የሙኒክ የዓለም የፀጥታ ጉባኤ | ዓለም | DW | 01.02.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሙኒክ የዓለም የፀጥታ ጉባኤ

በዓለም አቀፋዊ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ የሚነጋገረው የሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ ዛሬ ማምሻውን ተጀምሯል። ለ3 ቀናት የሚቆየው ይኽው ጉባኤ በማሊእና በሶሪያ እንዲሁም በሌሎች ብጥብጥ ባየለባቸው ሃገራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይነጋገራል።

ወደአራት መቶ የተገመቱ ታዳሚዎችን የሚያስተናግደዉ ዓመታዊዉ የሙኒክ ዓለም ዓቀፍ የፀጥታ ጉባኤ ዛሬ ማምሻዉን ተጀምሯል። ጉባኤዉ በተለይ የማሊ እና የሶርያ ቀዉስ ላይ ትኩረቱን ማድረጉን ከስፍራዉ የወጡ ዘገባዎች ያመለክታሉ። በጉባኤው ላይ መራህያነ መንግሥትና ርዕሳነ ብሄራትን ጨምሮ 70 የሚሆኑ የመከላከያ ሚኒስትሮችና የጦር መሣሪያ ኢንዱስትሪና የልዩ ልዩ የንግድ ተቋማት መሪዎች በአጠቃላይ ወደ 400 እንግዶች ተካፋይ ናቸው። ከተሳታፊዎቹ አንዱ የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ናቸው።

ባይደን በነገው እለት ከአትላንቲክ ወዲህና ወዲያ ማዶ ባሉት ግንኙነቶች በሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት በእንግሊዘኛው ምህፃር NATO ና ሩስያ ግንኙነት እንዲሁም ስለ ህንድና ብራዚል ፈጣን እድገት በሚካሄደው ንግግር ላይ ይካፈላሉ። ዛሬ ጀርመን የገቡት ባይደን ከጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጋር በርሊን ውስጥ በሁለቱ አገራት የንግድ ግንኙነት ላይ እንደሚመክሩም ተዘግቧል። ባይደን ነገ ከጀርመን ወደ ፈረንሳይ በማቅናት ሰኞ ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ ጋር ፓሪስ ውስጥ ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ባይደን ምክትል ፕሬዝዳንት ከሆኑ ወዲህ ጀርመንን ሲጎበኙ የአሁኑ የመጀመሪያቸው ነው። በሌላ በኩል ባይደን ለአንድ የጀርመን ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ ኢራን ከአሜሪካን በቀጥታ እንድትደራደር ሃሳብ አቅርበዋል።

ባይደን በዚሁ ቃለ ምልልስ ኢራን ያቋረጠችውን የኒዩክልየር መርሃ ግብሯ ላይ የሚካሄደውን ድርድር እንድትቀጥልም መገፋፋታቸው ተዘግቧል።

ለሶስት ቀናት በሚቆየዉ ጉባኤ የሚሳተፉት የአሜሪካኑ ምክትል ፕሬዝደንት ጆ ባይደን፤ ነገ ለጉባኤዉ ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። ከጉባኤዉ አስቀድመዉ ግን ዛሬ ከሰዓት በኋላ ከጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ጋ ስለሁለቱ ሀገሮች እና ስለአዉሮጳ ኤኮኖሚያዊ ይዞታ መነጋገራቸዉ ተሰምቷል። ስለጉባኤዉ የጀርመን መገናኛ ብዙሃን ያነሷቸዉን ነጥቦች እንዲያጋራን የበርሊኑን ወኪላችንን ይልማ ኃይለሚካኤልን በስልክ አነጋግሬዋለሁ፤

ይልማ ኃይለሚካኤል

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic