የመጥፋት አደጋ የተደቀነባቸው የጫካ ቡና ዝርያዎች | ኢትዮጵያ | DW | 13.02.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የመጥፋት አደጋ የተደቀነባቸው የጫካ ቡና ዝርያዎች

ባለፈው ጥር ወር አጋማሽ በሳይንስ መጽሔቶች (ጆርናሎች) ላይ የታተሙ ሁለት ጥናቶች 60 በመቶ የሚሆኑት የጫካ ቡና ዝርያዎች የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠባቸው ይፋ አድርገዋል። ጥናቶቹ ትኩረት ካደረጉባቸው ሀገራት መካከል አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ ከ70 ዓመት በኋላ የቡና ዝርያዎቹ ተፈጥሯዊ መጠን በ50 በመቶ እንደሚቀንስ ተተንብዩዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:11

የኢትዮጵያ የጫካ ቡና ዝርያዎች የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል

ኪው በሚል መጠሪያ የሚታወቀው የእንግሊዙ ዕውቅ የዕጽዋት ምርምር ተቋም ባለፈው ጥር ወር ለንባብ ያበቃቸው ሁለት የምርምር ውጤቶች ለቡና አፍቃሪዎች መልካም ዜናን ይዘው አልመጡም። በእውቅ የምርምር መጽሔቶች (ጆርናሎች) ላይ የታተሙት እነዚህ ጥናቶች ኢኮኖሚያቸው በቡና ላይ ለተመሰረተ ለእንደ ኢትዮጵያ አይነት ሀገራትም የማንቂያ ደውል ሆነዋል።

“ሳይንስ አድቫንስ” በተሰኘው ጆርናል የታተመው የመጀመሪያው ጥናት በመላው ዓለም ካሉ የጫካ ቡና ዝርያዎች ውስጥ መቶ ሃያ አራቱ የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠባቸው ይፋ አድርጓል። ከእነዚህ ውስጥ ሰባ አምስቱ የመጥፋት ስጋት ያለባቸው ሲሆን አስራ ሶስቱ ለመጥፋት የተቃረቡ ተብለዋል። አርባ ዝርያዎች በአደጋ ውስጥ ያሉ ተብለው ሲመዘገቡ ሃያ ሁለቱ ደግሞ ለአደጋ መጋለጣቸው ተገልጿል።

Kaffee Bauer in Äthiopien

 የአለም አቀፍ የቡና ምርት አረቢካ እና ሮቡስታ የተሰኙት ሁለት አይነት የቡና ዝርያዎች ላይ የተመረኮዘ ነው። በኢትዮጵያም የሚመረተው አረቢካ ቡና 60 በመቶውን የአለም አቀፍ የቡና ግብይት ይሸፍናል። በአረቢካ ስር ያሉ የጫካ ቡና ዝርያዎች የመጥፋት ስጋት ከተደቀነባቸው ውስጥ በዋነኛነት እንደሚጠቀሱ “ግሎባል ቼንጅ” በተባለው የምርምር መጽሔት ለንባብ ያበቃው ሌላኛው ጥናት አመልክቷል። ትኩረቱን በኢትዮጵያ ላይ ያደረገው ይህ ጥናት በኪው ተቋም አጥኚዎች እና በኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች የተደረገ ነው። 

የአካባቢ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የቡና ደን መድረክ በሚባል ሀገር በቀል ድርጅት ውስጥ በከፍተኛ ተመራማሪነት እየሰሩ ያሉት ዶ/ር ታደሰ ወልደማርያም ጥናቱን ካካሄዱት ባለሙያዎች አንዱ ናቸው። ላለፉት 20 ዓመታት በቡና እና ደን ላይ ያተኮሩ ጥናቶች ሲያካሄዱ የቆዩት ዶ/ር ታደሰ የአሁኑ ጥናት ከቀድሞዎቹ ይለያል ይላሉ።

ለ50 እና 60 ዓመታት የተሰበሰቡ የሜትሮሎጂ መረጃዎችን ያጠኑት ተመራማሪዎቹ በኢትዮጵያ የአየር ጸባይ ለውጥ ምክንያት የሙቀት መጠን መጨመሩን ደርሰውበታል። እንደ ዶ/ር ታደሰ አባባል በኢትዮጵያ በየዓመቱ በአማካይ ወደ 0.28 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሙቀት ይጨምራል። የአየር ጸባይ ለውጡ በዚሁ ከቀጠለ ወደፊት በአንዳንድ አካባቢዎች እስከ አምስት ዲግሪ ሲንቴግሬድ ያህል የሙቀት መጠን መጨመር ሊከሰት እንደሚችልም ይተነብያሉ። እንዲህ አይነት የአየር ጸባይ ለውጥ ጥናታቸው ትኩረት ባደረገበት የጫካ ቡና ላይም ብዙ ተጽዕኖ ማሳደሩን ያስረዳሉ።

ልዩ ጣዕም ያላቸው የቡና አይነቶች ወፍ ዘራሽ ሆነው በደን ውስጥ በብዛት እንደሚገኙ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ። የመጥፋት አደጋ አለባቸው የሚባሉት እኒህ አይነት የጫካ ቡናዎች በምዕራብ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በብዛት እንደሚገኙ ይገልጻሉ። እነ ዶ/ር ታደሰ ያካሄዱት ጥናት በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ያሉትን የጫካ ቡናዎች የዳሰሰ ነው።

በኢትዮጵያ ያለው የጫካ ቡና የተፈጥሮ መጠን በአየር ጸባይ ለውጥ፣ በተለያዩ በሽታዎች እና በደን ጭፍጨፋ ምክንያት ከ70 ዓመት በኋላ በ50 በመቶ እንደሚቀንስ ጥናቱ ይተነብያል። የቡናው የተፈጥሮ መጠን ሲቀንስ በዚያው የሚጠፉ የቡና ዝርያዎች እንደሚኖሩም ጥናቱ ይጠቁማል።

በኢትዮጵያ የጠፋ የቡና ዝርያ መኖሩን እስካሁን በጥናታቸው እንዳልደረሱበት የሚናገሩት ዶ/ር ታደሰ በጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳን ግን ይህ መከሰቱን ይገልጻሉ። በኢትዮጵያም በተመሳሳይ ከፍታ ላይ ያሉ ቦታዎችም ዝርያዎች ጠፍተው ሊሆን ይችላል ይላሉ። በኢትዮጵያ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸውን የጫካ ቡና ዝርያዎች ለመታደግ ከአሁኑ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው ተመራማሪው ያሳስባሉ።

ሙሉ ዝግጅቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።  

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ 

Audios and videos on the topic