የሙጋቤ ስንብትና የ«ህዳሴው ግድብ» ውዝግብ | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 24.11.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የሙጋቤ ስንብትና የ«ህዳሴው ግድብ» ውዝግብ

የዚምባብዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ሥልጣን የመልቀቃቸው ዜና፤ ግብጽ የ«ህዳሴው ግድብ»ን በተመለከተ ሰጠችው የተባለው ማስጠንቀቂያ እንዲሁም በኢትዮጵያ እስር ቤቶች ውስጥ እስረኞች ላይ ይደርሳል የተባለው ሰቆቃ በሳምንቱ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ትኩረት ሰስቧል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:27

ሙጋቤ ተሰናብተዋል የ«ህዳሴው ግድብ» አወዛግቧል

ሣምንቱ የተንደረደረው የዚምባብዌ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለመልቀቅ የመወሰናቸውን ዜና በማስተጋባት ነበር። ጓድ ሮበርት ሙጋቤን እንደምን ቀን ከዳቸው? የህዝቡ ጭፈራ እና ፈንጠዝያ፣ የምዕራባውያኑ ጋዜጠኞች ቡረቃ፤ ብሎም የሌላኛው አምባገነን የመተካት ዳርዳርታስ ምን ይመስላል? የዛሬው ዝግጅታችን ዋነኛ ትኩረት ነው። «ውሃ የሕይወት እና የሞት ጉዳይ» ነው ስላለችው ግብጽ እና የ«ህዳሴው ግድብ» ላይ የተሰጡ አስተያየቶችንም እንቃኛለን። ኢትዮጵያውያን እስረኞች በተለያዩ እስር ቤቶች ሰቆቃ ይደርስባቸዋል የሚሉ አስተያየቶችም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተነስተጋብቷል። 

ዚምባብዌን ከቅኝ ግዛት አንስቶ ለ37 ዓመታት ያህል የመሯት (እንደ ፓርቲ አባሎቻቸው አጠራር) ጓድ ሮበርት ሙጋቤ በዚህ ሳምንት ሥልጣናቸውን የለቀቁት ከብዙ ውዝግብ በኋላ ነበር። ዛኑ ፒኤፍ የተባለው ፓርቲያቸው የሰጣቸው የ24 ሰአት ገደብ ማክሰኞች ዕለት ሳይጠናቀቅ በፊት ምሽት ላይ ብቅ ብለው ንግግር ሲያሰሙ እንደተጠበቀው ሥልጣናቸውን ስለመልቀቃቸው ይናገራሉ ተብሎ ነበር። እሳቸው ግን ሥልጣኑን ተቆጣጥረው የቤት ውስጥ እስረኞች ያደረጓቸውን ጄነራሎች አመስግነው «ሁሉም ነገር በቀና መንፈስ ለሀገር ጥቅም ሲባል ነው የተደረገው» የሚል እምነት እንዳላቸው ሥልጣን ስለመልቀቃቸው ግን አንዳችም ሳይገልጡ ለ20 ደቂቃ ግድም ንግግር አሰሙ። «ያሳሰባቸውን ነገር ለማስመዝገብ የተጓዙበት መንገድ ጥቅምና ጉዳቱ ምንም ይሁን ምን፤ እኔ እንደ ዚምባብዌ ፕሬዚዳንት እና ጠቅላይ ጦር አዛዥነቴ ትኩረቴን እንዲስብ ላደረጉት ጉዳይ ዕውቅና እሰጣለሁ። እናም ይህ የሆነው ከእውነት በመነጨ መንፈስ ብሎም ለሀገሪቱ መረጋጋት ጥልቅ ከሆነ አርበኝነታዊ መቆርቆር ነው ብዬ አምናለሁ።»

ሙጋቤ በስተመጨረሻም የመጨረሻ ንግግራቸውን ቴሌቪዥን መስኮት ላይ አፍጥጦ ሲጠባበቃቸው ያመሸውን ተመልካች በኪስዋሂሊ አፍ «አሳንቴ ሳና» ብለው አመስግነው ተሰናበቱ።  ንግግራቸውን ቴሌቪዥን መስኮት ላይ አፍጥጦ ሲከታተል የቆየው ዓለም በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ላይ ንግግራቸውን እየመነዘረ የየበኩሉን አስተያየት መሰንዘር ጀመረ። 

«ሥልጣን ለቅቄያለሁ አላሉም፤ ምንድን ነው እየሆነ ያለው?» እንዲሁም «የለም፤ ደህና እደሩ ማለታቸው በእጅ አዙር ሥልጣኔን መልቀቄ ነው ማለታቸው ነው» እንዲሁም «ሙጋቤ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው ሥልጣኔን ለቅቄያለሁ ለማለት ኩራታቸው አይፈቅድላቸውም ግን ሥልጣኑን መልቀቃቸው አይቀርም» የሚሉ እና ሌሎች መላ ምቶችም ሲሰነዘሩ ቆዩ። እናም ፓርቲያቸው ሙጋቤን በምክር ቤት ለመክሰስ ዳር ዳር ማለት ሲጀምር እሳቸውም በቁም እስር ወደሚገኙበት ቤታቸው የካቢኔ አባላቶቻቸውን ለስብሰባ ጠሩ። ካቢኔያቸውን ሲጠሩ የመጨረሻቸው ነበር። ከአምስቱ የካቢኔ አባላት በቀር ግን ሌሎቹ ዝር ሳይሉ ወደ ምክር ቤት ማቅናታቸው ነበር የተነገረው። አፍታም ሳይቆይ ሙጋቤ ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ለዓለም አወጁ። መዲናዪቱ ሐራሬ ጮቤ በሚረግጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ተጨናነቀች።

በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ሙጋቤ የጻፉት ነው የሚል ደብዳቤን ጨምሮ ድጋፍ እና ተቃውሞው መሰንዘሩን ቀጠለ። የተክልዬ ባሪያ የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ የሚከተለውን ጽፏል። «የሰው ሀገር ወታደር እንዲህ ቁም ነገር ይሰራል እኛ ሀገር ኮንትሮባንድ ንግዱን ያጧጡፋል። በል ሲለው ወገኖቹ ላይ ጥይት ያዘንባል ምን ይደረግ? እውቀት ተቀምሞ በመርፌ አይወጋ!» 

አብደረስ ቀዋሲሳት ደግሞ በዛው በፌስቡክ፦ «ማንም ዘላለማዊ አይደለም! ፕሬዚዳንቱን በሰላማዊ መንገድ ማሰናበቱ ጥሩ ነው። ሆኖም የምዕራባዊያን እጅ ካለበት የዙምባቡዌ መተራመስ አይቀሬ ነው!» የሚል ጽሑፍ አስነብቧል። ራእየ ዮሐንስ  «37? ስልጣን ለቀቁ ወይስ ስልጣን ለቀቃቸው??» ሲል በሙጋቤ የሥልጣን ዘመን እጅግ መራዘም ተሳልቋል። «የዘገየ ውሳኔ ቢሆንም ስልጣን የህዝብ መሆኑ አስተማሪ ነው» የሚል አጠር ያለ አስተያየት የሰነዘረው ደግሞ መንግሥቱ ትግስቱ በርታ ነው።

ኢትዮ ኦብዘርቫቶሪ በትዊተር ገጹ ባቀረበው ጽሑፉ፦ «ሕወሃት ሲያምታታ ሙጋቤ ከሥልጣን 'በፈቃዳቸው' ለቀቁ ይላል! ይህ ውሸት ነው! ፓርቲው ቀደም ብሎ ከአመራር አውርዶት፣ ፓርላማው ተሰብስቦ ሊፈነግለው እያለ በውርደት ሊገፈተር ሲል ነው በደብዳቤ ለቀቅሁ ያለው!» ብሏል። ከመልእክቱ ጋርም «ሮበርት ሙጋቤ ስልጣናቸውን በራሳቸው ፈቃድ ለቀቁ» የሚል የፋና ቴሌቪዥን የድረ-ገጽ ጽሑፍንም አያይዟል። 

የሺሀሳብ አበራ በፌስቡክ ገጹ ላይ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤን አወድሶ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ «እንደ አፄ ምኒሊክ እና ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፣እንደነ ማርክስ ጋርቤይ፣ እንደነ ማርቲን ሉተር ኪንግ...ለጥቁር በመኖር ባለታሪክ ናቸው» ያለው የሺሀሳብ ነገር ግን ሲል ይቀጥላል። «ነገር ግን ምዕራባውያን ሙጋቤን አኮስሰው ማንዴላን አንግሰዋል። ማንዴላ ለምዕራቡ ምቹ ነው። ደቡብ አፍሪቃ ዛሬም በነጭ ቅኝት የምትዘፍን ሀገር ናት። ዝንባብዌ ግን እንደዛ አይደለችም። ሙጋቤ እንደዛ አይደለም። ጀግና መሪ ሀገር ይፈጥራል» ብሏል። 

ማዳም ደማቂያ በትዊተር ያሰፈረው መልእክት ከሺሀሳብ አስተያየት ተቃራኒ ነው። እንዲህ ሲል ይንደረደራል። «መቼስ ባለፈው 40 አመት ለበቀል ሲጎኖጉኑ አልነበረም አይባልም። ግን ሙጋቤ መሬቱን ነጥቆ ለአራሹ ሳይሆን ለፖርቲው ሹሞች ነው ያከፋፈለው» ይላል። የዚምባብቄ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ በ37 ዓመት አገዛዛቸው በተለይ በምዕራባውያን ጥርስ ካስነከሰባቸው ነገራቸው አንዱ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ከሐብታም ነች ዚምባብዌያውያን ቀምተው ለጥቁሮች ማከፋፈላቸው ነበር። ማዳም ደመቂያ የትዊተር ጽሑፍን የሚቋጨው የሙጋቤን የአስተዳደር ርእዮተ-ዓለምም በመተቸት ነው፦«የሚከተሉት ማርክሲዝም ደሞ ገበሬውን አደኸየው። ህዝቡንም ሊመግብ አልቻለለም። ተቃዋሚዎችን አጠፋ። በዛ ላይ ሙስናው» በሚል ጽሑፍ።

የዚምባብዌ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ለጥቁር ዚምባብዌያውያን ጻፉት በተባለ ደብዳቤ ላይ በምድር ላይ ቀናቸው እያከተመ መሆኑን በመግለጥ ወደፊት እሳቸው ከዚህ ዓለም ሲሰናበቱ ዜምባብዌያውያን እንደሚያመሰግኗቸው ተናግረዋል። ለዚያ ደግሞ፦ እስካሁን ድረስ ከሌሎቹ የአፍሪቃ ሃገራት በተለየ የሀገራቸውን መሬት በነጮች ከመቀራመት ማዳናቸውን ጠቅሰዋል። «እስኪ ሌሎች የአፍሪቃ ሃገራትን ተመልከቱ። ብዙም ሳትርቁ ደቡብ አፍሪቃን እዩ። ማንዴላ መሬቱን ሽጦ ምጣኔ ሐብቱን በመሉ ለነጮች አስረክቧል» ይላል የሙጋቤ ነው የተባለው ደብዳቤ። «ደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ጥቁሮች ዝንት ዓለም ለነጭ ደቡብ አፍሪቃውያን ባርያ ኾነው ይቆያሉ» ሲሉ  ሙጋቤ ማከላቸውም ይነበባል በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች የተሠራጨው ደብዳቤ።

እንደ ሙጋቤ ሥልጣን የመልቀቅ ዜና ባይሆንም፤ የግብጹ ፕሬዝዳንት አብደል ፈታህ አልሲሲ ኢትዮጵያን በተዘዋዋሪ መንገድ ኾኖም  በጥብቅ በድጋሚ የማስጠንቀቃቸው ዜናም የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎችን ትኩረት ስቦ ነበር። ቀደም ሲል ውሃ ለግብጻውያን የኅልውና ጉዳይ መሆኑን በመግለጥ ሀገራዊ ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ «አቅሙ» እንዳላቸው የተናገሩት አልሲሲ፦ የአባይ ውሃ ድርሻ «የሕይወት እና የሞት ጉዳይ» ነው ሲሉ ባሳለፍነው ቅዳሜ ማስጠንቀቂያ ሰንዝረዋል። 

አብደል ሐሰን ትዊተር ላይ ያስነበበው የእንግሊዝኛ ጽሑፍ እንዲህ ይላል። «ግብጻውያን በአባይ ሊጨነቁ አይገባም። ይኼ በ2020 አባይን ለእስራኤል የማሻገር ስምምነቱን እንዲቀበሉ ጫና የመፍጠር ስልት ነው።» የአብደል ሐሰን ጽሑፍ ከታች እና ከላይ የእስራኤል ባንዲራ ሰፍሮ ከመሀል የኢትዮጵያ፤ የግብጽ እና የሱዳን መሪዎች ሲጨባበጡ የሚታይበት ፎቶግራፍ አብሮ ተያይዟል። 

የአባይ ውሃ ጉዳይ ግብጽና ሱዳንንም ማወዛገቡ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች የተንሸራሸሩ ጽሑፎች አመላክተዋል። የግብጹ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሳሜህ ሹክሪ ረቡዕ እለት ባሰሙት ንግግር ግብጽ የአባይ ውሃ የሱዳንን ድርሻ ትወስድ የነበረው ከሱዳን ዕውቅና ውጪ አይደለም ብለዋል። ውጭ ጉዳይ ሚንሥትሩ ይህን ያሉት የሱዳኑ አቻቸው ኢብራሒም ጋንዶር በቅርቡ ባሰሙት ንግግር በቅርብ ዓመታት ውስጥ ግብጽ የሱዳንን ድርሻ በተደጋጋሚ እየወሰደች ነው በማለታቸው ነው።

«ግብጽ የ1959ኙ ‘ስምምነት' በኢትዮጵያ ዕውቅና እንዲያገኝ ትሻለች» ሲል በትዊተር ገጹ የጻፈው ክፍሉ ኬንሶ፦ «እንደዚያ ‘ስምምነት'  ከሆነ የአባይ ውሃ ሙሉ ለሙሉ የተሰጠው ለግብጽ እና ሱዳን ሲሆን የኢትዮጵያ ድርሻ ዜሮ ነው» ብሏል። ቀጠል አድርጎም፦ «ኢትዮጵያ  85% የአባይ ፍሰት አስተዋጽዖ ታደርጋለች» በማለት ክፍሉ የግድቡን ግንባታ በፎቶ አያይዟል።  

የኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በበኩላቸው ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ የጀመረችዉን ግድብ አስመልክተው ሲናገሩ፦ «ማንም ወገን ሊያስቆመው የሚችል ፕሮጀክት አይደለም» ብለዋል። 

በእስር ቤት እንግልትና ሰቆቃ የደረሰባቸው እስረኞች በፍርድ ቤት ስለሚገጥማቸው በደል የሚያወሱ ጽሑፎች በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች ተነበዋል። ከጽሑፎቹ መካከል አንድ ታሳሪ አቤቱታቸውን ለማቅረብ ሲማጸኑ ከዳኞች ፈቃድ ባለማግኘታቸው «ህዝብ ይፍረደኝ» ብለው በሰቆቃ የተኮላሸ ሐፍረታቸውን በፍርድ ቤት ውስጥ አሳዩ፤ «ያለቀሱም ነበሩ» የሚለውን ጽሑፍ ብዙዎች በትዊተር እና በፌስቡክ ተቀባብለውታል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ
 

Audios and videos on the topic