የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ፍርድ | ኢትዮጵያ | DW | 03.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ፍርድ

በኢትዮጵያ የሙስሊም መፍትሄ ኮሚቴ አባላት በዛሬው ቀን ከሰባት እስከ 22 አመታት እስራት ተፈረደባቸው። በእነ አቡበከር አህመድ የክስ መዝገብ የሽብርተኝነት ክስ የቀረበባቸው 18 ተከሳሾች ከብይኑ በፊት የቅጣት ማቅለያ አላቀረቡም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:29
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:29 ደቂቃ

የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ፍርድ

የኢትዮጵያ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ የወንጀል ችሎት በእነ አቡበክር አህመድ የክስ መዝገብ የተከሰሱ 18 ተከሳሾችን ከ7 አመት እስከ 22 አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ቀጥቷቸዋል ። በአሸባሪነት ክስ የተመሰረተባቸው መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ጠበቃ የሆኑት አቶ መሃመድ አብደላ ፍርድ ቤቱ በእነ አቡበከር አህመድ የክስ መዝገብ የቀረቡትን ተከሳሾች በአራት ከፍሎ ውሳኔ መስጠቱን ለዶይቼ ቨሌ ተናግረዋል። በዚህም መሰረት አቡበክር አህመድ፣ አህመዲን ጀበል፣ ያሲን ኑሩ እና ከሚል ሸምሱ በ 22 አመት፤ በድሩ ሁሴን፣ ሳቢር ይርጉ፣መሃመድ አባተ፣አቡበክር አለሙ እና ሙኒር ሁሴንን እያንዳንዳቸውን በ18 አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ወስኗል።

በእነ አቡበከር አህመድ የክስ መዝገብ ሼህ መከተ ሙሄ፣ አህመድ ሙስጠፋ፣ ሼህ ሰኢድ አሊ፣ ሙባረክ አደም እና ካሊድ ኢብራሂም በሶስተኛው ምድብ የ15 አመት ጽኑ እስራት እንዲሁም ሙራድ ሽኩር፣ ኑሩ ቱርኪ፣ ሼህ ባህሩ ዑመር እና የሱፍ ጌታቸውን በ7 አመት ጽኑ እስራት እንደተበየነባቸው ጠበቃ መሃመድ አብደላ ተናግረዋል። ከሳሽ አቃቤ ህግ «ተከሳሾች ወንጀሉን የፈጸሙት በስምምነትና በአንድነት ነው» የሚል የቅጣት ማቅለያ ያቀረበ ሲሆን ተከሳሾች«መጀመሪያ ጥፋተኛ የተባሉበት ፍርድ ላይ የማይስማሙ በመሆኑ፤ ሲጀመርም ንጹሃን ነን ብለው የተከራከሩ በመሆኑና በፍርድ ቤትም ጥፋተኛ መባላቸውን የማያምኑበት ስለሆነ» የቅጣት ማቅለያ አለማቅረባቸውን የተከሳሾች ጠበቃ ተናግረዋል።

ከአራት አመታት በፊት የእስልምና እምነት ተከታዮች በመንግስት የተባረሩት የአወሊያ አስተዳደሮች ወደ ቦታቸው ይመለሱ፤መንግስት በመጅሊስ ምርጫ ጣልቃ ሊገባ አይገባም እና የአል-ሃበሽ አስተምህሮ በግድ ልንቀበል አይገባም በሚሉ ተቃውሞዎች የተጀመረውን ልዩነት ለመፍታትና ለማሸማገል በፈቃደኝነት የተሰበሰቡት የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ከታሰሩ ከሶስ አመታት በላይ አልፈዋል። አሁን ከ7-22 አመታት እስር የተበየነባቸው የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ህዝበ ሙስሊሙ ያነሳቸውን ጥያቄዎች በመያዝ ከመንግስት ጋር ድርድር ጀምረው ነበር። ድርድሩ ተቋርጦ ከመፍትሄ አፈላላጊዎች መካከል ሁለት ድርጅቶችን ጨምሮ ሰላሳ አንድ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው የሽብርተኝነት ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን፤ በክርክር ወቅት የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ሰዎችን እና ሁለት ድርጅቶችን አሰናብቷል። አሁን በ18 የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ላይ ውሳኔ ያሳለፈው የፍርድ ሂደት በእስልምና እምነት ተከታዮች፤የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና በተቃዋሚዎች ከፍተኛ ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል።

የተከሳሾች ጠበቃ አቶ መሃመድ አብደላ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ከደንበኞቻቸው ጋር በመነጋገር ይግባኝ እንደሚሉ ጠቁመዋል። ለዶይቼ ቨሌ አስተያየታቸውን የሰጡ ሰዎች በበኩላቸው ውሳኔው የጠበቁት መሆኑን ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች