የሚሌኒየሙ ዕቅድ፤ ተሥፋና እክሉ | ኤኮኖሚ | DW | 17.10.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የሚሌኒየሙ ዕቅድ፤ ተሥፋና እክሉ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዓለም ላይ ተስፋፍቶ የቀጠለውን ድህነትና ረሃብ በግማሽ በመቀነስ ታዳጊ አገሮች የ 21ኛው ምዕተ-ዓመት የልማት ዕርምጃ ተሳታፊዎች ለመሆን እንዲበቁ ለማድረግ የሚሌኒየም ዕቅድ ካወጣ ሰባት ዓመታት አለፈዋል።

ፕሬዚደንት ኮህለር

ፕሬዚደንት ኮህለር

ዕቅዱ በ 2000 ዓ.ም. ሲወጣ ታዲያ ግቡ በተለያዩ ምክንያቶች በተመደበለት የ 15 ዓመት ጊዜ ውስጥ የማይደረስበት መሆኑን በጊዜው ያስገነዘቡት ጥቂቶች አልነበሩም። ዛሬ ዕቅዱ ከግማሽ ጊዜ ላይ ሲደረስ በዕውነትም ዓለምአቀፉ የምግብ ፖሊሲ ምርምር ተቋም ሰሞኑን ያወጣው ዓመታዊ ዘገባ እንደሚያመለክተው በተለይ የብዙዎቹ የአፍሪቃ አገሮች ተሥፋ የመነመነ ነው። ችግሩ ምንድነው? መፍትሄውስ?
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ 2000 ዓ.ም. መግቢያ ላይ የታዳጊውን ዓለም ዕድገት አንቀው የያዙትን ችግሮች ለመቋቋም ስምንት ነጥቦችን ያዘለ የሚሌኒየም ዕቅዱን ገሃድ ሲያደርግ ዋና ዋናዎቹ እስከ 2015 ዓ.ም. ረሃብና ድህነትን በግማሽ ማስወገድ፣ በጨቅላ ዕድሜ የሚቀጩ ሕጻናትን ሞት በሁለት ሶሥተኛ መቀነስ፣ ኤይድስን የመሳሰሉ የጤና መቅሰፍቶችን መታገል ነበሩ።
ትግሉ ዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ትስስር ግሎባላይዜሺን ከፈጠረው ፈተናና ከምዕራቡ ዓለም የፖሊሲ ጉድለቶች፤ እንዲሁም በራሳቸው በታዳጊዎቹ አገሮች ካለው የማሕበራዊ ፍትህ ችግር አንጻር በተጣለለት የጊዜ ገደብ ከግቡ ሊደርስ መቻሉን ገና ከጅምሩ ብዙዎች አጠያያቂ አድርገዋል። ግምታቸው ባለፉት ቅርብ ዓመታት የቀረቡ የጥናት መረጃዎች እንደጠቆሙት በእርግጥም ብዙ የተሳሳተ አልሆነም። ዋሺንግተን ላይ ተቀማጭ የሆነው ዓለምአቀፍ የምግብ ፖሊሲ ምርምር ኢንስቲቲቱት ሰሞኑን የሚሌኒየሙን ዕቅድ ዘመን አጋማሽ ምክንያት በማድረግ ባወጣው ዘገባ አብዛኞቹ ታዳጊ አገሮች ሁለት ቁልፍ ግቦችን ለማሟላት መብቃታቸውን አጠያያቂ አድርጓል። “የረሃብ ፈተና በ 2007“ በሚል ርዕስ ተቋሙ ያወጣው 60 ገጾችን ያቀፈ ዘገባ ጥናቱን የመሠረተው በተለይ በሁለቱ ዓበይት የሚሌኒየም ዕቅዶች በረሃብና በሕጻናት ሞት ቅነሣ ላይ ነው።
ተቋሙ 118 ታዳጊ አገሮች ከተጠቀሱት ሁለት ቀደምት ግቦች ለመድረስ በሚያደርጉት ጥረት ከምን ደረጃ እንደሚገኙ ለማነጻጸር ሞክሯል። በጥናቱ መሠረት ተሥፋ ሰጭ እመርታ በማድረግ ላይ የሚገኙት የላቲን አሜሪካና የካራይብ፤ እንዲሁም የምሥራቅ እሢያና የፓሢፊክ አካባቢዎች ብቻ ናችው። ሌሎቹ የዓለም አካባቢዎች ግን በቂ ካልሆነ ጥቂት ዕርምጃ እስከ ማቆልቆል ከሚሌኒየሙ ግቦች ርቀው እንደቀጠሉ ነው የሚገኙት። ሃቁ ይህ ሲሆን ዘገባውን ያጠናቀሩት የዓለምአቀፉ የምግብ ፖሊሲ ተቋም ተመራማሪ ዶሪስ ቪስማን እንደሚሉት የወቅቱ የዕርምጃ መጠን እንዲፋጠን ካልተደረገ የተወሰኑ አገሮች የልማት ግባቸውን ዕውን ማድረግ መቻላችው ዘበት ነው። ከነዚሁም አብዛኞቹ የሚገኙት ደግሞ ቀደም ሲል እንደተጠበቀውና እንደተፈራው ከሣሃራ በስተደቡብ ባለው የአፍሪቃ ክፍል ነው።

ዘገባው እንደሚጠቁመው ከአካባቢው 42 መንግሥታት 31ዱ የሕጻናትን ሞት በመቀነሱ ረገድ በአሁኑ ወቅት ሊደረስበት ከሚገባው ደረጃ በታች ናቸው። 35 ገደማ የሚጠጉት የሕጻናት አመጋገብ ጉድለትን፤ 27 የሚሆኑትም በአጠቃላይ የሕዝባቸውን የምግብ ችግር ለመቀነስ አልቻሉም። በአጠቃላይ በዓለም ላይ የረሃቡ መጠን ከፍተኛ ከሆነባቸው አገሮች ከአሥር ዘጠኙ የሚገኙት በዚሁ ከሣሃራ በስተደቡብ ባለው የአፍሪቃ ክፍል ነው። አጠቃላዩ መሪር ሃቅ ይህ ሲሆን እርግጥ በሌላ በኩል በዚሁ አካባቢ የሚገኙት ሁለት መንግሥታት ጋናና ሞዛምቢክ ረሃብን በመቀነሱ ግብ አቅጣጫ ታላቅ ዕርምጃ ማድረጋቸው ነው የሚነገርላቸው።
የምጣኔ-ሐብት ባለሙያዎች በጋና የፖለቲካውን ዕርጋታ፤ በሞዛምቢክም ከአሠርተ-ዓመታት የእርስበርስ ጦርነት በኋላ ማገገም መቻሉን እንደ ዋና ምክንያት ይጠቅላሉ። በእርግጥም የፖለቲካ ዓመጽና ሙስና ጠንቅነታቸው በአንድ አገር ደህንነት ላይ ብቻ ሣይሆን ረሃብንና ከዚሁ የተያያዙ ችግሮችን ማባባሳቸው ጭብጥ ሃቅ ነው። ዘገባው በዝርዝሩ መጨረሻ ያስቀመጣቸው ቡሩንዲንና ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎን የመሳሰሉት ለአያሌ ዓመታት በጎሣ ግጭት የተጠመዱ አገሮች ለዚህ ጥሩ ምሳሌዎች ይሆናሉ። በእሢያም ሰሜን ኮሪያ ራሷን ከዓለም በማግለል፣ በምጣኔ-ሐብት አያያዝ ዝቤትና በወታደራዊ ፖሊሲዋ ቀደም ካሉት አገሮች ብዙም አልተሻለችም።

ዛሬም እንዳለፈው ምዕተ-ዓመት ሁሉ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት አገሮች በተትረፈረፈ ምርት በቅንጦት በሚኖሩበት ጊዜ ብዙሃኑ የዓለም ሕዝብ በድህነት አዘቅት ውስጥ ወድቀው እንደቀጠሉ ናቸው። አንድ ሚሊያርድ ገደማ የሚጠጋ የዓለም ሕዝብ ከድህነት ዝቅተኛ መስፈርት በታች የሚሰቃይ ሲሆን አብዛኛው የሚገኘውም አፍሪቃ ውስጥ ነው። የመፍትሄ ያለህ ማለቱ ቀጥሏል። ትናንት ታስቦ የዋለውን የዓለም የምግብ ቀን ምክንያት በማድረግ ሮማ ውስጥ በዓለም የአርሻና የምግብ ድርጅት መቀመጫ ተገኝተው ንግግር ያሰሙት የጀርመኑ ፕሬዚደንት ሆርስት ኮህለር የችግሩን መንስዔ በማመላከት የልማት ፖሊሲ ተሃድሶ ማስፈለጉን ነበር የጠቆሙት።

“የዓለም ድህነት በተለይ ሁለት ምክንያቶች አሉት። አንዱ አብዛኛውን በኤኮኖሚ አቅም ማነስና በበጎ አስተዳደር ጉድለት የተነሣ በዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ትስስር በግሎባይዜሺን ላይ የበቂ ድርሻ እጦት ሲሆን ሌላው ደግሞ መንግሥታትና የግሉ የኤኮኖሚ ዘርፍ ያላንዳች አስተያየት የራሳቸውን ጥቅም አስቀድመው መመልከታቸው ነው። ሁኔታውን ዘላቂ በሆነ መልክ ለማሻሻል የመላውን የሰውልጅ ደህንነት ማተኮሪያው ያደረገ የልማት ፖሊሲን ይጠይቃል” ሲሉ አስገንዝበዋል። እርግጥ ኮህለር አያይዘው እንዳሉት የዓለም ሕዝብ ቁጥር አሁን ከሚገኝበት 6,5 ሚሊያርድ በ 2050 ገደማ ምናልባት ከዘጠኝ ሚሊያርድ በላይ የሚያድግ በመሆኑ ፈተናው ታላቅ ነው የሚሆነው። ዕጣዋ ከመቸውም በላይ በአንድ በተሳሰረው በዛሬይቱ ዓለማችን ሰላምን፣ ነጻነትን፣ ምግብ ለሁሉ መዳረሱን፤ የልማትንና የተፈጥሮ እንክብካቤ ችግሮችን መፍታት የሚቻለው በጋራ ጥረትና በመተሳሰብ መንፈስ ብቻ ነው።

የጀርመኑ ፕሬዚደንት እንደሚያምኑት ረሃብ ሊወገድ የማይችል ነገር አይደለም። ችግሩ ከሚመለከታቸው ወገኖች በኩል ተገቢው ዕርምጃ ቅድመ-ግዴታ መሆኑ እንጂ! በኮህለር አነጋገር “የመጀመሪያው ግዴታ የታዳጊ አገሮች መንግሥታት የሕዝባቸውን የምግብ ዋስትና የፖሊሲያቸው ቀደምት ግብ አድርገው መገኘታቸው ነው። መላው የሰውልጅ ጤናማ፣ ከልምዱ የተጣጣመና በዚሁ መስፈርት የተመረተ ምግብ የማግኘት መብት ሊኖረው ይገባል። እርግጥ መንግሥታቱ በሕዝባቸው መሠረታዊ ፍላጎቶች ላይ ሊያተኩሩና ተገቢውን ክብደት ሊሰጡ የሚበቁት ደግሞ ዜጎች የዴሞክራሲ ተሳትፎ ማድረግ ሲችሉ ብቻ ነው”

ባለፉት ዓመታት በዚህ አኳያ የታየው ሂደት ብዙም የሚያበረታታ አይደለም። ዛሬም አንድ ሚሊያርዱ የዓለም ሕዝብ የዕለት ኑሮውን ከአንዲት ዶላር ባነሰች የቀን ገቢ የሚገፋ ሲሆን 900 ሚሊዮን ገደማ የሚጠጋው በረሃብ ይሰቃያል። በድህነት ሰበብ በየዕለቱ የሚሞቱት ሕጻናት 24 ሺህ ይሆናሉ። በተለይም ይበልጡን የድህነቱ ሰለባ ሆኖ የሚገኘው የታዳጊዎቹ ሃገራት የገጠር ነዋሪ ነው። የዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ትስስር ዘመን የኤኮኖሚ ተጽዕኖ የብዙሃኑን አርሶ-አደር ሁኔታ አባባሰው እንጂ የተሻለ እንዲሆን አላደረገውም። ይህም ድህነትንና ረሃብን መታገሉን ይብስ ያከብደዋል።

ረሃብን በመታገሉ ረገድ ስኬት ለማግኘት በታዳጊ አገሮች ልማትን አንቀው የያዙት ጦርነቶችና ግጭቶች መወገዳቸውም ግድ ነው። የረሃብ ቁራኛ በሆነው ከሣሃራ በስተደቡብ በሚገኘው የአፍሪቃ ክፍል የልማት ዕርምጃቸው በአያሌ ዓመታት ወደ ኋላ የተጎተተውና እየተጎተተ ያለባቸው አገሮች ጥቂቶች አይደሉም። በዓለምአቀፉ ግብረ-ሰናይ ድርጅት በኦክስፋም ግምት በክፍለ-ዓለሚቱ በያመቱ ለጦርነት የሚፈሰው ገንዘብ 18 ሚሊያርድ ዶላር ገደማ ይጠጋል። በአማካይ 15 በመቶው የኤኮኖሚ ዕድገት በዚሁ ከንቱ ሆኖ ይቀራል ማለት ነው። የፈውስ ያለህ የሚያሰኝ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ዕቅድ ለልማት ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ግማሹ ተገባዶ የቀረው ሲቀር የተጣሉትን ግቦች ዕውን ለማድረግ ብዙ ለውጥ፤ ተጨማሪ ሃሣብ ወይም ማሻሻያ ተግባራዊ ዕርምጃዎች ሳይውል-ሳያድር መወሰዳቸው ግድ የሚሆን ነው የሚመስለው። በታዳጊዎቹ አገሮች አስፈላጊውን ማሕበራዊ፣ የፖለቲካና የኤኮኖሚ ሁኔታ የማሟላቱን ያህል በኢንዱስትሪ ልማት ከበለጸጉት መንግሥታት በኩልም ይህንኑ የሚደግፍ ጭብጥ ዕርምጃ መታየቱ ግድ ነው። የልማት ዕርዳታው ፖሊሲ ድህነትን ለመቀነስ በሚያስችል መልክ ተቀርጾ በሥራ ላይ ካልዋለ የረባ ትርጉም አይኖረውም። ስለዚህም በዚህ በጀርመን “የምግብ መብት” የተሰኘው ዓለምአቀፍ ድርጅት ባልደረባ አርሚን ፓሽ እንደሚጠይቁት የበለጸጉት መንግሥታት በአዲስ የልማት ፖሊሲ ጽንሰ-ሃሣብ ላይ ማቅማማታቸው ግድ ነው የሚሆነው።

“ዛሬ በዓለም ላይ ረሃብ ለመስፋፋቱ እርግጥ ግሎባላይዜሺን ብቸኛው መንስዔ አይደለም። ግን አንዱ ክብደት ያለው ምክንያት እንደሆነ አምናለሁ። የእርሻ ንግድን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ታዳጊዎቹ አገሮች ከ 80ኛዎቹ ዓመታት መጀመሪያ አንስቶ በዓለም ባንክና በዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም በ IMF ዘግየት ብሎም በዓለም ንግድ ድርጅት በኩል ገበዮቻቸውን እንዲከፍቱ ሲገፉ ነው የቆዩት። ታዲያ እነዚህ ገበዮች አብዛኛውን ጊዜ በአውሮፓ ሕብረትና በአሜሪካ ምርቶች ይጥለቀለቃሉ። ይህ ሂደት ደግሞ አነስተኛ ገበሬዎች ከገበዮቹ እንዲፈነቀሉ ነው ያደረገው” ይላሉ።

የታዳጊ አገሮችን ልማት ለማፋጠን፤ ብሎም የሚሌኒየሙ ግቦች የሚደረስባቸው እንዲሆኑ ለማድረግ አንዱ ማሠሪያ ማግኘት ያለበት ችግርም የፍትሃዊ ንግድ ጉዳይ ነው። ለታዳጊ አገሮች የኤኮኖሚ ዕርምጃ የሚጠቅም የንግድ ግንኙነት ለማስፈን በዓለም ንግድ ድርጅት ሲካሄድ የቆየው የዶሃ ድርድር ዙር ይበልጡን በሃብታሞቹ መንግሥታት ግትርነት ባለፈው ዓመት ከከሸፈ ወዲህ ለጊዜው የመነቃቃት ተሥፋ አይታይበትም። የበለጸጉት መንግሥታት ገበዮቻቸውን ለመክፈትና የታዳጊውን ዓለም ገበሬ የፉክክር አቅም ያሳጣውን የእርሻ ድጎማቸውን ለማስወገድ ቅን ሆነው ካልተገኙ ወደፊትም ለታዳጊው ዓለም ዕድገት መፋጠንም ሆነ ድህነትን ለማሸነፍ ጥርጊያ ይከፈታል ብሎ ማሰቡ ከንቱ ዘበት ነው።
ለማጠቃለል በተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ዕቅድ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ መጀመሪያ በወቅቱ የተጣሉት ግቦች ለስኬት እንዲቃረቡ ወይም ቢቀር በትክክለኛ አቅጣጫ እንዲራመዱ ለአራሚ ዕርምጃዎች መነሣቱ ግድ ነው የሚሆነው። ምናልባት ለየት ያለ የልማት አማራጭና ሌላ የጊዜ ገደብ የማስፈለጉም ሃሣብ ሊጤን ይችላል። የሆነው ሆኖ ብዙሃኑ የዓለም ሕዝብ በ 21ኛው ምዕተ-ዓመትም በረሃብተኝነት ሊቀጥል አይገባውም።