የሙስሊም ሃገራት ትብብር ለፍልስጤም የመንግሥትነት ዕዉቅና ሰጠ | ዓለም | DW | 13.12.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የሙስሊም ሃገራት ትብብር ለፍልስጤም የመንግሥትነት ዕዉቅና ሰጠ

በኢስታንቡል የሚካሄደዉ የሙስሊም ትብብር ድርጅት በምህጻሩ OIC አባል ሃገራት ጉባኤ ኢየሩሳሌም የፍልስጤም ዋና ከተማ ናት ሲል ዕዉቅና ሰጠ። ይህ የተገለጸዉ የጉባኤዉ አስተናጋጅ ቱርክ ፕሬዝደንት ረቺፕ ጠይብ ኤርዶኻን  መንግሥታት ባፋጣኝ ለፍልስጤም ሀገር ዕዉቅና በመስጠት ኢየሩሳሌምን ዋና ከተማ አድርገዉ እንዲቀበሉ ዛሬ ጥሪ ካቀረቡ በኋላ ነዉ።

 የኢስታንቡል ጉባኤ የአሜሪካን ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እርምጃን የሚቃወም የሙስሊም ኅብረትን ለመመስረት የሚካሄድ ስብሰባ መሆኑ ነዉ የተገለጸዉ። በጉባኤዉ ላይ ከ57 የሙስሊም ትብብር ድርጅት አባል ሃገራት የተዉጣጡ ባለስልጣናት ተገኝተዋል። ኤርዶኻን ፕሬዝደንት ትራምፕ ኢየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማ ናት የሚል እዉቅና መስጠታቸዉን ይፋ ካደረጉ በኋላ ጠንከር ያለ ትችት ከሰነዘሩት የሃገራት መሪዎች አንዱ ናቸዉ።

«ዓለም አቀፍ ሕግ እና ፍትህን የሚያከብሩ ሃገራት በሙሉ ኢየሩሳሌምን እንደ ፍልስጤም ሀገር ዋና ከተማ አድርገዉ ዕውቅና እንዲሰጡ እጋብዛለሁ። ከዚህ የበለጠ መዘግየት የለብንም። እንደ ኢስላም ሃገራት ዋና ከተማዋ ኢየሩሳሌም የሆነች ሉዓላዊ እና ነፃ ፍልስጤምን መጠየቃችንን በፍፁም አንቋርጥም።»

የፍልስጤም ፕሬዝደንት ማህሙድ አባስ በበኩላቸዉ በመካከለኛዉ ምሥራቅ የሰላም ሂደት ዉስጥ ከእንግዲህ የአሜሪካንን ሚና እንደማይቀበሉ ለተሰብሳቢዎቹ ባደረጉት ንግግር አስታዉቀዋል። በጉባኤዉ ላይ ያልተገኙት የሳዉድ አረቢያዉ ንጉሥ ሳልማን ደግሞ ፍልስጤማዉያን ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን ዋና ከተማቸዉ የማድረግ መብት አላቸዉ ማለታቸዉን የፈረንሳይ የዜና ወኪል ዘግቧል።