የመጸዳጃ ቤት አገልግሎት ብሎም ንፅህና ለሁሉም | ጤና እና አካባቢ | DW | 24.11.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

የመጸዳጃ ቤት አገልግሎት ብሎም ንፅህና ለሁሉም

በዓለማችን 2,5 ቢሊዮን የሚሆነዉ ህዝብ አግባብ ያለዉ የንፅህና መጠበቂያ ስልት ተጠቃሚ ያለመሆኑ ነገር ለጤና እክል ከመጋለጡም በላይ የሰዉነት ክብርን የሚነካ እንደሆነበት ተገለጸ።

default

በናይሮቢ አንድ የህዝብ መጸዳጃ

መጸዳጃ ቤትን ባለመጠቀምና አግባብ ያለዉ የንፅህና ጥንቃቄ ካለማድረግ ችግር ጋ በተያያዘ በሚከሰተዉ የጤና እክልም 1,8 ሚሊዮን ሰዎች ህይወት በየዓመቱ እንደዋዛ እንደሚቀጠፍ ተመልክቷል። ከሟቾች አብዛኛዎቹ ደግሞ ህፃናት ምሆናቸዉ ነዉ የተገለፀዉ። ባለፈዉ ሳምንት ሐሙስ የዓለም የመፀዳጃ ቤት ቀን ታሰቦ ዉሏል። የመጸዳጃ ቤት አገልግሎት ብሎም ንፅህና ለሁሉም የተሰኘ አንድ ድረገጽ እንኳን በአዳጊና ደሃ አገራት በበለፀጉትም ቢሆን የመጸዳጃ ቤት ንፅህናን በመጠበቁ ረገድ ችግር ምኖሩን ይፋ አድረጓል። ልዩነቱ በበለፀጉት አገራት በግለሰቦች መኖሪያ ሳይሆን የህዝብ በሆኑ መጸዳጃ ቤቶች የንፅህና ጉድለቱ እንደሚታይ፣ በመጸዳጃ ቤቶቹ ለአገልግሎት የሚዉሉ ነገሮች እና እዚያ የሚጣሉ ቆሻሻዎች አወጋገድም ስርዓቱ እየተዛባ ምምጣቱን ድረገፁ ጠቁሟል።

በአዉሮዉያኑ ዘመን ቀመር ኖቬምበር 19ቀን የሚታሰበዉ የመጸዳጃ ቤቶች ቀን ከምንም በላይ ንፅህናን መጠበቅ፣ በአግባቡም መፀዳጃ ቤቶችን መጠቀም ጤናን ከመጠበቅ አኳያ አስፈላጊ መሆኑን ከዓለም ህዝብ ግማሽ ለሚሆነዉና አግባብ ያለዉ የመጸዳጃ ቤት ተጠቃሚ ላልሆነዉ የኅብረተሰብ ክፍል ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንደሆነ ተገልጿል።

ነገሩ ለሁለቱም ወገን መልዕክት አለዉ፣ መጸዳጃ ቤትን የመጠቀም እድል ያላገኘዉ ወገን ተገቢዉን የጤና ክብካቤ ለማድረግና እንደተቅማጥ ባሉ በሽታዎች እንዳይጠቃ ለመቀስቀስ፣ የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆነዉ ወገን ደግሞ መፀዳጃ ቤቶችን በንፅህና እንዲይዝና ከተላላፊ በሽታዎች ራሱን እንዲከላከል ለማሳሰብ ነዉ።

ድረገጹ እንደሚለዉ በዓለማችን የተቅማጥ በሽታ በየዓመቱ በታዳጊዉ አገራት የሚገድላቸዉ ህፃናት ቁጥር ኤች አይቪ ቫይረስ ከሚገድላቸዉ ወገኖች በእጥፍ ይልቃሉ፣ በየዕለቱም አምስት መቶ ሺዎች ይሞታሉ፥ ከዚህም ሌላ በወባ ምክንያት ታመዉ ከትምህርትም ሆነ ከስራ ከሚቀሩት ሰዎች ባልተናነሰም በሺዎች የሚቆጠሩት በንፅህና ጉድለት በሚከሰተዉ የተቀማጥ ህመም እየተሰቃዩ ከቤታቸዉ ይዉላሉ፥ ያም የአገርን ምጣኔ ሃብት ከሚያዳክሙ ችግሮች አንዱ አድርጎታል።

አክሎም የንፅህና ጉድለት በዓለማችን ለሚፈጠሩ ተህዋስያን ወለድ ተያያዥ የጤና እክል ዓይነተኛ ምክንያት ነዉ። ንፅህናቸዉ ባለተጠበቀ መፀዳጃ ቤቶችም ሆነ በየጎዳናዉ መፀዳዳት በሽታን ለሚወልዱ ባክቴሪያና ቫይረሶች ያጋልጣል። ከሰዉነት የሚወጣ ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድ ማለት በተቅማጥ ህይወታቸዉ የሚያልፈዉን ህፃናትና አዋቂዎች ቁጥር 40 በመቶ መቀነስ እንደሆነ ያስረዳል። መጸዳጃዎች በአግባቡ በሚገኙባቸዉ ስፍራዎች ደግሞ ፅዳታቸዉ በየእለቱ መጠበቁን መከታተል ብልህነት ነዉ። በሽታ አምጪ ጀርሞች በአይን የሚታዩ ስላልሆኑ የቱጋ ናቸዉ የሚለዉን መገመት ያዳግታል፣ በጥቅሉ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ መጸዳጃ ቤቶችን ማጽዳት፣ ፍሳስ ዉሃንም በአግባቡ ለጽዳቱ ማዋል፣ ከምንም በላይ የህዝብ መገልገያ በሆኑ መጸዳጃ ቤቶች ተገቢዉ የጀርም ማስወገጃ ጽዳት መካሄዱን መከታተል የሚመለከተዉ ምስሪያ ቤት ብቻ ሳይሆን ጤናማ ለመሆንና በበሽታ ላለመያዝ የያንዳንዱ ተጠቃሚ ኃላፊነት መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል።

ከዜናዉ ባሻገር በአዲስ አበባ የተካሄደዉን በአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃና የአካባቢ ማኅበረሰብን መብት ለማስከበር የሚጥሩ ክፍለ ዓለማዊ ድርጅቶች አፍሪቃ ዓቀፍ የግንኙነት መረብ ጉባኤን የሚመለከተዉን ጥንቅር ያዳምጡ።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ