1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአዲስ አበባ ከተማ የመጓጓዣ ታሪፍ ጭማሪ እና የነዋሪው አቤቱታ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 6 2017

ለፈው ሳምንት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ መደረጉን ተከትሎ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን አዲስ የመጓጓዣ ታፊፍ ጭማሪ ታውጇል፡፡ ወትሮም የመጓጓዣ እጥረትና የተጠቃሚዎች መብዛት በሚያጨናንቃት አዲስ አበባ በተለይም በአጭር ርቀት የመጓጓዣ ታሪፍ ላይ እስከ 100 ፐርሰንት የሚደርስ ጭማሪ ነው የተደረገው፡፡

https://p.dw.com/p/4lsTp
Äthiopien Addis Ababa city train
ምስል Joerg Boethling/IMAGO

በመዲናዋ የመጓጓዣ ታሪፍ ጭማሪ በነዋሪው ላይ ያመጣው ተጽዕኖ

የትራንስፖርት ጭማሪ ጫናው

ባለፈው ሳምንት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ መደረጉን ተከትሎ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን አዲስ  የመጓጓዣ ታፊፍ ጭማሪ ታውጇል፡፡

ወትሮም የመጓጓዣ እጥረትና የተጠቃሚዎች መብዛት በሚያጨናንቃት አዲስ አበባ በተለይም በአጭር ርቀት የመጓጓዣ ታሪፍ ላይ እስከ 100 ፐርሰንት የሚደርስ  ጭማሪ ነው የተደረገው፡፡

የከተማ አስተዳደሩ 4 ብር ከ50 ሳንትም የነበረውን የአጭር ርቀት የሚኒ ባስ 2 ኪ.ሜ. ታሪፍ ወደ 10 ብር ከፍ ሲያደርግ በረጅም ርቀትም ላይ ጭማሪዎች ተደርጓል፡፡

በመዲናዋ በተለይም በአነስተኛ ደመወዝ የሚተዳደሩ ሰራተኞች  ጭማሪውን ፈታኝ ሲሉ ይገልጹታል፡፡

 

የትራንስፖርት ጭማሪው በተጠቃሚዎች ላይ ያጠላው ስጋት

“የትራንስፖርት ክፍያ ከብዶኝ መንገዱን በእግር እያቆራረጥኩ እያረፍኩ ነው እየሄድኩ ያለሁት”፤ በአዲስ አበባ ጎዳና ከመንገድ ዳር ማረፊያ አረፍ ብለው ያገኘናቸው እድሜያቸው ጠና ያለ አዛውንት የሰጡን አስተያየት ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከዛሬ ጀምሮ ገቢራዊ የሆነው አዲሱ የትራንስፖርት ታሪፍ ከትራንስፖርቱም ባሻገር ጥላውን በሌሎች የኑሮ ሁኔታዎች ላይ የሚያሳርፍ በማለት ስጋታቸውንም ገልጸዋል፡፡ “ሰው ስንቱን ይችላል፤ ከትራንስፖርቱም ባሻገር ቤት ክራዩ ምግቡ ሁሉም ውትረት ነው” ሲሉም የከበዳቸውን የኑሮ ሁኔታ ለማብራራት ሞክረዋል፡፡

ምክሩ የተባሉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰራተኛ መሆናቸውን ገልጸው በሰጡን አስተያየትም ለመካከለኛ ገቢ ሰራተኞችም አልቀመስ ብሏል ያሉት ኑሮ አሁን ደግሞ በተደራረቡ እንደ ትራንስፖርት ባለው የዋጋ ጭማሪ መታጀቡ ይበልጥ ፈተናውን ያከብደዋል ነው ያሉት፡፡ “የከበደው የኑሮ ሁኔታ ላይ የትራንስፖርቱ ስጨመር ኑሮን ለመቋቋም ሳይከብድ አይቀርም” ነው ያሉት፡፡

የነዳጅ ምርቶች ዋጋ መናር

አስቴር የተባሉ የመዲናዋ ነዋሪም አስተያየታቸውን አከሉ፤ “አሁን አጭሯ ታሪፍ አስር ብር ገብታለች፡፡ ምንም ጥያቄ የለውም ህዝቡ ላይ ጫና ያሳድራል፡፡ እንደ ራይድ፣ ፈረስ የሚባሉ የሜትር ታክሲ የትራንስፖርት አማራጮች ላይም የተደረገው የዋጋ ችማሪ የትየለለ ነው፡፡ በተለያዩ የኑሮ ግብዓቶች ፈተና ላይ ይህ ስጨመር ህይወትን ለመጋፈጥ አዳጋች ሊሆን ይችላልም” ብለዋል፡፡

የታክሲ ተራ በአዲስ አበባ ከተማ
አስቴር የተባሉ የመዲናዋ ነዋሪም አስተያየታቸውን ሲሰጡ፤ “አሁን አጭሯ ታሪፍ አስር ብር ገብታለች፡፡ ምንም ጥያቄ የለውም ህዝቡ ላይ ጫና ያሳድራል፡፡ ብለዋልምስል Seyoum Getu/DW

የመንግስት ሰራተኛው ብርቱ ፈተና

በመንግስት ስራ ተቀጥረው በሚያገኙዋት አነስተኛ ገቢ ቤተሰቦቻቸውን እንደሚያስተዳድሩ የገለጹልን ሌላው አስተያየት ሰጪ የዛሬው የትራንስፖርት ታሪፍ ከፍተኛ ያሉት ጭማሪ አስደንግጦአቸዋል፡፡ እናም ከፍሎ ከመሄድ ይልቅ እያረፉ መጓዝን መርጠዋል፡፡ “በእግሬ እየተጓዝኩ ደክሞኝ ነው ትንሽ ልረፍ ብዬ እዚህች ጋ የተቀመጥኩ፡፡ የትራንስፖርት ጭማሪውን ዛሬ ከተሳፈርኩ በኋላ ነው የሰማሁት፤ ማታም በሚዲያ ተላልፏል አሉኝ፡፡ አጨማመሩ ካለው የኑሮ ሁኔታ አኳያ በጣም ከባድ ነው፡፡ አጫጭር መንገዶች አስር ብር ጨምረዋልና የእኛ ገቢ ባልጨመረበት ይህ የሚያስደስት ነገር የለውም” ብለዋል፡፡

የደሞዝ ጭማሪው «ሳይመጣ የሄደ ተስፋ» ወይስ ደጓሚ ?

መንግስት ለመንግስት ሰራተኞች ከባለፈው ሃምሌ ወር ጀምሮ በተለይም ዝቅተኛ ደመወዝ ላላቸው ሰራተኞች እስከ ሶስት እጥፍ የሚደርስ የደመወዝ ጭማሪ እንደሚያደርግ ቃል ገብቶ ነበር፡፡ ሰራተኞቹ ግን ይህ ጭማሪ እስካሁን አለመለቀቁን በማንሳት በደመወዝ ጭማሪው ሰበብ ነጋደው የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎችን ዋጋ እንዳናረባቸው ነው የሚገልጹት፡፡ “ሃምሌ ላይ የደመወዝ ጭማሪው መሰማቱን ተከትሎ በዚያው ላይ ነው የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች ችማሪ የናረው፡፡ ግን ይሄው ከመስከረም ጀምሮ ገቢራዊ ይሆናል ብባልም እስካሁን ጭማሪው እጃችን ላይ አልገባም፡፡ ጭማውንም ብታየው አዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤ ታች ላለውም ጭምር ሶስት እጥፍ አድጓልም ብባልም አሁንም የሚኖር አይደለም፤ እናም ከሚቆራረጥ ነገር ከፍተኛ መጠን ጋር ስዳመር ፈተናው ብርቱ ነው” ሲሉም አስተያየታቸውን አክለዋል።

የደሞዝ ማስተካከያና የመሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋ መጨመር

የነዳጅ ጭማሪ ተጽእኖ

ባለፈው ሳምንት አጋማሽ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በነዳጅ ዋጋ ላይ ከ20-25 በመቶ ጭማሪ ማድረጉን ተከትሎ በትራንስፖርት ታሪፍ ላይ አዲስ ማሻሻያ እንደሚያደርግ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ የምጣነ ሃብት ባለሙያው አብዱልመናን መሃመድ ይህ በቀጥታ የኑሮ ውድነቱ ሁኔታው ላይ የሚኖረውን አሉታዊ ተጽእኖ ስያስረዱ፤ “ነዳጅ ላይ የሚደረግ አነስተኛ ጭማሪ እንኳ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ስለሚያስከትል ብያንስ መንግስት የሚያደርጋቸውን ጭማሪዎች ለጊዜው ገታ ብያደርጋቸው” በማለት ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

የመንግስት ሰራተኞችን ጨምሮ ነዋሪዎችም በብዙ መልኩ የሚጨምረውን የዋጋ ንረት መቋቋም ከእለት እለት እንደ ከበደ ግን ሁሌም ይገልጻሉ፡፡  

ሥዩም ጌቱ

ታምራት ዲንሳ

ሸዋዬ ለገሰ