1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሙባረክ ዲስኩርና የህዝቡ ቁጣ

ረቡዕ፣ ጥር 25 2003

ከሥልጣን እንዲወርዱ ለአንድ ሳምንት በአደባባይ ተቀውሞ የተጠየቁት የግብፁ ፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክ በሚቀጥለው ምርጫ እንደማይወዳደሩ አስታወቁ ።

https://p.dw.com/p/QxgK
ሆስኒ ሙባረክምስል AP

ሙባረክ ትናንት ማምሻውን ለህዝባቸው ባሰሙት ንግግር ከሀገር እንዲወጡ በተደጋጋሚ ጥሪ ላቀረቡላቸው ወገኖችም ፣ ሀገራቸውን ግብፅን ለቀው የትም እንደማይሄዱ አረጋገጡ ። የሙባረክ ንግግር በአስቸኳይ እንዲወርዱ ሲጠይቅ የከረመውን ህዝብ አስቆጥቷል ። ሙባረክ ስልጣናቸውን እስካላስረከቡ ድረስ ተቃውሞው መቀጠሉ እንደማይቀር ህዝቡ እያስጠነቀቀ ነው ። ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ተመሳሳይ አቋም ይዘዋል ። ባየሙባረክ የቅርብ ወዳጅ ዩናይትድ ስቴትስ በግብፅ ስርዓቱን የጠበቀ ሽግግር እንዲካሄድና ይህም አሁኑኑ እንዲጀመር አሳስባለች ። የትናንት ምሽቱን የፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክን ንግግር ግብፃውያን በታላቅ ጉጉት ነበር የጠበቁት ። 10 ደቂቃ የወሰደው የሙባረክ የቴሌቪዥን ንግግር ግን ለአብዛኛዎቹ ዜጎች ፍፁም ተስፋ አልሰጠም ። ለ 30 ዓመታት ከገዙዋቸው ከሙባረክ የጠበቁትንና የፈለጉትን አልሰሙም ። ሙባረክ በትናንቱ ንግግራቸው በሚቀጥለው ምርጫ እንደማይወዳደሩ ተናግረው ሥልጣናቸውን ግን እንደተጠየቁት በአስቸኳይ እንደማይለቁ ከዚያ ይልቅ ቀስ በቀስ የማስረከብ እቅድ እንዳላቸው ነበር ያስረዱት ። «የመጀመሪያው ሀላፊነቴ በግብፅ ሰላም እና መረጋጋትን ማስፈን ነው ። በፕሬዝዳንት ዘመኔ በሚቀሩኝ ወራት ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ተግባራዊ እንዲሆን የሚያስችሉ እርምጃዎችን እወስዳለሁ ።» ሙባረክ ብዙዎች እንደሚጠብቁት እና ደጋግመው እንደጠየቁት ሀገር ለቀው የመውጣት ሀሳብ እንደሌላቸውም ግልፅ አድርገዋል ፤ ሞቴ በትውልድ ሀገሬ ነው የሚሆነው ሲሉ ። በዚሁ አጋጣሚ ግብፅ የኖርኩባት ለሉዓላዊነቷ የተዋጋሁላት ጥቃቷን የተከላከልኩላት እና ጥቅሞቿንም ያስጠበቅኩላት ሀገሬ ናትም በማለት ለሀገራቸውን ደህንነት እና ጥቅም ያደረጉትን አስተዋፅኦ ዘርዝረዋል ። ህገ መንግስቱን እንደሚያሻሽሉና ሙስናን እንደሚዋጉም ቃል ገብተዋል ። የፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክን ንግግር በታህሪር ወይም በነፃነት አደባባይ በፅሞና የተከታተለው ከአንድ ሚሊዮን የሚልቅ ህዝብ ንግግሩ እንዳበቃ ቁጣውን ማስተጋባት ቀጠለ ። እርስዎ ለቀው እስካልሄዱ ድረስ እኛም ጥለን አንሄድም ሲል ። ሙባረክ በአስቸኳይ ከሥልጣን እንዲሰናበቱ በተደጋጋሚ ጥሪውን ሲያስተጋባ የከረመው ህዝብ ወደፊት አደርጋለሁ ያሉትን አልተቀበለም ። ይልቁንም ንግግራቸው ለተጨማሪ አመፅ የሚያነሳሳና እልቂትንም የሚጋብዝ ነው ያሉም ነበሩ ። «ይህ ሰው እየተነኮሰን ነው ። ይህ ሰው ግብፅ በደም እንድታጠብ ነው የሚፈልገው » ሙባረክ ቀድሞም እንደሚያደርጉት ለህዝቡ ጥያቄ ጆሮ ዳባ ልበስ እያሉ ነው ያሉት ተቃዋሚ ቡድኖችም በበኩላቸው ሙባረክና መንግስታቸው ሥልጣን እንዲለቁ ያቀረቡት ጥሪ መልስ እስኪያገኝ ድረስ ፣ በተጀመረው የአደባባይ አመፅ መግፋታችን የማይቀር ነው ሲሉ የማያወላዳ አቋማቸውን አሳውቀዋል ። ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ደግሞ በግብፅ ህዝባዊ ንቅናቄ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል ። በግብፅ ተሀድሶ እና ነፃ ምርጫ እንዲደረግ ጥሪ ያቀረበችው አሜሪካን ሙባረክ በኃይል ቢወርዱ አክራሪ ሙስሊሞች ኃይል ያገኛሉ የሚል ስጋት ያደረባት ይመስላል ። ትናንት ለግማሽ ሰዓት ያህል ሙባረክን ጋር በስልክ ያነጋገሩት የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ሙባረክ ከሥልጣን እንዲወርዱ በቀጥታ አልጠየቁም ። ይልቁንም በተዘዋዋሪ መንገድ ሥልጣን የሚለቁበትን ወይም ደግሞ በርሳቸው አባባል ሽግግር የሚደረግበትን መንገድ እንዲያመቻቹ ጥሪ አቀረቡ እንጂ ። «አሁን የግብፅን መሪዎችን የመምረጡ ድርሻ የማንም ሌላ አገር አይደለም ። ይህን ማድረግ የሚችሉት የግብፅ ህዝቦች ብቻ ናቸው ። ግልጹ ነገርና ለፕሬዝዳንት ሙባረክ ዛሬ የጠቆምኩዋቸው በኔ ዕምነት ስርዓቱን የጠበቀ ሽግግር ትርጉም ያለው መሆን ያለበት ፤ ሰላማዊም መሆን አለበት ፤ ዛሬ መጀመር አለበት ። ከዚህ በተጨማሪም ሂደቱ የግብፃውያንን ድምፅ እና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በሰፊው ማካተት ይኖርበታል ። ነፃ እና ትክክለኛ ወደ ሆኑ ምርጫዎች ሊያመራ ይገባል ። ውጤቱም በዲሞክራሲያዊ መርሆዎች ላይ የተመሰረተ ብቻ ሳይሆን ለግብፅ ህዝብ ምኞት መልስ የሚሰጥ መንግስት መሆን አለበት ። » ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ የ82 ዓመቱ ሙባራክ በአስቸኳይ የሥልጣን ሽግግሩን እንዲጀምሩ ጠይቀዋል ። ጀርመንም ዋናው ቁም ነገር ሙባረክ ትናንት የተናገሩዋቸው ተግባራዊ ማድረጋቸው ነው ብላለች ። የታህሪር አደባባዩ ተቃውሞ ዛሬም ቀጥሏል ። ዛሬ በዚህ አደባባዩ የተገኙት የሙባረክ ደጋፊዎችም ናቸው ። ተቃዋሚዎችና ደጋፊዎች በመጋጨታቸው ጣልቃ የገባው ፖሊስ የተወሰኑትን አስራል ። የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው ዘጠነኛ ቀኑን በያዘው በግብጹ ህዝባዊ ንቅናቄ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ወደ 300 ይጠጋል ከ 3 ሺህ በላይ ደግሞ ቆስለዋል ።

Ägypten Kairo Proteste Demonstrationen Zusammenstöße
ደገፋዎችና ተቃዋሚዎች ሲጋጩምስል AP
Obama Rede zur Lage der Nation Kongress
ኦባማምስል AP
NO FLASH Ägypten Mubarak Kairo Proteste Demonstration 01.02.2011
ሰልፈኛው በከፊልምስል picture alliance/dpa

ሂሩት መለሰ

 ነጋሽ መሐመድ