የሚውኒኩ የፀጥታ ጉባኤ ስብሰባ በአዲስ አበባ | አፍሪቃ | DW | 14.04.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የሚውኒኩ የፀጥታ ጉባኤ ስብሰባ በአዲስ አበባ

የሚውኒክ የዓለም የፀጥታ ጉባኤ በአፍሪቃ የመጀመሪያውን ስብሰባ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ጀመረ። በዚህ ሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባዔ ላይ የተሳተፉት ወደ 60 የሚጠጉ ከአፍሪቃ፣ አውሮጳ እና ከዩኤስ አሜሪካ የተውጣጡ ልዑካን ወሳኝ በሚባሉ የዓለምና የአካባቢዉ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ በመምከር ላይ ይገኛሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:17

የፀጥታ ጉባኤ

በአዲስ አበባ የሁለት ቀናት ስብሰባውን የጀመረው የሚውኒኩ የፀጥታ ጉባዔ በምሥራቃዊ እና ሰሜናዊ አፍሪቃ ሽብርተኝነትን እና አዘውትሮ በሃይማኖት ስም የሚፈፀመውን የአክራሪዎች ጥቃት በጋራ ለመታገሉ ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶዋል። በአፍሪቃ የሚካሄድ ሽብር ከአህጉሩ አልፎ ለአውሮጳም ስጋት ስለሚደቅን የፅንፈኞችን ጥቃት ማስቆም ስለሚቻልበት ሁኔታ ከአፍሪቃውያን ጋር በአፍሪቃ እየተገናኙ መወያየት በጣም አስፈላጊ ነው። ለዚሁ ስብሰባም አዲስ አበባ የተመረጠችበትን ምክንያት ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው ጉባዔውን የሚመሩት ጀርመናዊው ቮልፍጋንግ ኢሽንገር ሲያስረዱ፣
«በመጀመሪያ አዲስ አበባ የአፍሪቃ ኅብረት መቀመጫ ናት። አፍሪቃውያን መንግሥታት በጋራ ርምጃ የሚወስዱበት አቅማቸው ሊጠናከር እና በሚገባ የሚሠራ የፀጥታ አካል ሊኖራቸው ይገባል ብለን እናምናለን። የጀርመን መንግሥት ይህን ዓይነቱን ጥረት፣ የጣና መድረክን ጭምር ጠንክሮ ሲደግፍ ቆይቶዋል። »


ለአፍሪቃ እና በአህጉሩ ላለው ፀጥታ ቅድሚያ የሰጠው የጉባዔው አጀንዳ በሁለት ጉዳዮች ላይማትኮሩን ኢሺንገር አስረድተዋል።
« የመጀመሪያው ሽበርተኝነት ነው። ብዙው የአውሮጳ ህዝብ ለምሳሌ «ቦኮ ሀራም» አፍሪቃ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የገደላቸው ሰዎች ቁጥር፤ ራሱን «እስላማዊ መንግሥት» ብሎ የሚጠራው ቡድን በኢራቅ፣ በሶርያ እና በሌሎች ያካባቢው ሃገራት ከገደላችው እንደሚበልጥ አያውቅም። በመሆኑም፣ የአክራሪነቱ ጥያቄ፣ ሽብርተኝነትን የሚያበረታቱ መንስዔዎችን አፍሪቃ እና አውሮጳ በጋራ መታገል ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው። »
የሶማልያ አማፂ ቡድን አሸባብ ከአንድ ዓመት በፊት በምሥራቅ ኬንያ የጋሪሳ ከተማ በጣለው ጥቃት 148 የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን፣ ወይም፣ ባለፈው ሰኞ በሶማልያ መዲና ሞቃዲሾ በመኪና ላይ ባጠመደው ቦምብ ቢያንስ የአምስት ሰዎችን ሕይወት የገደለበት ጥቃት ሲታሰብ የፀጥታው ጉባዔ በአፍሪቃ ምድር መደረጉን አስፈላጊ ያደርገዋል።
ጀርመን ካለፉት ጥቂት ጊዚያት ወዲህ አፍሪቃውያት የፀጥታ ኃይላትን ለማሰልጠን ማሊን ወደመሳሰሉ ሃገራት ተጨማሪ ወታደሮች መላክ መጀመሯ ያለምክንያት አለመሆኑን ኢሺንገር አስረድተዋል። እንደ ኢሺንገር ገለጻ፣ በአፍሪቃ የሚታይ የሽብርተኝነት አደጋ ፣ እንዲሁም፣ ሽብርተኝነትን ወደሌሎች አገሮች የማስፋፋቱ አደጋ አውሮጳን በቀጥታ የሚነካ ችግር ነው።
የጉባዔው መሪ ጀርመናዊው ቮልፍጋንግ ኢሽንገር ለዶይቸ ቬለ እንደገለጹት፣ ወጣት ሕዝቧ ፈጥኖ በማደግ ላይ ካለባት ከአፍሪቃ በወቅቱ የሚታየው ግዙፍ ፍልሰት ጉባዔው በተለይ ያተኮርበት ሌላው ርዕስ ነው።


« ሁለተኛው የስደተኞች ጉዳይ ነው። ምንም እንኳን በአሁኑ ጊዜ አውሮጳ በተለይ ከሶርያ በሚመጡ ስደተኞች ላይ ብታተኩርም፣ በሚቀጥሉት ዓመታት እና አ ሰርተ ዓመታት ቀውስ ካለባቸው የአፍሪቃ አካባቢዎች ፣ በተለይ በዚያ ያለውን ፈጣን የሕዝብ ቁጥር እና የኤኮኖሚ እድሎችን ስንመለከት፣ ወደ አውሮጳ የሚሰደዱት ሰዎች ቁጥር ከፍ ሊል እንደሚችል ልናውቅ ይገባል። »
አፍሪቃ የያዘችው ዓለም አቀፍ ትርጓሜ ከፍተኛ በመሆኑ በአፍሪቃ እና በአውሮጳ መካከል ፀጥታን የሚመለከተው ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊው እና ኤኮኖሚያዊው ውይይትም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ኢሺንገር አስታውቀዋል። በአዲስ አበባው ጉባዔ ከሚሳተፉት መካከል የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚደንት ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ፣ የተመድ ልዩ ልዑክ አዳማ ዲንግ፣ የቀድሞ የጀርመን ፕሬዚደንት ሆርስት ከለር፣ የጀርመን መራሒተ መንግሥት የአፍሪቃ ተጠሪ ጉንተር ኑክ ፣ የቀድሞው የተመድ ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን ይገኙባቸዋል።

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic