የመጠጥ ዉሃ መመረዝ በደቡብ ሱዳን | አፍሪቃ | DW | 29.05.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የመጠጥ ዉሃ መመረዝ በደቡብ ሱዳን

በደቡብ ሱዳን አንዳንድ  ቦታወች  ከፍተኛ የጤና ዕክል ሊያስከትል የሚችል የዉሃ ብክለት ማጋጠሙን አንድ የጀርመን መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ገለጸ። የተስፋ ምልክት ወይም በጀርመንኛ «ሆፍኑንግስ ሳይሽነን»በሚል መጠሪያ የሚታወቀዉ ይሄዉ ድርጅት ለችግሩ «ፔትሮናስ» የተባለዉ የማሌዥያ የነዳጅ ዘይት ኩባንያ ተጠያቂ ነዉ ሲል ገልጿል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:15

«ፔትሮናስ » ለችግሩ ተጠያቂ ነዉ ተብሏል


የድርጅቱ ባልደረባ ክላዉስ ሽቲግሊትስ የአካባቢዉን የመጠጥ ዉሃ ብክለት ችግር  የተገነዘቡት በአጋጣሚ ነበር።« በጎርጎሮሳዊዉ 2007 አ/ም አንድ የፕሮጀክት አጋራችን  ዉሃዉ መጥፎ ጣዕም እንዳለዉ አጫወተን»ይላሉ ክላዉስ ፤ከዚያ በሁላ የረድኤት ድርጅቱ «ሆፍኑንግስ ሳይሽነን» ጉዳዩን ዝም ብሎ አልተወዉም ይልቁንም  ነገሬ ብሎ መከታተል ጀመረ እንጅ ።
በደቡብ ሱዳን  ፔትሮናስ የተባለዉ የማሌዥያ ኩባንያ ነዳጅ የማዉጣት ስራ በሚያከናዉንበት  አካባቢ የተወሰደዉ የመጀመሪያዉ የዉሃ ናሙና በመጠኑም ቢሆን የጣዕም ችግር  መኖሩን ያመላከተ ነበር ተብሏል።በሁላ ላይ ከአንዳንዶቹ የዉሃ ጉድጓዶች የተወሰደዉ የምርመራ  ዉጤት ደግሞ በዉሃዉ ዉስጥ ከተለመደዉ በአራት እጥፍ የሚልቅ የጨዉ መጠን ተገኝቷል። ድርጅቱ ምርመራዉን ቀጥሎ ከአራት የተለያዩ ቦታወችና ከ96 ሰወች በተወሰዱ የፀጉር ናሙናወች መሰረት  በበርሊን ከተማ ሌሎች የምርመራ ዉጤቶችን ይፋ አድርጓል።
 ለነዳጅ ማዉጫዉ ቅርብ በሆኑ  የዉሃ ጉድጓዶች በተደረገዉ  ምርመራም ዉሃዉ  የአልካላይን ብረት ዝርያ የሆኑ «ባሪየምና ሊድ» በሚባሉ  መርዛማ ንጥረነገሮች የተሞላ ሆኖ ተገኝቷል። በ220 ኬሜ ላይ በምትገኘዉ ሩምቤክ  የሊዱ መጠን አነስተኛ ቢሆንም በ23 ኪሜ  ርቀት ላይ በምትገኘዉ ኮህ ግን የመርዛማ ንጥረነገሩ ይዞታ በአራት እጥፍ ያደገ መሆኑ ይፋ ሆኗል።የበርሊኑ ቻሪቲ ሆስፒታል የህክምና ህግ ባለሙያና የመርዛማ ንጥረነገሮች ተመራማሪ ፍሪትስ ፕራንግስት «ህዝብን የሚጎዳ» ሲሉ ይገልጹታል።በረዥም ጊዜ የሚያመጣዉ የጤና ጠንቅም ከፍተኛ መሆኑን ተመራማሪዉ ያስረዳሉ።
  «የመጀመሪያዉ የደም ማነስ ነዉ።ሁለተኛዉ የነርቭ ህዋሳት እንዳይታዘዝና ስራቸዉን በትክክል እንዳያከናዉንኑ ያደርጋል።ይህ ችግር  የማሰብ  ችሎታ መቀነስ ፣  ሽባነትንና የስነልቡና ቀዉስ የሚያመጡ ምልክቶችን ሊያስከትል ይችላል።ሶስተኛዉ ደግሞ የኬሚካሎች  መብዛት  ለከባድ የኩላሊት በሽታ  ሊዳርግም  ይችላል። » 

በነዳጅ ማዉጫዉ አካባቢ የሚኖሩ ሰወች «ሊድና ባርየም» በምን ያህል መጠን ወደ ሰዉነታቸዉ ገባ የሚለዉን  ለማረጋገጥ  ከጸጉር ምርመራ  በተጨማሪ የደም ምርመራ አስፈላጊ ነዉ የሚሉት ፕራግስት  የችግሩ መሰረት ግን ከነዳጅ ፍለጋና ማዉጣት ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ እርግጠኛ ናቸዉ ።
«ከዉሃ ፍጆታ ጋር የተያያዙ በሽታወችን በተመለከተ ከአካባቢዉ ሰዎች ከቀረቡ መረጃወች ሰምተናል።እንደ እኛ እይታ የችግሩ ሁሉ መንስኤ የነዳጅ ዘይት ፋብሪካዉ  የኬሚካሎችን ዝቃጭና ቆሻሻ  በተገቢዉ ሁኔታ አለማስወገዱ ነዉ።»
በነዳጅ ማዉጣት ሂደት  በዋናነት ያገለግላሉ የተባሉት የባሪየምና የሊድ ንጥረነገሮች ወደ መሬት ሰርገዉ በመግባት የአካባቢዉን  የመጠጥ ዉሃ ለብክለት መዳረጋቸዉን የረድኤት ድርጅቱ አመልክቷል።
በደቡብ ሱዳን ታር ጃት በተባለ ቦታ በነዳጅ ዘይት ፍለጋ ላይ የተሰማራዉ የማሌዥያ ኩባንያ ፤ ፔትሮናስ  ለዚህ ችግር ተጠያቂ ነዉ ቢባልም ዶቼ ቬለ ለኩባንያዉ ያቀረበዉ ጥያቄ ግን ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል።
እንደ «ሆፍኑንግስ ሳይሽነን »በደቡብ ሱዳን መንግስትና በነዳጅ ኩባንያዉ መካከል ለአመታት የዘለቀ ድርድር ቢካሄድም ችግሩን በመፍታት ረገድ ግን ምንም ጠብ ያለ ነገር የለም።የድርጅቱ ባልደረባ ክላዉስ ሽቲግሊትስ  የነዳጅ ኩባንያዉ ችግሩን በመፍታት ረገድ ብዙ መስራት ይጠበቅበታል ይላሉ።
« በመጀመሪያ ደረጃ እኛ ከፔትሮናስ የምንጠብቀዉ ለሰወች የንጹህ መጠጥ ዉሃ አቅርቦት ላይ ይሰራል ብለን  ነዉ።ፔትሮናስ  ለዚህ ሃላፊነት ይወስዳል ብለን እንጠብቃለን። እናም  ለሰወች የንጹህ መጠጥ ዉሃ የማቅረብና የህክምና እርዳታ ላይ አስተዋጽኦ የማድረግ  ብዙ ስራ አለ። »
«ፎርሙላ አንድ» በሚባለዉ የመኪና እሽቅድምድም  የሚታወቀዉ የዳይምለር ክለብ በዚሁ የነዳጅ ኩባንያ እስከ 40 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ የሚደረግለት በመሆኑ አብሮ መስራቱን እንዲያቆም «በሆፍኑንግ ሳይሽነን» በኩል ጥሪ ቀርቦለት ነበር።  ጉዳዩ በእጅጉ ያሳሰበዉ  የስፓርት ክለቡ አጠቃላይ ሁኔታዉን ለማሻሻል ጥረት አደርጋለሁ ቢልም በሀገሪቱ በሚካሄደዉ የርስበርስ ጦርነት ሳቢያ ጉዳዩ ዳር ሳይደርስ  ችግሩን  ለሀገሬዉ ሰዉ ትቶ የነዳጅ ኩባንያዉ ደቡብ ሱዳንን ለቆ መዉጣቱ ተሰምቷል።  የሽቲግሊትስና የድርጅታቸዉ «ሆፍኑንግ ሳይሽነን» አቋም ግን ቁርጥ ያለ ነዉ።ምንም ይሁን ምን ፤ ፔትሮናስ በአካባቢዉ ለደረሰዉ ጉዳት ሀላፊነቱን ሊወስድ ይገባል። 

ፀሐይ ጫኔ/ዳንኤል ፒልስ

ሂሩት መለሰ

 

Audios and videos on the topic