የመጋቢት 28 ቀን፤ 2012 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 06.04.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የመጋቢት 28 ቀን፤ 2012 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

የአቮሪኮስቱ ድንቅ የእግር ኳስ ተጨዋች ዲዲየር ድሮግባ፦ «አፍሪቃ ቤተ-ሙከራ አይደለችም» ሲል ሰሞኑን ቊጣውን ገልጧል። የቊጣው ሰበብ ደግሞ ኹለት ፈረንሳውያን ሐኪሞች በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው የተናገሩት ዘረኛ ንግግር ነበር። ፈረንሳውያኑ የኮሮና ተሐዋሲ ክትባት አፍሪቃ ውስጥ መሞከር አለበት ማለታቸው ቊጣ ቀስቅሶ ቆይቷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:46

ሳምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በዓለም ዙሪያ በርካቶችን ገድሎ የሰው ልጆች ላይ ብርቱ የጤና ስጋት ደቅኗል። ስፖርታዊ ውድድሮችንም ላልተወሰኑ ጊዜያት እንዲሸጋሸጉ አስገድዷል። የኮሮና ተሐዋሲ ሥርጭቱን እንደቀጠለ ነው። ምናልባትም የተሐዋሲውን ስርጭት ለመግታት በየሃገራቱ የተጣሉ እገዳዎች እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች እስከ መስከረም ወር ድረስ የሚቀጥሉ ከኾነ የአውሮጳ ሻምፒዮንስ እና የአውሮጳ ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች ሊሰረዙ እንደሚችሉ  የአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት (UEFA) ሥጋቱን ገልጧል። የአቮሪኮስቱ ድንቅ የእግር ኳስ ተጨዋች ዲዲየር ድሮግባ፦ «አፍሪቃ ቤተ-ሙከራ አይደለችም» ሲል ሰሞኑን ቊጣውን ገልጧል። የቊጣው ሰበብ ደግሞ ኹለት ፈረንሳውያን ሐኪሞች በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው የተናገሩት ዘረኛ ንግግር ነበር። 

የኹለቱ ፈረንሳውያን ሐኪሞች ንግግር ቊጣ ያጫረው ዲዲየር ድሮግባ ላይ ብቻ አይደለም። የባየር ሙይንሽኑ እና የኦስትሪያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ተሰላፊው ዳቪድ አላባም ኹለቱ ፈረንሳዊ ሐኪሞችን አጥብቆ ተችቷል። «ለመኾኑ» አለ ዳቪድ አላባ፤ «ለመኾኑ እነዚህ ኹለቱ ሰዎች ሐኪሞች ናቸው ወይንስ ቂላቂሎች?» ቀጠለ። «እንዲህ ያለውን ዘረኝነት መቼም ቢኾን ላስበው የምችለው አይደለም» ሲልም የባየር ሙይንሽኑ ተሰላፊ ይፋዊ የትዊተር ገጹ ላይ ጽፏል። 

የኹለቱ ፈረንሳውያን ሐኪሞች ዘረኛ ንግግራቸው ባለፈው ሳምንት ረቡዕ የተሰማው የኮሮና ተሐዋሲ ሥርጭትን ለመግታት የሳንባ ነቀርሳ ክትባትን በአማራጭ አውሮጳ እና አውስትራሊያ ውስጥ ስለመሞከር በሚያወሳው ውይይት ወቅት ነበር ። የክትባት ሙከራው መጀመሪያ የአፍሪቃ ነዋሪዎች ላይ አፍሪቃ ውስጥ መደረግ እንዳለበት በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው ያሰሙት ንግግር  በዓለም ዙሪያ ብርቱ  ቊጣን አጭሮባቸዋል። ሐኪሞቹ ዘረኛ ያስባላቸውን አስተያየታቸውን የሰነዘሩት ኤል ሲ ኢ በተሰኘው የፈረንሳይ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ቀርበው ነው።

የሐኪሞቹን ንግግር በመቃወም የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን እና የእንግሊዙ ቸልሲ ተሰላፊ አንቶኒዮ ሩዲገር በበኩሉ አስተያየቱን ሰንዝሯል። «አፍሪቃውያን ልክ አንዳች እንስሳት የኾኑ ይመስል፤ ይኼ የዘረኝነት ጥጉ ነው» ሲልም ትዊተር ገጹ ላይ ቊጣውን አንጸባርቋል።

አፍሪቃዊ ዝርያ ያላቸው አንቶኒዮ ሩዲገር እና ዳቪድ አላባ በአውሮጳ ቡድኖች ውስጥ ተሰልፈው በተጫወቱባቸው ዘመናት በተደጋጋሚ የዘረኝነት ስድብ የደረሰባቸው ሲኾን ሳይታክቱም ተቃውሟቸውን በማሰማትም ይታወቃሉ። 

የዘረኝነት ጉዳይ በእርግጥም በምዕራቡ ዓለም የስፖርት ውድድር ዘርፍ በተለይ በእግር ኳሱ በተደጋጋሚ በስፋት የሚታይ ተወጋዥ ድርጊት ነው። አፍሪቃውያኑ ዲዲየር ድሮግባ እና ሳሙኤል ኢቶም ተደጋጋሚ የዘረኝነት ስድብ የደረሰባቸው ተጨዋቾች ናቸው። 

እናም ድሮግባ የሐኪሞቹን ንግግርን ሲተች፦«አፍሪቃ ቤተ-ሙከራ አይደለችም» ብሏል። «ይኼ ፈጽሞ ሊታሰብ የማይችል ነው» ሲል ድሮግባ ኹሉም ሰው በጥንቃቄ ጉዳዩን ሊያየው እንደሚገባ አስገንዝቧል። «ግልጽ በኾነ ቋንቋም እነዚያን ንቀቶች፤ የሐሰት እና ከምንም በላይ ደግሞ ዘረኛ ንግግሮች ማውገዝ እፈልጋለሁ። አኹን የሚታየውን የኮቪድ 19 ሥርጭት በመግታት አፍሪቃን አድኑ፤ ርዱን» በማለት ይነበባል የዲዲየር ድሮግባ የትዊተር ጽሑፍ። አፍሪቃውያን መሪዎች «የተደቀነባቸው» ካለው «ብርቱ ሸፍጥም» የሕዝብ ቊጥራቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል ሲል በማስጠንቀቅ «ፈጣሪ ይጠብቀን» በማለት ጽፏል። 

በዓለም ዙሪያ 1.3 ሚሊዮን ግድም ሰዎች እስከዛሬ ድረስ በኮሮና ተሐዋሲ መጠቃታቸውን ከ70 ሺህ በላይ መሞታቸውን የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ይጠቊማል። ፈረንሳይ በዓለም ዙሪያ ዜጎቻቸው በኮሮና ተሐዋሲ በብዛት ከተጠቊባቸው ቀዳሚ ሃገራት መካከል ቻይናን ከኋላዋ አስከትላ አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ፈረንሳይ ውስጥ እስከ ዛሬ ድረስ 94 ሺህ ግድም ሰዎች በኮሮና ተሐዋሲ ተጠቅተው፤ ከ8 ሺህ በላይ ሞተዋል። አፍሪቃ ውስጥ ዘገባዎች እንደሚጠቊሙት በ51 ሃገራት ውስጥ 9 ሺህ ግድም ሰዎች በተሐዋሲው ተጠቅተው የሞቱት ሰዎች አጠቃላይ ቊጥር ይኽን ዘገባ እከምናጠናቅርበት ጊዜ ድረስ ከአምስት መቶ በታች ነበር።  ፈረንሳይ ብቻዋን በመላው አፍሪቃ በኮሮና ተሐዋሲ ከተጠቊት ከ10 በመቶ በላይ ሰዎች እያላት ኹለቱ ሐኪሞቿ አፍሪቃ ውስጥ የኮሮና ተሐዋሲ ሙከራ ይደረግ ማለታቸው በእርግጥም ቊጣ መቀስቀሱ የሚጠበቅ ነበር። 

የኮሮና ተሐዋሲ በብርቱ የመታት ጣሊያን በሀገሯ ይካሄዱ የነበሩ የእግር ኳስ ግጥሚያዎችን እስከሚቀጥለው የመኸር ወራት ድረስ ለማራዘም እያሰበችበት መኾኑ ተሰምቷል። የጣሊያን የእግር ኳስ ፌዴሬሽን  ፕሬዚደንት ጋብሪዬሌ ግራቪና ራይ ከተሰኘው የስፖርት ጣቢያ ጋር ትናንት ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ፦ እስከሚቀጥለው የመስከረም አለያም የጥቅምት  ወራት ድረስ ኹኔታዎች እግር ኳስ ዳግም የሚጀምርበትን መንገድ የሚያሳዩ አለመኾናቸውን ጠቊመዋል። 

በጣሊያን የሴሪኣው የእግር ኳስ ዳግም እንዲጀምር የተያዘለት ቀጠሮ አንድ ወር ከ11 ቀን ይቀሩታል። የጣሊያን መንግሥት ባለፈው ሳምንት ባስተላለፈው መመሪያ መሰረት በሀገሪቱ በኮሮና ተሐዋሲ መዛመት የተነሳ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር እስከ ትንሳኤ ማግስት ድረስ እንዲራዘም ወስኗል። እናም በአንጻሩ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች በጣሊያን በግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ዳግም ሊጀምር ይችላል የሚል ተስፋም ሰንቀዋል። 12 የውድድር ቀናት ቀርተውት የነበረው  የጣሊያኑ ሴሪ ኣ እንዲቋረጥ የተደረገው የካቲት 30 ቀን 2012 ዓ.ም ነበር። የዘንድሮ የሻምፒዮንስ ሊግ እና የአውሮጳ ሊግ ግጥሚያዎች ሊሰረዙ እንደሚችሉ ተጠቆመ። በዚሁ የኮሮና ተሐዋሲ መዛመት በተፈጠረው ቀውስ የተነሳ በዓለም ዙሪያ የተጣሉት ክልከላዎች እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች የሚቀጥሉ ከኾነ ጨዋታዎቹ ዘንድሮ እንደማይካሄዱ የአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት (UEFA) ፕሬዚደንት አሌክሳንደር ሴፌሪን ተናግረዋል። ኾኖም ግን ጨዋታዎቹን ሙሉ ለሙሉ ከመሰረዝ ይልቅ በዝግ ስታዲየሞች ውስጥ አከናውኖ ማጠናቀቅ እንደሚሻል ገልጠዋል። 

የሻምፒዮንስ ሊግ እና የአውሮጳ ሊግ ግጥሚያዎች ላልተወሰነ ጊዜ ነው የተቋረጡት። «ከመስከረም እና ጥቅምት ወራት ውጪ ጨዋታዎችን ለማካሄድ አንችልም» ሲሉም ፕሬዚደንቱ ስጋታቸውን ገልጠዋል። እናም ታዲያ እገዳዎች እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች መራዘማቸው የሚቀጥል ከኾነ ውድድሮቹ ሙሉ ለሙሉ ይተዉ ይኾን ተብለው ለተጠየቊትም፦ «ባለሥልጣናት እንድንጫወት ካልፈቀዱ መጫወት አንችልም» ሲሉ መልሰዋል። ውድድሮቹ በግንቦት ወር ሊጠናቀቊ ነበር ቀጠሮ ተይዞላቸው የነበረው። 

Logo Premier League

የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ተጨዋቾች ከሚያገኙት ገቢ ሠላሳ በመቶውን የኮሮና ተሐዋሲን ለመዋጋት ቢያውሉ ፍላጎቱ እንደነበር ዐስታወቀ። በኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽ ወቅት ፕሬሚየር ሊግ ለታላቋ ብሪታንያ የጤና አገልግሎት ርዳታው እስከምን ድረስ እንደሚኾን ለመምከር ከተጨዋቾች እና የእግር ኳስ ቡድኖች ጋር ተገናኝቷል። ፕሬሚየር ሊጉ ተጨዋቾች ከገቢያቸው 30 በመቶ እንዲለግሱ ቢሻም ከ20 ቡድኖች ጋር ያከናወነው ውይይት ቅዳሜ ዕለት ያለስምምነት መጠናቀቊ ተነግሯል።  የእግር ኳስ ውድድሮች እንግሊዝ ውስጥ ቢያንስ እስከ ግንቦት ወር ማብቂያ ድረስ የተራዘሙ ሲኾን፤ ጨዋታዎች  ዘንድሮ የማይጠናቀቊ ከኾነ ቡድኖች ላላደረጓቸው ጨዋታዎች እስከ 884 ሚሊዮን ዶላር ድረስ ለቴሌቪዥን ኩባንያዎች ሊከፍሉ እንደሚችሉ የጀርመን የዜና አገልግሎት ዘግቧል። 

ፕሬሚየር ሊጉ ለሀገሪቱ የጤና ዘርፍ 20 ሚሊዮን ፓውንድ በቀጥታ እንደሚለግስ ባለፈው ቅዳሜ ይፋ አድርጓል። «መንግሥት ቀርቦ ነርሶችን በገንዘብ ርዳ አልያም የመተንፈሻ አጋዥ መሣሪያዎችን ግዛ ብሎ ቢጠይቀኝ  ያን የማደርገው በኩራት ነው» ያለው ዋይኒ ሩኒ ኹሉም ተጨዋቾች የመለገስ ፍላጎት አላቸው ማለት እንዳልኾነ ተናግሯል። «ድንገት ግን ተነስቶ ተጨዋቾች በሙሉ 30 ከመቶ መክፈል አለባቸው» መባሉ ተገቢ አለመኾኑን ጠቊሟል። አንዳንድ የፕሬሚየር ሊጉ የእግር ኳስ ቡድኖች እና ተጨዋቾች የመደገፍ ፍላጎት እንዳላቸው ኹሉም ይክፈሉ መባሉ ግን እንዳልተስማማቸው ተናግረዋል። የዓለም የከባድ ሚዛን ቡጢኛው ግን በሚቀጥለው ተጋጥሜ ከማገኘው ግማሹን እሰጣለሁ ብሏል።

ቡጢ

የዓለማችን የከባድ ሚዛን ቡጢ ተፋላሚ ኩበራት ፑሌቭ ከብሪታንያዊው የከባድ ሚዛን ቡጢኛ ጋር ሊያደርግ ባሰበው የቡጢ ፍልሚያ ከሚያገኘው 4,7 ሚሊዮን ፓውንድ ግማሹን ለኮሮና ተሐዋሲ ፍልሚያ ለማዋል ቃል መግባቱ ተዘግቧል። 

የከባድ ሚዛን ቡጢ የአውሮጳ ባለድሉ ቡልጋሪያዊ ከከባድ ሚዛን የዓለም ባለድሉ ብሪታኒያዊ አንቶኒ ጆሹዋ  ጋር ለመፋለም ቀጠሮ የተያዘው ለቅዳሜ ሰኔ 13 ቀን፤ 2012 ዓ.ም በብሪታንያ መዲና ለንደን ከተማ የቶትናም ሆትስፐር ስታዲየው ውስጥ ነው።  የ38 ዓመቱ ቡጢኛ፦ «ገንዘቡን ይኽን ሴጣናዊ ተሐዋሲ ለሚፋለሙት» ላላቸው «ሐኪሞች፣ የሕመምተኞች ተንከባካቢዎች እና ሐኪም ቤቶች አስፈላጊ ቊሳቊሶች መግዢያ እንዲውል» ለመለገስ መዘጋጀቱን በጀርመንኛ ለሚታተመው ቢልድ የተሰኘው ጋዜጣ ተናግሯል። 

የ30 ዓመቱ  አንቶኒ ጆሹዋ ባለፈው ታኅሣሥ ወር በዳኞች ውሳኔ አንዲ ሩይዝን ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ አሸንፎ የዓለም ከባድ ሚዛን ቀበቶዎችን (IBF, WBA, WBO እና IBO)ካስመለሰ ወዲህ ተወዳድሮ አያውቅም። አንቶኒ ጆሹዋ እነዚህን ቀበቶዎቹን በዚሁ አሜሪካዊ ሜክሲካዊው ቡጢኛ የተቀማው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ በተደረገው ፍልምያ ነበር።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic