የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 26.04.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ባለፈው ሳምንት የተጀመረው የህክምና ባለሙያዎች ተቃውሞ በዚህም ሳምንትም ቀጥሏል። የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ይህን የተመለከቱ አስተያየቶች በማህበራዊ መገናኛ ገጾች አስፍረዋል። የኢትዮ ኤርትራ ድንበር መዘጋትም ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:38

«ይህ የምጥ ጣር መጀመሪያ ነው»

በአርሲ ዩኒቨርስቲ ያሉ ዕጩ ሀኪሞች የተቃውሞ ሰልፍ ፖሊስ ሃይል ተጠቅሟል ሲሉ የተነሳው ተቃውሞ ተዛምቶ፤ ተዛማች ጉዳዮችም ተነስተው በሌሎች በሀገሪቱ ያሉ ዩኒቨርስቲዎችና የህክምና ባለሙያዎች የተሳተፉበት የተቃውሞ ሰልፍ ተካሄዷል። በተማሪዎቹ ላይ የደረሰውን አካላዊ ጥቃት አውግዘዋል። ተዛማች ጥያቄዎቻቸውን አንስተው መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። በማህበራዊ የመገናኛ አውታሮች ላይ ይሄው ተስተጋብቷል። 
«ይህ የምጥ ጣር መጀመሪያ ነው» ይላሉ ያሬድ ምስጋናው የተባሉ በፌስ ቡክ አስተያየት በመንደርደሪያ ጽሁፋቸው። «ችግሩ እየደረሰ ያለው በኢንተርን ሀኪሞች ብቻ እንዳይመስላችሁ። ሁሉም የጤና ባለሙያ ተባብሮ ይሄን ያረጀና ያፈጀ የጤና ሥርዓት እንዲሻሻል መታገል አለበት። እኛ ሥንኖር ነው። ሌሎችንም የምንረዳው። በወደቀ የህክምና ሥርዓት የሚገነባ ሀገር የለም። አራት ነጥብ።» ብለዋል። 
የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር አማን በቲዊተር ገጻቸው የህክምና ባለሙያዎች ጥያቄዎቻቸውን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ የማቅረብ መብት እንዳላቸው ገልጸው «በአርሲ ዩኒቨርስቲ ኢንተርን ሀኪሞች ላይ በደረሰው ጉዳትና ባነሷቸው ጥያቄዎች ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት የተውጣጣ ቡድን በስፍራው በመገኘት ውይይት አካሂዷል» ብለዋል። ለጠቅ አድርገው በዛው በቲዊተር ገጻቸው «በኢንተርን ሃኪሞች ሰሞኑን በሰላማዊ መንገድ የተነሱ ጥያቄዎችና በተለያዩ የጤና ባለሙያዎች የሚነሱ ጥያቄዎችና በጋራ ለመፍታት ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርና ከጤና ሚኒስቴር በመወጣጣት የተቋቋመው ቡድን በጋራ በመስራት ላይ ይገኛል።» ሲሉ አስፍረዋል።  


ካሳሁን ግርማ የተባሉ ጸሀፊም በፌስ ቡክ «ወዴት ወዴት ክቡር ሚኒስትር?» ሲሉ ጠይቀዋል። ቀጠል አድርገውም «ጥያቄው የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀኪም ነው። የአንድ ባች አልያም ቡድን አስመስሎ መመለስ መሞከር መፍትሄ አይሆንም። ክቡር ሚኒስትር ያስታውሱ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሃኪም ትላንት በየBPR ስብሰባ ትንሽ ብቻ ታገሱን ያሏትን ቃል አክብሮ ብዙ እየታገሶት ነው። የችግርን ስር መሰረት ማስወገድ እንጂ ሲፈነዳ እየጠበቁ ማዳፈን ይዞን ይጠፋል።» ብለዋል። 
ንጉስ ፍቅሬ ትለል «ድርጊቱን የፈጸሙት አካላት ለህግ ቀርበው ተጠያቂ መደረግ አለባቸው። አለበለዚያ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ እጥረት ያለበት አገር ውስጥ ሌላ ተጨማሪ እጥረት ማስከተሉ አይቀሬ ነው» ሲሉ ጽፈዋል። የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር አማንም በቲዊተር ገጻቸው «በአገራችን ካለው የህዝብ ብዛት የጤና ፍላጎትና ካሉን የጤና ተቋማት አንጻር ያሉን የጤና ባለሙያዎች በቂ አይደሉም» ሲሉ ይሄንኑ አረጋግጠዋል። ቅዱስ ነብዩ «እስቲ ይህን መንግስት ተጨማሪ ደመወዝ የምንጠይቅበት ጊዜ ነው? ቢያንስ ዛሬ የአንተን የኑሮ ህልውና ለመታደግ ቻይና ሄዶ እየለመነ ነው። ወያኔኮ 1.4 ትሪሊየን ብር ዕዳ ያለባትን ሀገርኮ ነው ያስረከበችው። ለምን ማሰብ ያቅተናል? ምነው አልበዛም እንዴ 27 ዓመት ወያኔ መናገሪያህን ዘግታ የነበረ ጊዜ የት ነበርክ? እውነቱን ንገረኝ ካልክ ደግሞ የትኛውን ሰብአዊ አገልግሎት ስትሰጡ ነው? እድሜ ለግል ክሊኒክና ሆስፒታል። ሁሉም ነገር ጊዜና ቦታ አለው። ስንቱ ከቤትና ንብረቱ ተፈናቅሎ ባለበት ሀገር የእናንተ ደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ ምን የሚሉት ነው? ልክ ከመሬት ታፍሶ የሚሰጥ ይመስል።»
የአሮሚያና አማራ ክልሎች የህዝብ ለህዝብ መድረክ በአምቦ ከተማ ተካሄዷል። መድረኩ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጠናከር ታስቦ የተዘጋጀ በጋራ ለውጡን ለማስቀጠል እንዲያስችል መሆኑ ተጠቁሟል። በዚሁ መድረክ ላይ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን ጨምሮ ከፍተኛ የፌደራልና ክልል አመራሮች እና ከሁለቱ ክልሎች የተወከሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል። ይሄንኑ የኦሮሚያና አማራ ክልሎች የህዝብ ለህዝብ መድረክ አስመልክቶ በማህበራዊ መገናኛዎች በርካታ አስተያየቶች ተነብበዋል። ከእነዚሁ መሀል ጥቂቶቹን እነሆ። 
አሉላ ዩሃንስ በፌስ ቡክ አስተያየታቸው «ኢትዮጵያ ከ83 ብሄር ብሄረሰቦች እንዲሁም ዘጠኝ ክልል መስተዳደሮች ያቀፈች ሀገር ናት እንጂ ሁለት ክልል መሪዎች ብቻ ሲመቻቸው ተጠራርተው ጠጅ የሚገባበዙባት ሲጣሉ ደግሞ ሰላሟን የሚነሷት ያላቻ ጋብቻ አይደለችም። ከስሩ የታመመ ዛፍ ሁለት ቅጠሎች ብቻ ተወስዶ ቢታከም ቀድመው የሚደርቁት የታከሙት ቅጠሎች ናቸው። ያ እንዳይሆን ደግሞ በሁሉም ህዝብ መካከል የነበረውን ፍቅርና ሰላም እንዲመለስ የጋራ መግባባት እንዲኖር ሀገር አቀፍ ስራዎች መስራት ነው። ሌላውን ባይነቁራኛ እያዩ ተፋቅረናል፣ ታርቀናል፣ የሚለው ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ነው። ለኢትዮጵያ ከሌሎች የተለየ ታምር የሰራላት ብሄር አለ ብዮ አላምንም። አለ ከተባለ ግን ‘አንደኛ ነኝ’ የሚለው ከሃላ እንደሚሰለፍ ራሱም ጠንቅቆ ያውቃል።» ብለዋል። 


ማቴ ካሮ በመድረኩ ላይ የታዘቡትን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል። «እነዚህ ባለስልጣናት እንዲህ አካብደው ሰላም ሲባባሉ የአንድ አገር ልጅ ሳይሆኑ ወንዝ ውቅያኖስ የጋረዳቸው የሩቅ ዓለም ሰው ነው እሚመስለው። ስለዚህ ብዙም ባታራግቡት ህዝብ ለህዝብ የተጣላ የለም። ፖለቲከኞቻችን ካልሆኑ በስተቀር ለዘብ አርጉት።» ብለዋል። 
«እኔ የምለው ከመቼ ወዲህ ነው በኢትዮጵያ ውስጥ ህዝብ ከህዝብ ጋር ተጣልተው የሚያውቁት ይልቅ የምታጣሉትን በስልጣን የምትጣሉት እናንተ ፖለቲከኞች ከኦዴፓ ጀምሮ አዴፓ፣ ህወሀት፣ ደህዴን እና ሌሎች ተቋማዊ ፖለቲከኞች ናችሁ። የምትወክሉትን ህዝብ አዛኝ በመምሰል ለስልጣናችሁ ስትሉ የምታፋጇቸው። ህዝቡን ተውትና እርስ በራሳቹ መጀመሪያ ከመጠላለፍ ፖለቲካ ወጥታችሁ ሁላችሁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተነጋግራቹ የእውነት ለዚህ ሚስኪን አገር ከልባችሁ ስሩላት። የተጣላ ህዝብ የለምና ህዝቡን የተለየ ፊልም እየሰራቹ አታደንቁሩት። ኦሮማራ የማደንዘዣ ስልታችሁን ስለተባነነባችሁ ተውት አትድከሙ።» የዘሩ ቀለጠ አስተያየት ነበር። 
ዛግ ወደም በቲዊተር ገጽ ባሰፈሩት አስተያየት «ክልላዊ መስተዳድሮች ፍትሃዊና ተገቢ የልማት ተግባራትን አብረው የመሸከም ካልቻሉ መኖር የለባቸውም ቋንቋ አቀፍ ትርጉም አልባ ፋይዳቢስ የዘር ክልሎች መክሰም አለባቸው።» በዛው በቲውተር በሌላ ጽሁፋቸውም «ድራማ የሚባል ነገር የለም ይህ የጃዋር ታክቲክ ነው። መቀጨት አለበት። የአብይ መንግስት ለአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ውሃ ማቅረብ ካልቻለ መወገድ አለበት። የኦዴፓ ባለስልጣኖች በቆቃ ግድብ ውሃ አጠቃቀም ላይ ጥናት ቢያደርጉ ህዝባችንን የበለጠ ይጠቅማሉ።» ሲሉ ጽፈዋል። 
በዚህ ሳምንት ኢትዮጵያን ከኤርትራ የሚያገኛኙት ድንበሮች በሙሉ መዘጋታቸው ተሰምቷል። ዛላምበሳ-ሰርሃ ድንበርና ራማ-ክሳድ ዒቃ ድንበር ቀደም ብለው የተዘጉ ሲሆን፤ የሁመራ አማሃጀር ድንበር ባሳለፍነው ሳምንት ቀደም ሲል የተዘጋ ሲሆን የቡሬ አሰብ ድንበር እንዲሁ ተዘግቷል። ድንበሮቹ ለመዘጋታቸውን ይፋዊ መረጃ እንዳልተሰጠ ነው። 
ያንግ ቲ ሃጎስ በፌስ ቡክ አስተያየት የድንበሩን መዘጋት እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን አስፍረዋል።
«ለምን እንደተከፈተና እንዴትስ እንደተከፈተ ለህዝቡ ግልጽ አልነበረም። አሁንም ለምን እንደተዘጋ ለህዝቡ ግልጽ አይደለም። አገር ከአገር መታረቅ ያለበት እንጂ ግለሰብ ከግለሰብ አይደለም» ብለዋል። 
ፊታውራሪ እንዳሻው አለማየሁም «የማይተማመን ባልእንጀራ በየወንዙ ይማማላል አለ አይያ እውነቱን እኮ ነው። ከታረቅን ታርቀናል በሉን፤ ካልታረቅን የእባብ ለእባብ ጨዋታችንን እንጀምር ምንድነው ይሄ ካንገድ በላይ» ሲሉ 
«እንደሚታወቀው በቅርቡ ኢሳያስ የሱዳን ፕሬዚዳንትን በቱርክ የተነሳ ሲተች ነበር። አልበሽር ከስልጣን ከተወገደ በሃላ በድንበሩ በኩል አሽባሪዎች ይገባሉ በሚል ሰበብ ይመስለኛል እንጂ ያ ሁሉ በቅሎ፣ ጋሻ፣ ፈረስ፣ ጋቢ ... ኢሱ ወስዶ ጨክኖ አይዘጋውም።» ኤፍዮኪያ ገብረህይወት አስተያየት ነበር። 


አብደላ መሀመድ «መንገዱ የተዘጋው የኤርትራ መንግስት ከስልጣን ይውረድ ስለተባለ ያንን ለማረጋጋት ታስቦ ላልተወሰነ ቀን ነው የተዘጋው። ኢሳያስ የአልበሽር እጣ ፋንታ እንዳይደርሰው የሰጋ ይመስላል።» የድንበር መዘጋቱ ስጋት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል በአስተያየታቸው።
ጀምስ ባጊን የአብደላ መሀመድን አስተያየትን ያጠናክራሉ «ለኤርትራ እውነቷን ነው መዝጋትም አለበት። ጎረቤት ሀገራት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በአዳዲስ መሪዎች እየተመሩ ስለሆነ ያ ሁኔታ ለኢሳያስ የኩበት ፍም ነው ያ ፍም ወደ ነበልባል እንዳይሆን ስጋት አለው።»
ገነነ ተረፈ «መብታቸው ነው። እንኳን ዘጉት። ፋይዳ ቢስ ወሬ አንፈልግም ሲጀመር በህግ አንቀጽ የተቀመጠ የጋራ ውል በሌለበት የተከፈተ መንገድ ለሁለቱም ሀገራት አይጠቅምም። ዘለቄታም አይኖረውም ባይ ነኝ። ስለዚህ የሀገራችንን የውስጥ ችግሮች የመፍታቱን ስራ ማስቀመም እንጂ ጅቡቲ ለስደተኞች በር ከፈተች ኤርትራ የከፈተችውን በር ዘጋች የሚለው ዜና ወሬ አሁን ላይ ለእኛ አይጠቅመንም። ከጎረቤት ሀገራት ጋር መነካካትና መጨቃጨቅ ሳይሆን የሚያስፈልገን ወዳጅነትን ማጠናከር ብቻ ነው እላለሁ። ቸር እንሰንብት።» ብለው ተሰናብተዋል። 
 

ነጃት ኢብራሂም

ተስፋለም ወልደየስ

Audios and videos on the topic