የሙኒኩ ጉባኤና ኢራን | ዓለም | DW | 08.02.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሙኒኩ ጉባኤና ኢራን

ፕሬዝዳት ማሕሙድ አሕመዲኒጃድ ተጨማሪ የዩራንዮም-ማብላያ ተቋማት እንዲሰሩ ወይም ያላዉ ማብላያ እንዲጠናከር ማዘዛቸዉ ተሰማ።የአሜሪካዉ ሴናተር የጆን ሊበርማን አፀፋ ደግሞ ኢራንን እንደብድብ የሚል ሆነ።ዉዝግብ ዛቻዉ ባየለበት መሐል-ኢራን ሬዳር የማይቆጣጣረዉ አዉሮፕላን ማምረቷን አስታወቀች

default

ጉባኤዉ

08 02 10

የሁለት ተጠራጣሪ አለም ሰዎች-ክርክር።

«በጣም አስፈላጊዉ ነጥብ ይሕ ፖለቲካዊ ፍቃደኝነት ነዉ።በግሌ-ፖለቲታዊዉ ፍቃደኝነት እንዳለ ይሰማኛል።»

የኢራኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር-ማኑቼሕር ሙታኪ

«ከናንተ በኩል የሚቀርብ ማንኛዉም አይነት እቅድ በጣም በተቻለ ፍጥነት ለIAEA በፅሁፍ የሚቀርብ መሆን አለበት ብዬ ከልቤ ተስፋ አደርጋለሁ።መደራደሪያ ነጥብ ይሆናልና።አለበለዚያ ወሬ ብቻ እንደሆነ ይቀራል።»

የሲዊድኑ ወጪ ጉዳይ ሚንስትር ካርል ቢልት።ሙንሽን ወይም ሙዩኒክ። አርብ።ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።ከአርብ-እስከ ትናንት የዘለቀዉ የሙዩኒኩ የአለም የፀጥታ ጉባኤና የኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር ያጫረዉ አዲስ ዉዝግብ ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁን ቆዩ።

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ሥልጣን በያዙ በሁለተኛዉ ሳምንት ግድም አምና ተደርጎ እንደነበረዉ ጉባኤ የአሜሪካዉ ምክትል ፕሬዝዳት ጆን ባይደን አልነበሩም።የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል፥ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳት ኒኮላ ሳርኮዚም በሌላ ጉዳይ ተጠምደዉ ነበር።ጉባኤዉ ግን ከ1962 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ጀምሮ እንደነበረዉ በርግጥ አልታጎለም።ከአርባ ሥድስት ሐገራት ባለሥልጣናት፥ ዲፕሎማቶች፥ የፀጥታ ጉዳይ ባለሙያዎች በድምሩ ከሰወስት መቶ የሚበልጡ ሰዎች ተካለዉበታል።

ከጅምሩ የጉባኤዉ አዘጋጆች እንዳስታወቁት በሰወስት አለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል ነበር-አላማ እቅዱ።የአፍቃኒስታን የወደፊት ጉዞ-እንዴትነት፥ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ይዘት እና የመካከለኛዉ ምሥራቅ ሁኔታ።ጉባኤተኞች ድርድርና ትብብርን የሚያጠናክሩበትን ብልሐት፥ የጦር መሳሪያን ለመቀነስ የሚረዱ አዳዲስ ሐሳቦችን የሚቃኙበትን ሥልት ፥በአፍቃኒስታንና በመካከለኛዉ ምሥራቅ ሠላም ለማስፈን የሚደረገዉ ጥረት የሚጠናከርበትን ዘዴ ይፈልጋሉ ነበር።የጉባኤዉ አዘጋጆች መሪ፥-ቮልፍጋንግ ኢሺንገር

«የፀጥታዉ ማሕበረሰብ (ሐሳቦቹ) መቼና እንዴት ገቢር ሊሆኑ እንደሚችሉ ማወቅ ይፈልጋል።የጦር መሳሪያ ቅነሳና ቁጥጥሩ እንዴት (ተግባራዊ) ይሆናል።በመካከለኛዉ ምሥራቅ ምን እየተፈፀመ ነዉ?-እነዚሕ ነጥቦች ናቸዉ ሙኒኩ (ጉባኤ) ለዉይይት የምናቀርባቸዉ።»

ከሁለት ሳምንት በፊት የሐያል-ሐብታሙን አለም ባለሥልጣናት ለንደን ላይ ያነጋገረችዉ አፍቃኒስታን በሙኒኩም ጉባኤ በርግጥ አልተረሳችም።የወደፊት ሠላም ፀጥታዋ ብዙ አነጋግሯል። የለንደን ጉባኤተኞች የተስማሙበትን ሐሳብ ገቢር ለማድረግ የሚጥሩት ወይም ቃል የገቡት የሐገሪቱ ፕሬዝዳት ሐሚድ ካርዛይ እንዳሉት ሐገራቸዉ የራሷን ፀጥታና ደሕንነት በራሷ ሐይላት የምትጠብቅበት ጊዜ እሩቅ አይደለም።

Westerwelle / Sicherheitskonferenz / München

ቬስተርቬለ

«አፍቃኒስታን የተባባሪዎቻችንና የወዳጆቻችን ሸክም መሆን አትፈልግም።አፍቃኒስታን በቅርቡ የራስዋን ግዛት፥ሕዝብና ፀጥታ በአፍቃኖች ሥልት መከላከል ትፈልጋለች።»

በቅርቡ እዚያዉ አፍቃኒስታን የአፍቃኖች ጉባኤ ለመጥራት ያቀዱት ካርዛይ ያሉት መያዝ-መሳቱ ወደፊት የሚታይ ነዉ-የሚሆነዉ።ደግሞ ፍላጎት-የድርጊት ምልክት ሊሆን አይችልም።ያም ሆኖ የፕሬዝዳት ካርዛይ መልዕክት የሙኒኩ ጉባኤ በጦርነት የምትታመሰዉን ሐገራቸዉን አለመርሳቱን ማረጋገጡ አልቀረም።

ዩናይትድ ስቴትስ ለታይዋን ከስድት ቢሊዮን ዶላር የሚበልጥ የጦር መሳሪያ ለመሸጥ መወሰኗ የቻይናን ቁጣ በቀሰቀሰ ማግስት፥ ሩሲያ ለሊቢያ የ1.8 ቢሊዮን ዶላር የጦር መሳሪያ ለመሸጥ በተስማማች ሰሞን የተሰየመዉ ጉባኤ ሥለ ጦር መሳሪያ መነጋገሩም አልቀረም።የጠመንጃ ሽያጭ ንግዱ እንደደራ የጦር መሳሪያ ቅነሳ-ድርድር ብሎ መርሕ ገቢር መሆኑ ነዉ-አጠያያቂዉ።

እስከ ጉባኤዉ መክፈቻ ዕለት ብዙም ያልተነገረዉ አንድ ሁነት ግን አጠያያቂዉን ለመጠየቅ፥ ሥለ ጦር መሳሪያ-ሽያጭ ቅነሳ፥ ሥለ አፍቃኒስታን፥ ሥለ መካካለኛዉ ምሥራቅ ለመነጋገር የነበረዉን እቅድ ፍላጎት ጨርሶ ባያጠፋዉ ሁሉንም ሸፍኖታል።-የኢራን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጉባኤዉን መቀየጥ። አርብ።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ማኑቼሕር ሞታኪ ብዙም ሳይጠበቁ በጉባኤዉ ላይ መገኘታቸዉ ኢራን ከምዕራባዉያን ሐገራት ጋር ለገጠመችዉ ዉዝግብ የመጨረሻ መፍትሔ አይደለም።

የጉባኤዉን ሒደት በአዲስ ጎዳና ለማሾር-ሌሎቹን ርዕሶች ጀቡኖ በኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር ላይ እንዲያተኩር ለማድረግ በርግጥ በቂ ነበር።ከዚሕም በላይ የጉባኤዉ አስተባባሪ ቮልፍጋንግ ኢሺንገር እንዳሉት ሥለ አወዛጋቢዉ የኑክሌር መርሐ-ግብር የኢራንን መልዕክት ለመስማት፥ የድርድሩ ሒደት መቀጠል አለመጠሉን ለማወቅም ትልቅ ትርጉም አለዉ።

«ባለን አጭር ጊዜ ዉስጥ ከኢራን ጋር ሥለ ኑክሌር መርሕ መነጋገር ሥለሚቻልበት ሁኔታ ከኢራን መልዕክተኞች ጋር ለመወያየት

Sicherheitskonferenz in München

ሞታኪ

እንሞክራለን።»

የኢራንን አቋም ለመስማት አጋጣሚዉ ጥሩ ነበር።አመታት ያስቆጠረዉን ዉዝግብ በድርድር ለመፍታት ግን ብዙም የተከረዉ የለም።ሞታኪ የምናደርገዉ ሁሉ የአለም አዉቶሚክ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን የ(IAEA) ደንብ በሚያዘዉ መሠረት ነዉ-ባይ ናቸዉ።

«የኛ እንቅስቃሴ በሙሉ በIAEA መርሕና ቁጥጥር መሠረት የሚደረግ ነዉ።እናንተ የምታወሩት ሥለ ዩራንየም ማብላላት ማቋረጥ ነዉ።እኛ እንዳደረግ ነዉ ታዉቃላችሁ።ከEU-3፥ ከ3+3 እና በዚያን ጊዜ በነበሩት በሌሎቹም ሥልት መሠረት አድርገነዋል።ከሁለት አመት በልጦታልም።ዉጤቱ በመጨረሻ ምንድ ነዉ-የሆነዉ?ለኢራን አንድ ማዕቀፍ ሰጣችሁ።የዚያ ማዕቀፍ ዋና አካል ኢራን ዉስጥ ዩራኒየም ማብላላት አትችሉም የሚል ነበር።»

የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተርቬለ ግን የሙታኪን አባባል አልተቀበሉትም።

«እጃችን እንደተዘረጋ ነዉ።እስካሁን ግን የጨበጠዉ ነገር የለም።ተባብሮ ለመስራት አዲስ መርሕ መኖር ካለበት ከኢራን የሚሰሙት ቃላት ምግባር ሊከተላቸዉ ይገባል።»

የሲዊድኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ካርል ቢልት ደግሞ ከጀርመኑ አቻቸዉም እልፍ-ብለዉ ሙታኪን አናምናችሁም ነዉ-ያሏቸዉ።

«ማለቴ አገልግሎት የማስይሰጥ ማብላያ አላችሁ።ከሩሲያ ማቀጣጠያ (ነዳጅ) ተሰጥቷችኋል።የረቀቀ የማብላላት መርሐ-ግብር ዘርግታችኋል።ይሕ በትክክል ጥርጣሬን አስከትሏል።የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ያላችሁን በጥሞና ማድመጥ፥ማቋረጥ፥ ይሕን ግልፅ ማድረግ ለናንተ ጠቃሚ ነዉ-አዉዳሚ ጦር መሳሪያ እንዳይመረት የሚያግደዉ (ዉል) በሚያስገድደዉ፣ በተስማማንበትና በሚሰጣችሁ መብት መሠረት።»

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት የባራክ ኦባማ የፀጥታ ጉዳይ አማካሪ ጀምስ ጆንስ አከሉበት።

«በሩ እንደተከፈተ ነዉ።ይሁንና መርሐችን የሚያተኩረዉ የኑክሌር ጦር መሳሪያ የታጠቀች፥ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ለማምረት አቅሙ ያላት ኢራን ተቀባይነት የላትም በሚለዉ ትወራ ነዉ።የአለም ፍላጎትን (የሚፃረር ነዉ)።በመካከለኛዉ ምሥራቅም የጦር መሳሪያ ምርት እሽቅድምድም ያስከትላል።»

የሙኒኩ ጉባኤ-ብዙዉን ርዕሶችን አደብዝዞ የኢራንን የኑክሌር ዉዝግብ እንዳጦዘ-የኢራኑ ፕሬዝዳት ማሕሙድ አሕመዲኒጃድ ተጨማሪ የዩራንዮም-ማብላያ ተቋማት እንዲሰሩ ወይም ያላዉ ማብላያ እንዲጠናከር ማዘዛቸዉ ተሰማ።የአሜሪካዉ ሴናተር የጆን ሊበርማን አፀፋ ደግሞ ኢራንን እንደብድብ የሚል ሆነ።ዉዝግብ ዛቻዉ ባየለበት መሐል-ኢራን ሬዳር የማይቆጣጣረዉ አዉሮፕላን ማምረቷን አስታወቀች።ዉዝግብ ዛቻዉ ማሳረጊያ ግን ከኒዮርክ፥ከብራስልስ፥ ከዋሽግተን፥ ከቴሕራን እየተጠበቀ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

Dw,Agenturen

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic