የሚሰባበረው አጥንት ድምፅ | ባህል | DW | 17.02.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የሚሰባበረው አጥንት ድምፅ

ስለሴት ህፃናት ወታደሮች የሚያወሳው ይህ ፅሁፈ-ተውኔት ካናዳ ውስጥ ነው የተፃፈው፤ ሱዛኔ ሌቤው በተባለች ፀሀፌ-ተውኔት። ቤልጂየም ውስጥ ለመድረክ ከበቃ በኋላ አሁን በምስራቅ አፍሪቃ ሀገራት ለእይታ በመዞር ላይ ነው።

ተዋናይት ዲዮፕ

«የሚሰባበረው አጥንት ድምፅ» ተዋናይት ዲዮፕ

መድረኩ ላይ ሶስት ተዋንያን በአንድ ተዋጊ ቡድን  በግዳጅ ለውትድርና የተመለመሉ ህፃናት ሴቶችን መከራ ያሳያሉ።  ታሪኩ የሚከናወነው ዓለም ላይ የሆነ ቦታ ነው። ከፍተኛ እንግልት እና መከራ በበዛበት የዓለማችን አንዱ ክፍል።  እናም ተደራሲያኑ ተውኔቱ ውስጥ የታዳጊዋ ኤሊካን የህይወት ውጣ ውረድና መከራ ሲመለከቱ ወዲያውኑ ከራሳቸው የህይወት ተመክሮ ጋር እንዲጋፈጡ ያስገድዳቸዋል ። ታዳጊዋ ኤሊካ ከቤተሰቦቿ  በኃይል ተነጥላ በግዳጅ ወታደርነት የተሰማራችው በለጋ እድሜዋ ነበር። ከሶስት ዓመታት  የመከራ ቆይታ በኋላ ግን ከአንዲት እስረኛ ጋር ያመልጣሉ። ያሳለፉት ህይወት ምን ያህል በሰቆቃ የተሞላ እንደነበር በሽሽት ላይ ሳሉ የሚታይባቸው ከፍተኛ ጭንቀት ይመሰክራል።

ተዋንያኑ መድረኩ ላይ ከባድ ግን እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ርዕሰ ጉዳዮችን ያነሳሉ፤ «በጦርነት ውስጥ ያሉ ህፃናት» አንዱና ዋነኛው የመነጋገሪያ ርዕሳቸው ነው።

«ብዙውን ጊዜ ይህ ጉዳይ ትኩረት አይሰጠውም። ይሁንና ግን የህፃናቱ ሰቆቃ ማብቂያ የለውም። የበለጠ ተጠቂዎቹ ደግሞ ታዳጊ ሴቶች  ናቸው።  ህፃናት ከመሆናቸው ባሻገር፤ በሴትነታቸው ለወሲብ ብዝበዛ ይዳረጋሉ። በግድ ልብስ እንዲያጥቡና በፅዳት ተግባርም እንዲሰማሩ ይደረጋሉ።»

በአንድ ወቅት ህፃናት ወታደሮች የነበሩ

በአንድ ወቅት ህፃናት ወታደሮች የነበሩ

የታላላቅ ሀይቆች አካባቢ የተውኔቱ መቼት ተደርጎ ሲወሰድ ባጋጣሚ አልነበረም ትለናለች በተውኔቱ ውስጥ ከተሳተፉት ተዋንያን መካከል አንደኛዋ ተዋናይት ኢሳቱ ዲዮፕ፤

«በመጀመሪያ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ሰዎች የሚገኙበትን ቦታ መረጥን። ምክንያቱም እዚያ ሰዎቹ ከልምዳቸው የሚያውቁት ነገር አለና። አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ በየቦታው ስለዚያው ጉዳይ እንገልፃለን። ምዕራባውያን የችግሩ ከፊል ተጠያቂዎች መሆናቸው የታወቀ ነው።  ብራስልስ ውስጥም እንደዚህ አይነት ነገር ላይ መከራከርና መወያየት አለባቸው። ግን እዚያ የሚቀርበው የተለየ ነገር ነው። ያ ግልፅ ነው።»

ግጭትን አስወግዶ አብሮ የመኖርና ይቅርታ የመደራረግ መንፈስ በተውኔቱ ውስጥ በዋናነት ተንፀባርቋል።   ይህ  የዕርቅ መንፈስን የሚያጎላው ጭብጥ «የሚሰባበረው አጥንት ድምፅ» የተሰኘው ተውኔት ካካተታቸው አበይት መልዕክቶች መካከል ዋነኛው ነው። መልዕክቱ በኤሊካ እና የስደት ጓደኛዋ ጆሴፋ መካከል በሚደረገው ውይይት በግልፅ ተቀምጧል።  ሁለቱም የተለያያ ቋንቋ ተናጋሪዎች ቢሆኑም ያሳለፉት አንድ አይነት መከራ ግን ሲያስተሳስራቸው በተውኔቱ ውስጥ እንመለከታለን። የተለያያ ቋንቋ መናገር የልዩነት እና የግጭት መሰረት አለመሆኑን ሌላኛዋ ተዋናይት ማሀደን ስትገልፅ፥

«ያ ምንም ችግር አያመጣም። ይህንንም ነው ለማሳየት የፈለግነው። እኛ የጥበብ ሰዎች ከቋንቋ   እና  ከባህል ልዩነት ባሻገር እንጓዛለን።  ማንም ከየትም ይምጣ ከየት አብረን መጫወት፤ አብረን መኖር እንችላለን። ሁሌም በአንድነት መፍትሄ መሻት፣ በአንድነትም ተቻችለን መኖር እንችላለን። »

የኤሊካ የስደት ዘመን ጓደኛ በስተመጨረሻ ላይ  ከቤተሰቦቿ ጋር ለመገናኘት ይሳካላታል። ተውኔቱ የበለጠ ስሜት የሚነካው ግን ኤሊካ በኤድስ  ታማ ስትሞት የሚታይበት ክፍል ነው። ያንን ያሳየነው ግን ይላሉ ተዋንያኑ፤ ያንን ያሳየነው ኅብረተሰቡ ጉዳዩን የበለጠ እንዲያስብበት ለማስገንዘብ ነው። እንደካናዳዊቷ ፀሀፌ-ተውኔት ከሆነ ኤሊካ መድረኩ ላይ ስትሞት የሚታየው ከመጋረጃው ጀርባ ስለሚልቁት በርካታ ህፃናት ወታደሮች ለማሳሰብ ነው። በነገራችን  ላይ በዓለማችን ከ250 ሺህ በላይ ህፃናት የግዳጅ ወታደሮች ሲኖሩ አብዛኛዎቹ የሚገኙት በአፍሪቃ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic