የሚያዝያ 25 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 03.05.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የሚያዝያ 25 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች ኦልትራፎርድ ውስጥ ተምመው በመግባት ተቃውሞዋቸውን ገልጠዋል። ትናንት ከሊቨርፑል ጋር የነበረው ግጥሚያም ተሰርዟል። አያክስ አምስተርዳም የውድርር ዘመኑ ሊጠናቀቅ ሦስት ጨዋታዎች እየቀሩት ከወዲሁ የሆላንድ ኤሬዲቪሴ ዋንጫ ማንሳቱን አረጋግጧል። ለ35ኛ ጊዜ ነው ለዚህ አይነቱ ድል ሲበቃ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:54

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ከ56 ሰአታት በላይ መዝለቅ ያልቻለው የአውሮጳ ሱፐር ሊግ ሙከራ ክሽፈት የአውሮጳ ቡድኖች ላይ ጣጣ አስከትሏል። የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች ኦልትራፎርድ ውስጥ ተምመው በመግባት ተቃውሞዋቸውን ገልጠዋል። ትናንት ከሊቨርፑል ጋር የነበረው ግጥሚያም ተሰርዟል። አያክስ አምስተርዳም የውድርር ዘመኑ ሊጠናቀቅ ሦስት ጨዋታዎች እየቀሩት ከወዲሁ የሆላንድ ኤሬዲቪሴ ዋንጫ ማንሳቱን አረጋግጧል። ለ35ኛ ጊዜ ነው ለዚህ አይነቱ ድል ሲበቃ። ሮሜሉ ሉካኩ በበኩሉ ሴሪ አው ሳይጠናቀቅ ኢንተር ሚላን ዋንጫ እንዲያነሳ አስችሏል። በስፔን ላሊጋ አትሌቲኮ ማድሪድ፣ ሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና አንገት ለአንገት ተያይዘዋል። ላሊጋው ሊጠናቀቅ አራት ዙር ጨዋታዎች እየቀሩት አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሴቪያም በቅርብ ርቀት ይከተላል። በጀርመን እግር ኳስ ማኅበር (DFB-Pokal) ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ፉክክር የሁለተኛ ዲቪዚዮኑ ኪይልን ቅዳሜ ዕለት 5 ለ0 የረታው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ለፍጻሜው ከላይፕትሲሽ ጋር ይፋለማል። 

ፕሬሚየር ሊግ
ኦልትራፎርድ ስታዲየም ትናንት የእግር ኳስ ሳይሆን የተቃውሞ ሰልፈኞችን አድማ አስተናግዶ ቆይቷል። የተቆጡ ደጋፊዎቹ ወደ ስታዲየሙ ጥሰው በመግባት በሚንቦለቀው ጢስ መሀል እየዘመሩ ሲፈክሩም ውለዋል። የግላሰር ቤተሰብ ከማንቸስተር ዩናይትድ ይውጣ የሚሉ እና ሌሎች ጥያቄዎችንም አስተጋብተዋል። 

የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች «የግላሰር ቤተሰብ ይውጣ» የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰሙ ዘመናዊ ችቦዎችን ለኩሰው የማንቸስተር ዩናይትድ ባሕላዊ መለያ የኾነውን ቢጫ እና አረንጓዴ ቀለም በጢስ እንዲቡለቆለቅ አድርገዋል። ወደ ስታዲየሙ ሜዳ ከሁለት መቶ የማያንሱ ደጋፊዎች ገብተው ተቃውሞዋቸውን ሲገልጡ ከውጪ በሺህዎች የሚቆጠሩት ድምጻቸውን አሰምተዋል። 

የደጋፊዎቹ ቁጣ ሰበብ ማንቸስተር ዩናይትድን የሚመሩት አሜሪካውያኑ የግላሰር ቤተሰቦች ቡድኑን ለጥቅማቸው ሲሉ ወደማይሆን አቅጣጫ መርተውታል የሚል ነው። በዋናነት ደግሞ ባለፉት ሳምንታት የበርካቶች መነጋገሪያ የነበረው የአውሮጳ ሱፐር ሊግ ምሥረታ ዕቅድ ውስጥ ማንቸስተር ዩናይትድ ተሳታፊ መሆኑ ነው። በእርግጥ ሱፐር ሊጉ ከ56 ሰአታት በላይ ሳይዘልቅ ተበትኗል። ከእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ዩናይትድን ጨምሮ ስድስት ቡድኖች ተሳታፊ ነበሩ። ከበርካታ አቅጣጫ ብርቱ ተቃውሞ ሲከሰት በኋላ ላይ እነሱም ራሳቸውን ከሱፐር ሊጉ አግልለው ሱፐር ሊጉም በእንጭጩ ተቀጭቷል።

የአውሮጳ ሱፐር ሊግ የአውሮጳ ጥቂት ግን ደግሞ ምርጥ ቡድኖችን ይዞ ከአውሮጳ የእግር ኳስ ስርዓት በተገነጠለ መልኩ ለመንቀሳቀስ ዓልሞ ነበር። ብዙዎች በተለይ ደግሞ ደጋፊዎች ጥቂት ለገንዘብ የቆሙ ስግብግቦች ለረዥም ጊዜ የዘለቀውን የእግር ኳስ ባህል ሊያዛቡ ነው፤ ዓላማቸው ገንዘብ ብቻ ነው በሚል በጥብቅ ተችተዋል። የአውሮጳም ሆነ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበራት ይመሰረታል ተብሎ በነበረው «ሱፐር ሊግ» ተሳታፊ የሆኑ ቡድኖች ላይ ከባድ ቅጣት እንዲሚያሳርፉ ዝተው ነበር። ለወራት በዝግ እና በምሥጢር ሲማከሩ የነበሩት ባለሐብቶች እና የተወሰኑ የእግር ኳስ ባለሞያዎች በስተመጨረሻ እጃቸውን ሰጥተው ይመሰረታል የተባለውም ሊግ በእንጭቹ ተቀጭቷል። 

የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች ኦልትራፎርድ ስታዲየማቸውን በብርቱ ተቃውሞ ያናወጡት የቡድኑ ባለቤት ቢሊዬነሩ ጆዬል ግላሰር በስተመጨረሻ ይቅርታ የጠየቁበት የሱፐር ሊግ ጉዳይ ነበር። የማንቸስተር ዩናይትድን ባህል ባለማስጠበቄ ይቅርታ ብለው ቡድናቸውን ከሱፐር ሊግ እንዲወጣ ያደረጉት ግላሰር አሁን ከደጋፊዎች ሌላ ጥያቄ ቀርቦባቸዋል። ከቡድኑ ባለቤቶች ዋነኛ ድርሻውን የሚይዘው የግላሰር ቤተሰብ ላይ ላለፉት 16 ዓመታት ተቃውሞ ሲደርስበት ከርሟል። የ«ሱፐር ሊጉ» ጉዳይ ግን የመጨረሻዋ ሰበዝ ሆናለች። 

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፦ ለትናንት ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የማንቸስተር ዩናይትድ እና የሊቨርፑል ወሳኝ ጨዋታም ኦልትራፎርድ ውስጥ ጥሰው በገቡ የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች ተቃውሞ ምክንያት ተሰርዟል። በፕሬሚየር ሊጉ 67 ነጥብ ይዞ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ ትናንት ከሊቨርፑል ጋር ተጫውቶ ቢሸነፍ ኖሮ ማንቸስተር ሲቲ 4 ዙር ግጥሚያዎች እየቀሩት ዋንጫውን መውሰዱን ያረጋግጥ ነበር።  ማንቸስተር ሲቲ በ80 ነጥብ ፕሬሚየር ሊጉን እየመራ ይገኛል። 54 ነጥብ ይዞ በ7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሊቨርፑልም በሚቀጥለው የውድድር ዘመን ለሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ለመሆን ዕድሉን ያሰፋ ነበር።  ላይስተር ሲቲ በ63 ነጥብ፤ ቸልሲ በ61 ነጥብ ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። 

ኤሬዲቪሴ 
አያክስ አምስተርዳም ለ35ኛ ጊዜ የሆላንድ ኤሬዲቪሴ ዋንጫ ማንሳቱን አረጋግጧል። ዘንድሮ የዋንጫ ባለቤት መሆኑን ያረጋገጠው የውድርር ዘመኑ ሊጠናቀቅ ሦስት ጨዋታዎች እየቀሩት ከወዲሁ ነው። አያክስ አምስተርዳም የዋንጫ ባለቤት የሆነው 16ኛ ደረጃ ላይ ያለውን ኤመንን 4 ለ0 ባሸነፈበት 31ኛው ዙር ግጥሚያ ነው። አያክስ የዋንጫው ባለቤት መሆኑን ሲያረጋግጥ በመሪነቱ ፒኤስቪ አይንድሆቨንን በ14 ነጥብ እና በ37 ግቦች ርቆ ነው። 

ሴሪ ኣ
ሮሜሉ ሉካኩ ኢንተር ሚላን ለ11 ዓመታት ሲጠብቀው የነበረውን ሕልም ዕውን አድርጓል።  በለኢንተር ሚላን ቆይታው ሮሜሉ ሉካኩ ለ63 ጊዜያት ተሰልፎ 44 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። አታላንታ ትናንት ከሳሶሉ ጋር ባደረገው ግጥሚያ ኢንተር ሚላንን የጨዋታ ዘመኑ ሳያልቅ ዋንጫውን መውሰዱን እንዳያረጋግጥ ለማድረግ ማሸነፍ ነበረበረበት፤ ትናንት ግን አንድ እኩል ነው የተለያየው። ኢንተር ሚላን የዛሬ ሁለት ዓመት የጨዋታ ዘመኑን ሲያጠናቅቅ ከተቀናቃኙ ጁቬንቱስ በ21 ነጥብ ርቆ ነበር። ሮሜሉ ሉካኩ እና አሰልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ ወደ ቡድኑ መምጣታቸው ግን ያን ቀይሮታል። ባለፈው የጨዋታ ዘመን ግን ከጁቬንቱስ በአንድ ነጥብ ብቻ ተበልጠው ነው በሁለተኛነት ያጠናቀቁት። አሁን በአንቶኒዮ ኮንቴ 3፣5፣2 አሰላለፍ ሮሜሉ ሉካኩን ከፊት ላውታሮ ማርቲኔዝ ጋር በማጣመር የቀረጹት ሙከራ ፍሬ አፍርቶላቸዋል። ሮሜሉ ሉካኩ በቀድሞ ቡድኖቹ ኤቨርተን እና ማንቸስተር ዩናይትድ 7 የአጥቂ መስመሩን ለብቻው ነበር እንዲወጣ የሚሰለፈው። በኢንተር ሚላን ግን ያ ተቀይሮ ስኬታማ ኾኗል። 

ላሊጋ
በስፔን ላሊጋ አትሌቲኮ ማድሪድ፣ ሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና ዋንጫ ለማንሳት አንገት ለአንገት ተያይዘዋል። መሪው አትሌቲኮ ማድሪድ በ76 ነጥቡ ተከታዮቹ ሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎናል የሚበልጣቸው በ2 ነጥብ ብቻ ነው። ላሊጋው ሊጠናቀቅ አራት ዙር ጨዋታዎች እየቀሩት አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሴቪያም በቅርብ ርቀት ይከተላል። 70 ነጥብ አለው። አርጀንቲናዊው የኳስ ጥበበኛ ሊዮኔል ሜሲ በ57ኛው እና 69ኛው ደቂቃ ላይ ሁለት ግቦችን አስቆጥሩ አንድ ፍጹም ቅጣት ምት ስቷል። ሌላኛው 63ኛው ደቂቃ ላይ የተቆጠረው ግብ የአንቷን ግሪንዝማን ነው። ባርሴሎና ትናንት በ50 ደቂቃ ላይ በተቆጠረበት ግብ በቫሌንሺያ እየተመራ ቆይቶ ነበር ከኋላ በመነሳት ወሳኝ ድል ያስመዘገበው። ከመሪው አትሌቲኮ ማድሪድ የሚበለጠውም በሁለት ነጥብ ብቻ ነው። 

የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር
በጀርመን እግር ኳስ ማኅበር ዋንጫ ቦሩስያ ዶርትሙንድ እና ላይፕትሲሽ ለፍጻሜ ደርሰዋል፤ ዋና ከተማዪቱ ቤርሊን ውስጥ ይጋጠማሉ። በቡንደስሊጋው የሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ላይፕትሲሽ ቬርደር ብሬመንን 2 ለ1 ረትቶ ነው ለፍጻሜው የደረሰው።  አምስተኛ ደረጃ ላይ የሰፈረው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ደግሞ በግማሽ ፍጻሜው ከሁለተኛ ዲቪዚዮን የመጣው ሆልሽታይን ኪዬልን 5 ለ0 አንኮታኩቷል። በቦሩስያ ዶርትሙንድ እና ላይፕትሲሽ መካከል የፍጻሜው ግጥሚያ የፊታችን ሐሙስ ሳምንት ቤርሊን ከተማ ውስጥ ቀጠሮ ተይዞለታል። 

ሻምፒዮንስ ሊግ
የሻምፒዮንስ ሊግ የመልስ ጨዋታዎች ነገ እና ከነገ በስትያ ምሽት ላይ ይከናወናሉ። በነገው ዕለት የፈረንሳዩ ፓሪ ሳን ጃርሞ ሽንፈቱን ለመበቀል ማንቸስተር ሲቲን ይጋጠማል። በመጀመሪያው ግጥሚያ ማንቸስተር ሲቲ ፓሪ ሳን ጃርሞን ያሸነፈው 2 ለ1 ነበር። የፓሪ ሳን ጃርሞው አሰልጣኝ ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ ቡድናቸው ባለፈው ግጥሚያ የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ጨዋታውን ተቆጣጥሮ ሁሉን ንገር ያጣበትን ምክንያት በጥልቀት መመርመራቸው አይቀርም። ምን ይዘው እንደሚመጡም በነገው እለት መመልከት ነው። 

ፎርሙላ አንድ

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ብሪታኒያዊው የመርሴዲስ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን በፖርቹጊዝ ግራንድ ፕሪ የመኪና ሽቅድምድም ትናንት ድል ተቀዳጅቷል። ሌዊስ ሐሚልተን ከሌላኛው የመርሴዲስ ቡድን አባሉ ቫለሪ ቦታስ እና ከሬድ ቡሉ አሽከርካሪ ማክስ ፈርሽታፐን ብርቱ ፉክክር ቢገጥመውም ከ66 ዙሩ ሽቅድምድም 34ቱን በቀዳሚነት ተወጥቶ ነው ለድል የበቃው። እስካሁን በተከናወኑ የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድሞች ሌዊስ ሐሚልተን እስካሁን 69 ነጥብ መሰብሰብ ችሏል። በትናንቱ ውድድር በሁለተኛነት ያጠናቀቀው ማክስ ፈርሽታፐን በአጠቃላይ 61 ነጥብ ሌዊስን ይከተላል። ትናንት ሦስተኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው ቫለሪ ቦታስ አጠቃላይ 32 ነጥብ ይዞ ደረጃው አራተኛ ነው። የማክላረኑ አሽከርካሪ ላንዶ ኖሪስ ትናንት የሬድ ቡሉ ሠርጂ ዮፔሬዝን ተከትሎ የአምስተኛ ደረጃ በመያዝ ነው ውድድሩን ያገባደደው። ሌዊስ ሐሚልተን በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ታሪክ እስካሁን ለሰባት ጊዜያት ዋንጫዎችን ማሸነፍ የቻለ የዓለማችን ብርቱ አሽከርካሪ ነው።  ገና ብዙ አስደማሚ ውጤቶችን የማስመዝገብ ብቃት እንዳለውም ከወዲሁ እያስመሰከረ ነው። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic