የሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ እና ሶርያ | ዓለም | DW | 15.02.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ እና ሶርያ

የሥምምነቱን መፅናት-መፍረስ ለማወቅ ምናልባት ሽታይንማየር እንዳሉት ከእንግዲሕ አንድም ሁለትም ሳምንት መታገስ ያስፈልግ-ይቻልም ይሆናል።ጦርነትን ለጊዜዉም ቢሆን ለማቆም የተስማሙት መንግሥታት ሥለ ሥምምነቱ ተናግረዉ ወደ ጉባኤዉ አዳራሽ የገቡት ግን እንደወትሮዉ እየዛቱ ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:26
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
12:26 ደቂቃ

የሙኒክ ጉባኤ

ካለፈዉ አርብ እስከ ትናንት ሙኒክ-ጀርመን ዉስጥ ሥለ ዓለም ሠላም የመከረዉን ጉባኤ ያዘጋጁት ቮልፍጋንግ ኢሽንገር እንዳሉት ዓለም ከቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ ወዲሕ እጅግ «ከተበለሻ (ፖለቲካዊ) ሥርዓት» ላይ ደርሳለች።የጎሪጎሪያኑን 2015 በጉባኤ ጀምረዉ በጉባኤ የሸኙት የዓለም መሪዎች፤ ኢሽንጋር ባዘጋጁት ጉባኤ እንደገና የተሠበሰቡትም «በጣም አደገኛ» በሚባሉ ግዛቶች በጋራ ሠላም ለማስፈን የሚቻልበትን መንገድ ለመተለም ነዉ ይላሉ-ኢሽንገር።ተሳክቶ ይሆን?

2015 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) አንዳድ ዘገቦች እንደሚጠቁሙት የጉባኤ ዓመት ነበር።የአፍሪቃ መሪዎች ከመደበኞቹ አሐጉራዊ፤ ክፍለ አሐጉራዊ ና አካባቢያዊ ጉባኤዎቻቸዉ በተጨማሪ የደቡብ ሱዳን፤የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ፤ የሶማሊያ፤የኮትዲቯር፤ የማሊ፤ የቡሩንዲ ቀዉስና ግጭት፤ የአፍሪቃ እና የሕንድ የአፍሪቃና የቻይና፤ የአፍሪቃ እና የአዉሮጳ ትብብር ጉባኤ እንዳሉ-ዓመቱን በጉባኤ ተቀብለዉ በጉባኤ ሸኙ።

የአዉሮፆች የባሠ ነዉ።የግሪክ፤የፖርቱጋል፤ የሥደተኞች፤የዩክሬን፤ የሶሪያ፤ የኢራን፤ የአየር ንብረት፤ የምጣኔ ሐብት----ይቀጥላል።የሶሪያ ጦርነት፤ የየመን ጦርነት፤ የአፍቃኒስታን ጦርነት፤ የኢራቅ ጦርነት፤ የፍልስጤም እስራኤሎች ጦርነት፤ የዩክሬን ጦርነት፤ የኮሎምቢያ ጦርነት፤ የሞስኮ፤ ዋሽግተን-ብራስልስ ልዩነት፤ የኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር፤ የሰሜን ኮሪያ የኑክሌር መርሐ-ግብር፤ የኢቦላ ሥርጭት፤ የዓየር ንብረት ለዉጥ፤ የርዳታ ማሰባሰኒያ ሁሉም የልዩ ጉባኤ ሰበብ ምክንያቶች ነበሩ።

የዓለም መሪ፤ ሚንስትር የጦር አዛዦች ከብራስልስ-ኒዮርክ፤ ከአዲስ አበባ-ካይሮ፤ ከለንደን-ፓሪስ፤ ከሚኒስክ-በርሊን እንደባተሉ 2015ን በጉባኤ ሸኝተዉ-2016ትንም

በጉባኤ ነዉ-የተቀበሉት።አርብ ሌላ ቀን፤ ሌላ ሥፍራ-ሙኒክ፤ ሌላ ግን መደበኛ ጉባኤ።«ፊት ለፊት መገናኘቱ ጥሩ ነዉ» ይላሉ SIPRI በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የሲዊድን ጥናት ተቋም ሐላፊ ዳን ስሚዝ-የጉባኤዉን ድድግሞሽ።

«በስተ መጨረሻዉ የሚያመለክተዉ ምንድነዉ፤ ዓለም ከዲጅታል ዘመን ላይ ብትደርስም የሰዎችን ፊለፊት መገናኘት የሚተካ ነገር የሌለ መሆኑን ነዉ።ለመስማማትም ሆነ ከሥምምነት የሚያደርስ መሠረት ለመጣል በሚደረግ በየትኛዉም የዲፕሎማሲ ወይም የድርድር ሒደት ፊትለፊት መገናኘት ምትክ የለዉም።»

የጉባኤ ዓመት በተባለዉ በ2015 ከተደረጉ በርካታ ዓለም አቀፍ የሠላም ጉባኤ፤ ድርድር፤ ዲፕሎማሲዎች ሁሉ «ለአግባቢ ስምምነት የበቁት ሁለት ናቸዉ» ይላሉ የሙኒኩ ጉባኤ አዘጋጅ ቮልፍጋንግ ኢሽንገር።የኢራን የኑኬሌር መርሐ ግብር እና የዓለም የአየር ንብረት ለዉጥ።

የማዕቀብ ቅጣት፤ የዲፕሎማሲ ዉዝግብ፤ የጦር ሜዳ ዉጊያም ከየመን እስከ ሶሪያ፤ ከዩክሬን እስከ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ፤ ከኢራቅ እስከ አፍቃኒስታን፤ ከኮሪያ ልሳነ ምድር እስከ ኮሎምቢያ እልቂት፤ ሥደት፤ ሥጋትን ከማናራቸዉ ባለፍ አሸናፊም ተሸናፊም አለመኖሩ ነዉ-እንቆቅልሹ።

ኢሽንጋር «በጣም አደገኛ በሆኑ ግዛቶች» ሠላም የሚሠፍንበትን ሥልት ለመተለም ያለመ-ያሉት የዘንድሮዉ የሙኒክ የዓለም የፀጥታ ጉባኤ በግራ-አጋቢ እንቆቅልሽ ለተበተበዉ ለሶሪያዉ ጦርነት መፍትሔ መፈለግ ቀዳሚ ርዕሡ ነበር።በሶሪያዉ ጦርነት የተዘፈቁት መንግሥታት ባለሥልጣናት በጉባኤዉ መጀመሪያ አርብ ያደረጉት ሥምምነት ደግሞ ተራዉን ዓለም ግራ የሚያጋቡት ሐብታም ሐያላን መንግሥታት ግራ አጋቢዉን ጦርነት ለጊዜዉም ቢሆን ለማቆም መቁረጣቸዉን ጠቋሚ ነበር።

የፕሬዝደንት በሽር አል-አሰድን መንግሥት ለመጣል አረብን፤ቱርክን፤ ምዕራብ አዉሮጶችን ከጎንዋ ያሰለፈችዉ ዩናይትድ ስቴትስ፤ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሯ ጆን ኬሪ እንዳሉት ግጭቱን ለማስቆም ቆርጣለች።

«ግጭቱን በብሔራዊ ደረጃ ባንድ ሳምንት ጊዜ ዉስጥ ለማቆም ተስማምተናል።ይሕ በርግጥ በጣም የተለጠጠ ነዉ።ይሁንና በተቻለ ፍጥነት ገቢር ለማድረግ ሁሉም ወገን የሚቻለዉን ጥረት ለማድረግ ቆርጧል።»የፕሬዝደንት በሽር አል-አሰድን መንግሥትን ከሚደግፉ ጥቂት መንግሥታት አንዷ፤ ሩሲያም የተለየ አቋም አላት አልተባለም።እንዲያዉም ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ሥምምነቱን «የሥራችን ዉጤት» በማለት ነበር-ያወደሱት።

«ሥራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ያስገኘዉ ዉጤት መሆኑን ላሰምርበት እፈልጋለሁ።ዛሬ የፈረምነዉ ሠነድ በፖለቲካዉ እና በሠብአዊ ርዳታዉ ብቻ ሳሆን በወታደራዊዉ መስክም መተባበር እና መቀናጀት እንደሚያስፈልግ የሚያረጋግጥ ነዉ።»ሥምነቱን የደማስቆ መንግሥት ደጋፊና ጠላት የሚባሉት የፋርስ፤የአረብ እና የቱርክ መንግሥታት ባለሥልጣናትም አድንቀዉ-አፅድቀዉታል።የሶሪያ ተፋላሚ ሐይላትን የሚሸምግሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአረብ ሊግ ልዩ መልዕክተኛ ስታፋን ደ ሚስቱራ በፋንታቸዉ «ታላቅ እመርታ» ነበር ያሉት።

«ደሕና፤ ይሕ ታላቅ እመርታ ነዉ።ምክንያቱም አዋጅ አይደለም፤መግለጫም አይደለም።ቃል ነዉ።ቃላቸዉን ተግባራዊ በሚያደርጉ ወገኖች የተገባ ቃል ነዉ።ከዚሕ አኳያ ሲታይ አዎ-ታላቅ እመርታ ቢባል ተገቢ ነዉ።ጆን ኬሪም ሚንስትር ላቭሮቭም እንዳሉት ቃሉ እስኪፈተን ድረስ ግን ትንሽ አጠብቃለሁ።»

የአርቡ ሥምምነት ሲወደስ፤ ሲደነቅ፤ የሙኒኩ ጉባኤ በመልካም ዉል የመጀመሩ ቸር ዜና ሲነገር-ሲዘገብ፤ የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር እንደ የዋሕዋ ኢትዮጵያዊት ልጃገረድ-«---- አላምንም» ማለታቸዉን ብዙ ያስተዋለዉ አልነበረም።

«ያለፈዉን ጊዜ ልምዳችንን እናዉቀዋለን።ሥለዚሕ ዛሬ ታላቅ እመርታ ታይቷል ብዬ አልናገርም።(ስምንነቱ ) ታላቅ እምርታ ከሆነ በሚቀጥሉት ሳምንታት ይረጋገጣል።»የሥምምነቱን መፅናት-መፍረስ ለማወቅ ምናልባት ሽታይንማየር እንዳሉት ከእንግዲሕ አንድም ሁለትም ሳምንት መታገስ ያስፈልግ-ይቻልም ይሆናል።ጦርነትን ለጊዜዉም ቢሆን ለማቆም የተስማሙት መንግሥታት ሥለ ሥምምነቱ ተናግረዉ ወደ ጉባኤዉ አዳራሽ የገቡት ግን እንደወትሮዉ እየዛቱ ነበር።የሳዑዲ አረቢያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አደል አልጀባር «የመጨረሻዉ ግባችን የበሽር አል-አሰድን መንግሥት ማስወገድ» ነዉ አሉ።አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ ሚንስትሩ እንዳሉት በተለይ እራሱን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት የሚለዉን ቡድን ለማጥፋት ሳዑዲ አረቢያ እግረኛ ጦር ለማዝመት ዝግጁ ነች።

«በዳዓሽ ላይ ጦርነት የከፈተዉ እና ከመጀመሪያዉ ጀምሮ አባል የሆንበት ዓለም አቀፍ ሕብረት ከአየር ድብደባዉ በተጨማሪ ወደ ሶሪያ እግረኛ ጦር እንዲዘምት ከወሰነ ሳዑዲ አረቢያ ልዩ ጦር ለማዝመት ዝግጁ ነች።»

ቱርክም እግረኛ ጦር የማዝመቱን ሐሳብ እንደምትጋራ ባለሥልጣናትዋ ጠቁመዋል።የሐያላኑ መንግሥታት ባለሥልጣናትም ሥለአርቡ የቱኩስ አቁም ሥምምነታቸዉ አብራርተዉ ሳይጨርሱ ይወቃቀስ ይወናጀጀሉ ገቡ።

«በእኛ እምነት እስከ ዛሬ ድረስ አብዛኛዉ የሩሲያ ጥቃት የተፈፀመዉ በሕጋዊ ተቃዋሚ ቡድናት ላይ ነዉ።የተደረሰዉን ሥምምነት ለማክበር የሩሲያ የጥቃት ኢላማ መቀየር በጣም አስፈላጊ ነዉ።ይሕ ተግባራዊ እንዲሆን ሩሲያን ጨምሮ ዓለም አቀፉ የሶሪያ ደጋፊ ቡድን ተስማምቷል።ይሕ መከበር አለበት።»

የአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ።የሩሲያዉ ጠቅላይ ሚንስትር የዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ንግግር ደግሞ ከሶሪያም አልፎ የሐያላኑን ሁለንተናዊ ልዩነት ጠጠር ባሉ ቃላት ያፈጋ ነበር።

«ኔቶ ሥለ ሩሲያ የሚከተለዉ መርሕ የጠላትነት እና ድብቅ ነዉ።ወደ ቀዝቃዛዉ ጦርነት ዘመን እያሽቆለቆልን ነዉ-ከሚያሰኝ ደረጃ ላይ ደርሰናል።በየትኛዉም መስክ እኛ ለኔቶ፤ ለአዉሮጳ ወይም ለዩናይትድ ስቴትስ በጣም አስጊ ተደርገን ነዉ የምንታየዉ።ባልደረባዬ ሚስተር ሽቶልተንበርግ ይሕን አረጋግጠዋል።ልክ እንደ አስፈሪ ፊልም የኑክሌር ጦርነት የምትጀምረዉ ሩሲያ እንደሆነች አቅርበዋል።እንዳዴ የምኖነረዉ በ2016 ነዉ ወይስ በ1962 እያልኩ እደነቃለሁ።ግን በዚች ትንሽ ዓለማችን ተጨባጭ ሥጋት አለ።»

የሙኒኩ ጉባኤ ከሶሪያ በተጨማሪ ከናጄሪያ እስከ አፍቃኒስታን፤ ከሶማሊያ እስከ ዩክሬን የሚገኙ ቀዉሶችን አንስቶ ተነጋግሯል።አሸባሪነትን ለመዋጋት መወሰድ ሥለሚገባዉ የጋራ እርምጃ፤ የሥደተኞችን አያይዝና ብዛት፤ የአምደ መረብ አጠቃቀምም የጉባኤተኞች ርዕሶች ነበሩ።

የምዕራባዉያኑን መንግሥታት መርሕን በተለይም የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (የኔቶን) ዉጊያና ዘመቻ የሚቃወሙ ሠልፈኞችም የጉባኤዉን ሆቴል ከበዉ ተቃዉሟቸዉን ሲያሰሙ ነበር።ከሰባ ሐገራት የተወከሉ የስድስት መቶ ጉባኤተኞችን ብዙ ርዕሶች ያኮሰሰዉ ግን የሶሪያ ጦርነትና እብዙ ሥፍራ የተከፈሉት የሐያል፤ ሐብታም መንግሥታት ተቃራኒ አቋም ነበር።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ስታፋን ደ ሚስቱራ በጦርነቱ አሸናፊም ተሸናፊም የለም፤ ወደፊትም አይኖርምም ይላሉ።

«ተጨባች መፍትሄ የለም።አንደኛዉ ወገን በጦር ሐይል ቢያሸንፍ እንኳ፤ ሚስጥሩ ሐገሪቱን እንዴት ማረጋጋት ይቻላል ነዉ?እንዴት ነዉ ዳግም መገንባት የሚቻለዉ ነዉ?በነገራችን ላይ አሸናፊ የለም።ዉጊያዉን ማሸነፍ ይቻል ይሆናል፤ የሶሪያን ጦርነት ግን ከእንግዲሕ ማሸነፍ አይቻልም።»

የሐያል፤ ሐብታም መንግስታትንና የሚደግፏቸዉን ሐይላት አሠላለፍን ያዘበራረዉ የሶሪያ ጦርነት የመባስ እንጂ የመርገብ አዝማሚያ አላሳየም። በሳምንቱ ማብቂያ የተጋጋመዉ ዉጊያ በደማስቆ መንግሥት እና በጠላቶቹ መካከል ከመሆን ይልቅ በዩናይትድ ስቴትስ እና በአረብ ወዳጆችዋ በሚደገፉ በሁለት የደማስቆ መንግሥት ጠላቶች መካከል መሆኑ ነዉ ዕዳዉ።የቱርክ መንግሥት ጦር እና የሶሪያ ኩርድ አማፂያን።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ

Audios and videos on the topic