት መልዕክት ነው። ዶ/ር ደብረፂዮን በትግራይ ሊደረግ የታቀደዉን ምርጫ ለማደናቀፍ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ፣የኤርትራ መንግሥትና ሌሎች ሃይሎች በተቀናጀ ሁኔታ እየሰሩ ነዉ ማለታቸው ብዙዎችን ያላሳመነ ነበር። በርካቶችም መግለጫውን ተቀባብለውታል።  አንተ ሰው አድርገኝ የተባሉ አስተያየት ሰጪ በዶይቸ ቬለ የፌስ ቡክ ገፅ ላይ «አብይ አህመድ ኤርትራ በመሄዳቸው ያደረባቸው ጥርጣሬ እና ፍራቻ ነው» ሲሉ ሞገስ ደግሞ « ምርጫ ወይስ ቅርጫ?በዚህ ኣሳሳቢ ግዜ የሰውን ህይወት ማትረፍ ሲቻል፤ ለስልጣን ቅድድም ስትሄዱ ኣታፍሩም።ሰው ከሌለ ማንን ነው የምታስተዳድሩት? ሲሉ ይጠይቃሉ።  ያሬድ ተፈራ ደግሞ « ተቀናቃኝ ፓርቲዎችን ከክልሉ ካባረረ በኋላ ምን አይነት ምርጫ ሊደረግ ነው ? ተፎካካሪ ህወሀት፣ አስመራጭ ህወሀት፣ ተዛቢ ህወሀት፣ ምርጫ ቦርድ ህወሓት ድምፅ የሚቆጥረው እና ማሸነፉን የሚያውጀውም ራሱ ህወሓት» የሚል አስተያየት ነው ያሰፈሩት።  ዮናስ ይልማ «የሚያወጧቸው መግለጫዎችና የሚታገሉበት ምክንያትና ግብ ፣እንኳን ለኛ ለነሱም የገባቸው አይመስልም።» ሲሉ ይተቻሉ። አሉላ ሰለሞን ደግሞ በትዊተር በእንግሊዘኛ ቋንቋ ባሰፈሩት አስተያየት፤ በትግራይ ወቅቱን ጠብቆ ምርጫ ይካሄዳል። አስመራ እና አራት ኪሊ ውስጥ የምርጫ አለርጂክ ያለባቸው አያስቆሙትም።  የትግራይን ህዝብ ምርጫ ከማካሄድ ለማስቆም መጣር ከንቱ ሙከራ ነው» ብለዋል። 

እንዲሁ በዚሁ ሳምንት የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ቀልብ የሳበው ጉዳይ ከድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በተነሱ አመፆች የወደሙ ንብረቶችን፤ መፈናቅሎች እንዲሁም ሞትን የሚመለከቱ ዘገባዎች ነበሩ። ኢትዮጵያ ውስጥ የኢንተርኔት አገልግሎት በከፊል ከተከፈተ በኋላ የተሰባበሩ መስኮቶች፣ በእሳት የጋዩ መኪናዎች እና ህንፃዎችን የሚያሳዩ ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች ትኩረት ስበዋል። እንዲሁም ንብረት እና የቤተሰባቸው ህይወት የጠፋባቸው ሰዎች አቤቱታ ተሰምቷል። የከፋ አደጋ ካስተናገዱ ከተሞች አንዷ በሆነችው ሻሸመኔ የደረሱትን ውድመቶች የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ምስሎችን እየተቀባበሉ የደረሰው ጥቃት ሶርያ ወይም ኢራቅ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሆነ በቁጣ እየተናገሩ ነበሩ። ጥቃቱ ብሔር ተኮር ነበር ሲሉ የወቀሱም አሉ። የተለያዩ ትናንሽ እና ትላልቅ ባለሀብቶች ድርጅታቸው ወድሞ  ባዶ እጅ መቅረታቸውን የተመለከቱ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የመፍትሄ ሀሳብም ሰንዝረዋል።  ጉቱ ለታ መንግስት ለተጎጅዎች ተገቢውን ካሳ በፍጥነት መክፈል አለበት ሲሉ ቢንያም አርሴናል ደግሞ « ያላምንም ጥያቄ ከክልሉ ባጃት ተቀንሶ ለተጎጂዎች መሰጠት አለበት እነዚህ ሰዎች እኮ ለክልሉ መንግስት ግብር ሲከፋሉ የነበሩ ናቸዉ» ብለዋል።
ዘኩሉ፤  ዲያስፖራ ነው እንዴ በገጀራና በቆንጮራ ሲጨፈጭፋችሁ የኖረ፣ ንብረት ያቃጠለባችሁ፣ ለመውጣት ለመግባት ስጋት የሆነባችሁ፣ በፕሮፓጋንዳ ሲያደርቃችሁ የሚውለው? ዲያስፖራ አገሪቱን አደራ ብሏችሁ ቢወጣ እናንተ እንዳይሆን አደረጋችኋት! ያሳዝናል! ነው ያሉት።
ሙና ሀበሻ፤ «ወገኔ ኑሮውን ለማቅናት ስንት አመት ለፍቶ ያፈራውን ንብረቱን በአንድ ቀን ለሌት!  እሺ ንብረት ሊተካ ይችላል የሰውልጅስ? ፍርዱ ከፈጣሪ ነው! ህይወት ይቀጥላል ኢትዮጵያ የቃልኪዳን ምድር ነች» ብለዋል። እንዲሁ ከውጭ ሀገር አስተያየታቸውን በትዊተር ያጋሩት እና ኢትዮጵያ የተባሉ ሰው፣ « ኢትዮጵያ ሀገራችንን አታውድሙ። የሰማችሁትን ነገር ጭንቅላታችሁን ተጠቅማችሁ አሰላስሉ ሀገር ማፍረስ ቀላል ነው መገንባት ሊቢያ እና ሶሪያም አልቻሉም። 
ከሚኪይ ደግሞ «ኢትዮጵያዊ እንዴት ከእጅ ወደአፍ እንደሚኖር ጠፍቷቸው ነው የደሃ ንብረት የሚያቃጥሉት? የጤና ተቋም የሚያቃጥሉ?» ብለዋል።
የደረሰውን ጥቃት ጨርሶ ቦታ ያልሰጡ፣ ለቀጣይ አመፅ የሚያበረታቱ እና የጥላቻ ንግግር የሚያሰራጩንም የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሰሞኑን አስተናግደዋል።

ልደት አበበ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic