የሙኒኩ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ስብሰባና ተቃውሞው | ኤኮኖሚ | DW | 18.05.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የሙኒኩ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ስብሰባና ተቃውሞው

የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና የንግድ ማኅበረሰብ አባላት የጀርመን ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ገብተው መዋዕለ-ንዋይ እንዲያፈሱ ለማባበል ሐሙስ ግንቦት 4 ቀን፣ 2008 ዓ.ም. ሙይንሽን ከተማ ጀርመን ውስጥ ተሰብስበው ነበር። ስብሰባው ቀኑን ሙሉ ሲኪያሄድ ኢትዮጵያውያን አዳራሹ ውስጥ እና ከአዳራሹ ውጪ የተቃውሞ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:27
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:27 ደቂቃ

የኢንቨስትመንት ጉባኤና ተቃውሞ በሙኒክ

ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ሙይንሽን ከተማ የሚገኘው የሙይንሽኖች የጥበብ ቤት (Münchner Künstlerhaus) የተሰኘው አዳራሽ ጥበቃዎች ሥራ በዝቶባቸው ነው የዋሉት።

«ኢትዮጵያ የአፍሪቃ አዲሷ የንግድ መዳረሻ» በሚል በተሰየመው ስብሰባ ለመሳተፍ ኢትዮጵያውያን ባለሥልጣናት እና ባለሀብቶች እንዲሁም ጀርመናውያን ባለወረቶች ወደ አዳራሹ መግባት የጀመሩት ጠዋት ረፋዱ ላይ ነበር። ስብሰባው የተጠራው ጀርመናውያኑ ባለሀብት ኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ-ንዋይ ቢያፈሱ ምን ያኽል ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ለማሳመን ነው። ከውጭ ደግሞ ስብሰባው ከመጀመሩ አንስቶ ኢትዮጵያውያን የተቃውሞ ድምጻጽ ሲያሰሙ ነበር።

ካለፉት ጥቂት ዓመታት አንስቶ የምዕራባውያኑ የመገናኛ አውታሮች ኢትዮጵያ ሚሊየነሮችን በፍጥነት እየፈጠረች ነው በሚል «የአፍሪቃ አንበሳ» የተሰኘ ስያሜ ሰጥተዋታል። በዐሥር ሚሊዮኖች የሚጠጉ የሀገሪቱ ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅት የረሀብ አደጋ እንዳንዣበበባቸውም የመገናኛ አውታሮቹ ሳይዘግቡ አላለፉም። የሀገሪቱ መንግሥት በበኩሉ በየዓመቱ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገብን ነው ሲል በተደጋጋሚ ይደመጣል። 140 ግድም ታዳሚዎች በተገኙበት የሙይንሽኑ አዳራሽም ይኸው አባባል ተደግሟል።

በእርግጥ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ሁለት ዓመታት በግማሽ መቀነሱን ነው የሚናገረው። በዋናነትም በሀገሪቱ የተከሰተው ድርቅን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከ10.2 በመቶ ወደ 4.5 በመቶ ማሽቆልቆሉን ጠቅሷል። በሙሽይንሽኑ ተሳታፊ የነበሩት፤ አዲስ አበባ በሚገኘው የጀርመን ኤምባሲ የኢኮኖሚ አታሼ ዶ/ር ፓትሪክ ቬግነር በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ የጀርመን ኩባንያዎች ላይ ተጽዕኖ «እምብዛም ነው»ብለዋል። «ለጀርመን ኩባንያዎች ድርቁ ያን ያኽል ተጽዕኖ አልፈጠረም። ኢትዮጵያ ውስጥ በግብርና ዘርፍ የሚንቀሳቀሱ ብዙ ባለሐብቶች እስካሁን የሉንም። ስለዚህ ድርቁ የጀርመን መዋዕለ-ንዋይ አፍሳሾች ላይ ያን ያኽል ተጽዕኖ ፈጥሯል ብዬ አላስብም» ሲሉ አክለዋል።

በሙይንሽኑ ጉባኤ የኢትዮጵያ ልዑካን ከጀርመን ባለሐብት እና ባለሥልጣናት ጋር

በሙይንሽኑ ጉባኤ የኢትዮጵያ ልዑካን ከጀርመን ባለሐብት እና ባለሥልጣናት ጋርኢትዮጵያ ላለፉት 12 ዓመታት በአማካኝ የ10.6 በመቶ እድገት ማስመዝገቧን የዓለም ባንክ መስክሮዋል ሲሉ በሙይንሽኑ ስብሰባ የተናገሩት አቶ ዘመድነህ ንጋቱ፤ ኢትዮጵያ በአፍሪቃ ኢኮኖሚያቸው ቀዳሚ ከሆኑ አገራት ትመደባለች ብለዋል።
«አፍሪቃ ውስጥ በኢኮኖሚ ቀዳሚዋ ናይጀሪያ ናት፤ ደቡብ አፍሪቃ ነበረች መሪዋ ከሁለት ዓመት በፊት ግን ለናይጀሪያ ቦታውን ለቃ ሁለተኛ ሆናለች። ሦስተኛ አንጎላ ናት። አራተኛ ማን እንደሆነች ገምቱ?» ሲሉ ተሰብሳቢዎቹን በማጠየቅ ወዲያው« አዎ ኢትዮጵያ ናት» ሲሉ ተናግረዋል።

የኧርነስት ያንግ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘመድነህ ንጋቱ የመንግሥት አማካሪም ናቸው። ከእሳቸው ንግግር ቀደም ብሎ በስብሰባው መክፈቻ ወቅት ዶ/ር ይናገር ደሴም ተሰብሳቢዎቹን የሚያባብል ንግግር አሠምተው ነበር። የኢትዮጵያ የንግድ ማኅበረሰብን እና የመንግሥት ተወካዮች ልዑካንን የመሩት የብሔራዊ ዕቅድ ኮሚሽን ሚንሥትር ዶ/ር ይናገር ጀርመናውያኑ ኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ንዋይ ቢያፈሱ ምን ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ዘርዝረዋል።

«ኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋይ ለማፍሰስ ውሳኔ ላይ እንድትደርሱ የሚያስችሉ በርካታ ነገሮች አሏት» በማለት የጀመሩት ሚንስትሩ ፦« አመርቂ የንግድ መስክ፣ የተረጋጋ ፖለቲካ፣ አስተማማኝ የኢኮኖሚ መርኆዎች፣ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ፣ ያልተነካ የተፈጥሮ ሀብት ፣ ሊሠለጥን የሚችል የሰው ኃይል፣ ውድ ያልሆነ የኃይል አቅርቦት፣ ሰፊ እና እምብዛም ተፎካካሪ የሌለበት ገበያ፤ እነዚህ በመላ በኢትዮጵያ ጎጂ ያልሆነ መዋዕለ-ንዋይ ለማፍሰስ ጠቃሚ ግብአቶች ናቸው» ሲሉም አክለዋል።

ሚንሥትሩ ንግግራቸውን በሚያሰሙበት ወቅት ግን ከተሰብሳቢዎች ጋር ተመሳስለው የገቡ ኢትዮጵያውያን «የኢትዮጵያ መንግሥት አምባገነን ነው፣ ኦሮሞ ተማሪዎችን መግደላችሁን አቁሙ» ሲሉ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተቃውሞዋቸውን አሠምተዋል።

የተቃውሞ ድምጻቸውን ያሰሙት ኢትዮጵያውያን ከአዳራሹ በጥበቃዎች ታጅበው ሲወጡ ስብሰባው ቀጥሏል። ከውጭ የተሰባሰቡት ኢትዮጵያውያን የተቃውሞ ድምጽም መሰማቱ አልተቋረጠም።

በሙይንሽኑ የኢንቨስትመንት ጉባኤ ተቃዋሚዎች ከአዳራሹ ውጪ የተቃውሞ ድምጽ ሲያሰሙ፤ በከፊል

በሙይንሽኑ የኢንቨስትመንት ጉባኤ ተቃዋሚዎች ከአዳራሹ ውጪ የተቃውሞ ድምጽ ሲያሰሙ፤ በከፊልጀርመናውያን ባለሐብቶች ስለኢትዮጵያ ያላቸው ግንዛቤ እና አመለካከት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መጥቷል ያሉት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የጀርመን ተወካይ አምባሳደር ኩማ ደመቅሳ በሙይንሽኑ ስብሰባ የተከሰተውን ተቃውሞ በተመለከተ «በአፈጻጸም የሚያጋጥሙ ጉድለቶች፣ የመልካም አስተዳደር ሌሎች ጉድለቶች ብለን ራሳችን የለየናቸው ችግሮች ትክክለኛ እና መመለስ ያለባቸው ናቸው ብለን እንወስዳለን። ነገር ግን» ሲሉ ቀጠሉ አምባሳደሩ «ነገር ግን፤ የተቃዋሚዎቹ መነሻ እኔ በጣም የሚያሳፍረኝ፤ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ፤ ለምሳሌ የዛሬውን ከወሰድክ ያልሆነ ቃል እየተጠቀሙ ከመጮኽ የስብሰባው አካል ሆነው የተሻለ ሐሳብ ካላቸው የተሻለ ሐሳብ ማራመድ ይችሉ ነበር። የሠለጠነ ተቃውሞ ማለት ይኼ ነው» ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደምም በርሊን ከተማ ላይ በተደረገው ተቃውሞ ተሳታፊ እንደነበሩ ለተቃውሞዋቸው ምንም ምላሽ እንዳላገኙ የተናገሩት የተቃውሞ ሰልፈኛ በድጋሚ ሙይንሽን መምጣታቸውን ገልጠዋል።

በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት አንስቶ የኢትዮጵያ መንግሥት በምዕራባውያን መንግሥታት ዘንድ ዋነኛ ተባባሪ ተደርጎ ይወሰዳል። ከሀገሪቱ መልክአ-ምድራዊ አቀማመጥ እና በአካባቢው ሃገራት ካለው የኃይል አሰላለፍ አንጻር ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያን ሥልታዊ ቦታ ላይ የምትገኝ ጠቃሚ አገር ሲሉ አጥብቀው ይዘዋል። በርካታ ተቺዎች ግን ሀገሪቱ ውስጥ በመዋዕለ-ንዋይ ስም ነዋሪዎች ሲንገላቱ፣ ለእስር ሲዳረጉ እና ሲገደሉ የምዕራቡ ዓለም መንግሥታት ዐይተው እንዳላዩ አለያም በአገም ጠቀም ብቻ አስተያየት ይሰነዝራሉ ሲሉ ይተቻሉ።

ጀርመን የኢትዮጵያ ሸቀጦችን በመግዛት ከሶማሊያ፣ ከኔዘርላንድ፣ ከሣዑዲ ዐረቢያ እና ከቻይና ቀጥላ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ትገናለች። በዋናነትም ቡና እና ጨርቃጨርቆችን ከኢትዮጵያ ስታስገባ ማሽኖችን እና መኪናዎችን ወደ ኢትዮጵያ ትልካለች። በዚህ የንግድ ልውውጥ በ2016 ዓመት ኢትዮጵያ 209 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ስታስገባ፤ ጀርመን በበኩሏ 238 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ አግኝታለች። የጀርመን ኤምባሲ የኢኮኖሚ አታሼ ዶ/ር ፓትሪክ ቬግነር መንግሥታቸው የኢትዮጵያ መንግሥት በመዋዕለ-ንዋይ ዘርፍ ማሻሺያዎችን እንዲያደርግ በቅርበት እየሠሩ መሆናቸውን ገልጠዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ስለልማት ሲናገር በኩራት የሚያነሳው የቀላል ባቡር በአዲስ አበባ ከተማ አገልግሎት ሲሰጥ

የኢትዮጵያ መንግሥት ስለልማት ሲናገር በኩራት የሚያነሳው የቀላል ባቡር በአዲስ አበባ ከተማ አገልግሎት ሲሰጥበሙይንሽኑ አዳራሽ የተገኙት አምባሳደር ኩማ ደመቅሳ እንደተናገሩት ከሆነ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ከ140 በላይ ጀርመናውያን ባለሐብቶች ይገኛሉ።

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2007 ዓመት አንስቶ ኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ-ንዋይ አፍስሶ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው የግል ኩባንያ (INPROCON) ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚሻኤል ፍሪክ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ ተጠቃሚ መሆኑን ለሙይንሽን ተሰብሳቢዎች ተናግረዋል።

«በሀገሪቱ ከፍተኛ የቢዝነስ (ንግድ) ዕድል አለ። ሀገሪቱ ጥሩ የንግድ ድባብ አላት» ያሉት ባለሐብት አክለው ሲናገሩም፦ «ኢትዮጵያ ከአፍሪቃ በህዝብ ብዛት ሁለተኛ መሆኗ፣ የሕዝቡ እንግዳ ተቀባይነት እና ልዩ ባህል፣ በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ ደኅንነቱ አስተማማኝ በመሆኑ ነው መዋዕለ-ንዋይ ያፈሰስነው» ብለዋል። ሌቨርኩሰን ከሚባለው የጀርመን ከተማ ረዥም ርቀት አቋርጣ ለተቃውሞ ሙይንሽን የመጣችው እና ጂጂ እንደምትባል የገለጠችው ሰልፈኛ ከቀዬው የሚፈናቀለው ኢትዮጵያዊ ተገቢው ካሣ ሊሰጠው ይገባል ትላለች።

«ለአንድ አገር እድገት ኢንቨስትመንት የግድ ነው። ይገባኛል አውቃለሁ። ግን ሰውን ወዴት እያደረከው ነው? ወዴት እያሳደድከው ነው? ወዴት እየወሰድከው ነው? ለዛ ሰው ተመሳሳይ ቦታ እና ተመሳሳይ ገንዘብ ካሣ ሰጥተኸው ያንን ሰው ብታስነሳ እሺ፤ ግን ያለምንም ካሣ ያለምንም ተመሳሳይ ገንዘብ እና ያለምንም ተመሳሳይ ቤት አንድን ገበሬ ብታስነሳ እና ለችግር ብታጋልጠው ለኢትዮጵያ የወደፊቱ ዕድል ምንድን ነው ነው?»

በሙይንሽኑ ስብሰባ የመንግሥት ተወካዮች ጀርመናውያን ባለሐብቶችን ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ ቀኑን ሙሉ ያኪያሄዱት ስብሰባ ከሰአት ከዘጠኝ ሰአት በኋላ ቢጠናቀቅም ከአዳራሹ ውጪ ኢትዮጵያውያኑ የሚያሰሙት ተቃውሞ ግን እንደቀጠለ ነበር።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic