የሚንስትሯ የስራ መልቀቂያ እና የክልሎች የመንግስት ምስረታ  | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 01.10.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የሚንስትሯ የስራ መልቀቂያ እና የክልሎች የመንግስት ምስረታ 

አስተያየት ሰጭዋ «አዳዲሶቹ የክልል መንግስታት የጦርነት ወሬ ጠፍቶ ከገባንበት የሞትና የመፈናቀል ወሬ የሚያወጡን ከሆነ ጥሩ ነው።ያለዚያ አዲስ መንግስት አሮጌ መከራ ካሸከመን ዋጋ የለውም ።»ብለዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:25

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

 

የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚንስትር የስራ መልቀቂያ፣የኦሮሚያ የአዲስ አበባ እና የአማራ የክልሎች የመንግስት ምስረታ እንዲሁም የአማራ ብሄራዊ ክልል መንግስት አዲስ ርዕሰ መስተዳደር ሹመት በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርከት ያሉ አስተያየቶች የተሰጡባቸው ጉዳዮች ነበሩ።አንዳች መነጋገሪያ የማያጡት የማኅበራዊ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች  በዚህ ሳምንትም  የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚንስትር ፊልሰን አብዱላሂ  የስራ  መልቀቂያ ለጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ አህመድ ማስገባታቸውን በይፋዊ የፌስ ቡክ ገፃቸው መግለፃቸው ካነጋገሩ ጉዳዮች አንዱ  ነበር።ሚንስትሯ "በሕሊናዬ ላይ ከባድ ጫና በሚያሳድሩ" ባሏቸው የግል ጉዳዮች  ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ  የወሰኑት ደግሞ፤ በአዲሱ የመንግስት ምስረታ ዋዜማ ላይ በመሆኑ ብዙዎች የየራሳቸውን ምክንያት በማቅረብ  አስተያየት ሰጥተዋል። 
ዮሴፍ ፍሪደም«እንኳን በጊዜ ለቀቁ በአሁኑ ጊዜ የህፃናትና የሴቶችን ጉዳይ ከመምራት የበለጠ  ናላ የሚያዞር ነገር የለም።» ሲሉ፤ በሻህ ሀይሉ ደግሞ «ወይ ጊዜ የሚንስትር መልቀቂያ በፌስ ቡክ።መልቀቂያው የቀረበው ለኢትዮጵያ ህዝብ ነው ወይስ ለጠቅላይ ሚንስትሩ?»  ሲሉ ጠይቀዋል። 
ትግስት መድፉ «ስልጣንን በፍላጎት መልቀቅ መለመዱ ጥሩ ነው፡፡»ብለዋል ፤ አለማየሁ ገመዳ በቲዩተር ገፃቸው ደግሞ «ከመንግስት ስልጣን በፈቃድ መልቀቅ ምን ጊዜም መበረታታት ያለበት ነው።ከነስህተታቸው ሃለፊነት ላይ ያሉ ባለስልጣናት  ከፊልሳን  መማር አለባቸው።»በማለት በእንግሊዝኛ ፅፈዋል።


ጄጄ ጃክሰን በሚል ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ «ከአሜሪካ የጉዞ ማዕቀብ በጊዜ አመለጡ ማለት ነው?»የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
ጎቤ አሰፋ በበኩላቸው «ሲሾሙ ሳንሰማና ሳናውቃቸው መልቀቂያ አስገቡ የሚለውን የግብፅ ድረ- ገፆች  ሳይቀር ሌላ መልክ ሰጡት።ያበሳጫል።»ሲሉ፤
ኢክረም አላዊ «ምን ችግር አለው። በሌላም ውጤታማ በምትሆንበት ቦታ ብትሠራ ለሀገሯ ነዉ። ኢትዮጵያ የሠው ችግር የለባት። የአሥተሣሠብ እንጅ»የሚል ሀሳብ ሰጥተዋል።
«እውነቷን ነው ምን ታድርግ። የሴቶች  ህፃናት እና ወጣቶች  ሚኒስትር ሆና የሴት እና የህፃናትን መደፈርን  ከመስማት የበለጠ ምን የሚከብድ ነገር አለ ።» ያሉት ደግሞ ትዝታ ጌታሁን ናቸው።
ሶሎሞን በላቸውም «እውነት ነው።እንዴት ሆነው  ስልጣኑ ላይ ይቆዩ ። ይህ  ጉድ እየተሰማ ።»በማለት የላይኛውን ሀሳብ አጠናክረዋል።
ልመንህ ወንድሙ ግን በሃሳቡ የተስማሙ አይመስሉም «ላለፉት 2 ዓመታት በመላ ሀገሪቱ በሴቶች እና ህፃናት ላይ ያ ሁሉ ተዘርዝሮ የማያልቅ ግፍ ሲፈፀም ቢያንስ አንድ ቀን እንኳን ወደ ፊት መጥተው ድምፃቸውን  አሰምተው ነበር ወይ?የሚለው  ነው ዋናው ጥያቄ።»ብለዋል።
አቡ ከዲጃ ተውፊቅ«ደግ አረገች ስንቶች ናቸው ወይ የራሳቸውን ህሊና ነፃ አላደረጉ ወይ ለወገናቸው ድምፅ አይሆኑ።ኸይር ይግጠምሽ አቦ።»የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
ታሪኩ አስፋው ረዘም ካለው ፅሁፋቸው ውስጥ ደግሞ «በአንድ አቅጣጫ በፖለቲካ ብቻ ነገሮችን እየመነዘርን እየተረጎምን ለምን ግለሰቦችን እንደምናብጠለጥል፤ ማህበረሰብን ለምን እንደምናተራምስ ሊገባኝ አልቻለም። ምክንያቱ ምንም ይሁን ስልጣኔን በገዛ ፈቃዴ ለመልቀቅ ወስኛለሁና ተረከቡኝ አለች ።ምኑ ላይ ነው ፖለቲካ? ማንስ ተጎዳ ?የእህታችን ውሳኔ ሊከበር፣ ሊደነቅና ለሷም ክብር ሊሰጣት ይገባል ። ርስት ይመስል ስልጣን ላይ ሙጭጭ ማለት ይብቃ ።»በማለት ፅፈዋል።
ሌላው በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ የሆነው ጉዳይ የክልሎች የመንግስት ምስረታ ነበር። በሳምንቱ መጀመሪያ በኦሮሚያ ክልል የተጀመረው የመንግስት ምስረታና የካብኔ አባላትን የመምረጥ ስራ በሌሎች ክልሎችም ቀጥሎ ነበር የሰነበተው። ይህንን  ተከትሎም ብዙዎች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በአዲሱ የመንግስት ምስረታ ተስፋና ስጋታቸውን አንፀባርቀዋል።


እታፈራሁ የማርያም ልጅ«የመንግስት ሹመት የአገልጋይነት የኃላፊነት ሸክም ነው፣ በተለይ ከፍ ያለ ሹመት ከፍ ያለ ዕዳ ነው።ዕዳውን በአግባቡ ተወጡ።» ብለዋል።
ሜላት ዓለሙ «በጣም ጥሩ ነው ግን የሴቶችን አካታችነት ተረስቷል።ምክንያቱም ብቁ የሴት መሪዎች አሉ።»ሲሉ፤ ሀሲና ከድርም «የሴቶች ተሳትፎ እንዲህ ዝቅተኛ የሆነው እውነት ለቦታው የሚመጥኑ ብቁ ሴቶች ጠፍተው ነው? ይሁና።»ብለዋል።
መሲ የእናቷ ልጅ በሚል ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ «አዳዲሶቹ የክልል መንግስታት የጦርነት ወሬ ጠፍቶ ከገባንበት የሞትና የመፈናቀል ወሬ የሚያወጡን ከሆነ ጥሩ ነው።ያለዚያ አዲስ መንግስት አሮጌ መከራ ካሸከመን ዋጋ የለውም ።»የሚል ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የአዲስ አበባ አስተዳደርን  ጨምሮ በአንድዳንድ የክልል መንግስታት ሹመት  የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት መካተታቸውን አንዳንዶች በጥርጣሬ አንዳንዶች ደግሞ በአዎንታዊ መልኩ ተመልክተውታል።
አስሬ ጩፋ «ኢትዮጵያ የሁሉም ሀገር ሁሉም አስተሳሰቦች የሚስተናገዱባት ሀገር ትሁን!!ይቀጥላል ብለን እንጠብቃለን፡፡»ሲሉ፤ ያሲን ሙሀመድ ግን  «ስልጣን በመስጠት አፋቸውን ለማፈን ነው የተቀዋሚ ደጋፊዎችስ  ብልጽግናን ይደግፉ የብልጽግና ደጋፊወችስ? ብልጽግናን መርጠው ባልመረጧቸው ሲመሩ እንደት ነው ነገሩ። ይሄ ጠንካራ ተፎካካሪ እንዳይኖር የመዋጫ ዘዴ ነው።»በማለት የተቃዋሚዎችን ሹመት ተችተዋል። አልዓዛር በየነ ግን «ይህ አካታች የሆነ የፖለቲካ ውክልና የሚያበረታታና አውንታዊ  ርምጃ ነው።»በማለት ርምጃውን አድንቀዋል።
እያሱ ሀቤቦም «ኢትዮጵያዉያን በአገራቸዉ ጉዳይ በአመለካከታቸዉና በብሔራቸዉ የተነሳ ባይተዋር የማይሆኑበትን ዘመን ጅምር እያየን ነው። ተመስገን።»ብለዋል።


አስቴር ወገኔ ግን «እንዳያማህ ጥራው ነው።የይስሙላ ነው።»ብለውታል ሹመቱን።
አዳዲሶቹ የአዲስ አበባ ሴት የምክር ቤት አበላት ለብሰው የታዩት ጥቁር በቢጫ ልብስም በዙሁ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ብዙ ትችት ያስተናገደ ነበር።
ከዚሁ ከክልሎች የመንግስት ምስረታ ጋር ተያይዞ ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ አዲሱ የአማራ ክልል ምክር ቤት በአቶ  አገኘሁ ተሻገር ምትክ  የክልሉን ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ይልቃል ከፋለን ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ መሾሙ ነበር። አዲሱ ርዕሰ መስተዳድር ባደረጉት ንግግርም  የክልሉ ህዝብ  እየሞተ፣ እየተራበና ሀብት ንብረቱን ትቶ እየተፈናቀለ ባለበት ወቅት መሾማቸው ቢያሳዝናቸውም፤ ህዝቡን ነጻ ለማውጣት  እንደሚሰሩ ገልፀዋል።
ተዋቸው ሙላቴ«ብዙ ተግባር አልቫ ወሬዎችን ከመከራ ጋር ያስተናገደ ክልል ነውና የተረከብከው በርታ።» ሲሉ፤ ማሜ ማሜ በሚል ስም የሰፈረው አስተያየት «በሶስት ዓመት ውስጥ 5 መሪ የቀያየረ ጉደኛ ክልል።»ብለዋል ። ሀረግ አንማው «ጥያቄው ለምን ተቀየረ ነው።በመጀመሪያ መሪዎቻችን ተገደሉ መተካት ነበረበት ተተኩ።ሲቀጥል አማራን መሪ ለማሳጣት የሚደረገው ጥረት ከዚህ ይጀምራል የተሾመውን ሁሉ በማንቋሸሽ የትም አይደረስም።ጥፋት እንኳ ቢኖር መደጋገፍ እንጅ በዚህ ወቅት ጣት መጠቋቆም የትም አያደርስም።»የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።


ነፃነት ታምር «መልካም የስራ ዘመን ይሁንልዎ።የአማራንና የትግራይን ህዝቦች ከፍጅት ይታደጓቸው።»ሲሉ፤ ዉቢት ይስማው በበኩላቸው «ሁለቱን ህዝቦች ለመታደግ ።የዚያኛው መንደር ሰዎች ልብ ካልገዙ በቀር እሳቸው ብቻቸውን የሚሰሩት ስራ አይደለም»የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
ያሬድ አራጌ«ያው ነው የግንቦት 20 ፍሬ።»ሲሉ፤ ገለታ አስፋው ደግሞ «ማንም ይሾም ማን ብቻ ለክልሉ ህዝብ አሳቢና ተቆርቋሪ ይሁን። የህዝብን ችግር የሚፈቱ የአማራን ህዝብ ከሞትና ከመፈናቀል የሚያድኑ፣ ህጋዊ በሆነ መንገድ የክልሉን ጥቅም የሚያስከብሩ፣ የተናገሩትን የሚተገብሩ፣ ለህዝብና ለህዝብ ብቻ የቆሙ እንዲሁም ያልተመቻቸውን በግልፅ የሚቃወሙም ያድርጋቸው።»ብለዋል።
ታረቀኝ አምባው ደግሞ «ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም።»የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል። አባይነው ተስፋ«አሁን በዚህ ወቅት ህዝባችን ከገባበት ስቃይ እንዴት እናውጣው?ደግፈንም ቢሆን ብቃት ያለው መሪ እንዴት እናውጣ?።ይህን ማለት ሲገባ።የመጣውን ሁሉ መተቸት እና መለያየት አይጠቅመንም።» ብለዋል።
«መሾም ጥሩ ነው። የእናንተን ሹመት ልዩ የሚያደርገው ሲሶ የሚጠጋው የአማራ ክፍል በህወሃት ቀንበር ስር በወደቀበት ጊዜ በመሆኑ የቤት ስራችሁ ከልማትና ከእኩል ተጠቃሚነት ባሻገር መከራ የከበበውን የአማራ ህዝብ ነፃ ማውጣት ቀዳሚ ተግባራችሁ ሊሆን ይገባል።» ያሉት ደግሞ መንገሻ ሲሳይ ናቸው።


ፀሀይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic