የመጋቢት 20 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 29.03.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የመጋቢት 20 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ዋሊያዎቹ ለአፍሪቃ ዋንጫ የማጣሪያ ግጥሚያቸውን ነገ አይቮሪ ኮስት ዋና ከተማ አቢጃን ውስጥ ያከናውናል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ካሸነፈ አለያም አቻ ከወጣ ወይንም ደግሞ ተሸንፎም ቢሆን ማዳጋስካር በኒጀር ከተሸነፈ ወይንም አቻ የሚወጣ ከሆነ የማለፍ ዕድል አለው። በዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ግጥሚያዎች የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ሁለተኛ ጨዋታውን ትናንት

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:45

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ዋሊያዎቹ ለአፍሪቃ ዋንጫ የመጨረሻ የማጣሪያ ግጥሚያቸውን ነገ አይቮሪ ኮስት ዋና ከተማ አቢጃን ውስጥ ያከናውናል።  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ካሸነፈ አለያም አቻ ከወጣ ወይንም ደግሞ ተሸንፎም ቢሆን ማዳጋስካር በኒጀር ከተሸነፈ ወይንም አቻ የሚወጣ ከሆነ የማለፍ ዕድል አለው። በዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ግጥሚያዎች የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ሁለተኛ ጨዋታውን ትናንት 1 ለ0 ማሸነፍ ችሏል። ከአይስላንድ አንጻር ሩማኒያ ጠንካራ ተፎካካሪ ኾኖ ታይቷል። ፖርቹጋል አቻ በወጣበት ውድድር የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ሮናልዶ ግብ ተሽሮበታል። የሊቨርፑሉ ዲዮጎ ጆታ ሁለት ግቦችን ከመረብ አሳርፏል።  በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ሌዊስ ሐሚልተን ድል ቀንቶታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋሊያዎቹ ነገ ከሰአት የአይቮሪኮስ ቡድንን በዋና ከተማዋ አቢጃን ይገጥማሉ። በወዳጅነት ግጥሚያ ማላዊን በአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ደግሞ ማዳጋስካርን 4 ለ0 ማሸነፍ የቻሉት ዋሊያዎቹ በምድቡ 9 ነጥብ ይዘው የሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ተጋጣሚው አይቮሪ ኮስት ምድቡን የሚመራው በዐሥር ነጥብ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በነገው ግጥሚያ አቻ መውጣት ብቻ ይበቃዋል። 7 ነጥብ ያለው ማዳጋስካር ከምድቡ 3 ነጥብ ይዞ የመጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የኒጀር ቡድን ቢያሸንፍ እንኳን የሚኖረው 10 ነጥብ ነው። ያ ማለት ደግሞ ኢትዮጵያ አቻ ብትወጣ ከሚኖራት 10 ነጥብ ጋር ቢመሳሰልም ከ6 በላይ ግቦችን ማስቆጠር ይኖርበታል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 6 የተጣራ የግብ ክፍያ ሲኖረው ማዳጋስካር ምን የለውም።  በዚህም አለ በዚያ ኒጀር ተሰናባች መሆኑን አስቀድሞ ዐውቋል።  በዚህ ምድብ ኢትዮጵያ እና አይቮሪኮስት ተያይዘው ወደ ለቀፍሪቃ ዋንጫ የማለፍ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።

በሌሎች የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድሮች ደቡብ አፍሪቃን ትናንት ኦምዱርማን ውስጥ 2 ለ0 ማሸነፍ የቻለው የሱዳን ቡድን ለአፍሪቃ ዋንጫ ፉክክር ማለፉን አረጋግጧል። ሱዳን ወደ አፍሪቃ ዋንጫ መመለስ የቻለችው ከ12 ዓመታት ወዲህ ነው። የደቡብ አፍሪቃዎቹ ባፋና ባፋናዎች በአንድ ወቅት ለዓለም ዋንጫ መድረስ የቻሉ በመሆናቸው ከሱዳን ሽንፈት መልስ ቡድኑ እንዲበተን ደጋፊዎች ጥሪ እያስተላለፉ ነው።

ሌላኛዋ በዓለም ዋንጫ ውድድር ጥሩ ስም ያላት ጋና መዲናዪቱ አክራ ውስጥ ሳዎ ቶሜ ኤ ፕሪንሲፕ 3 ለ 1 ድል አድርጋ በ13 ነጥብ የምድቡ ቀዳሚ ሆና ወደ አፍሪቃ ዋንጫ ማለፍ ችላለች። 10 ነጥብ ያላት ሱዳን ከምድቡ ሁለተኛ ኾና ነው ያለፈችው። ተሰናባቿ ደቡብ አፍሪቃ 10 ነጥብ ሲኖራት፤ ሳዎ ቶሜ ኤ ፕሪንሲፕ የተሰናበተችው በ0 ነጥብ ነው።

ማሊ እና ጊኒ ከምድባቸው በ13 እና 11 ነጥብ ማለፍ ችለዋል። ናሚቢያ በ9 እንዲሁም ቻድ በ1 ከምድቡ ተባራሪ ኾነዋል። ሊቢያ እና ታንዛኒያ በ3 እና 7 ነጥብ ከተባረሩበት ምድብ ደግሞ ቱኒዚያ እና ኤኳቶሪያል ጊኒ አላፊ ኾነዋል። ቱኒዝያ 16 ነጥብ ሲኖራት፤ ኤኳቶሪያል ጊኒ በ9 ነጥብ ነው ያለፈችው። ሌሎች እስካሁን ማለፋቸውን ካረጋገጡ ቡድኖች መካከል፦ ናይጀሪያ፣ ሞሮኮ፣ አዘጋጇ ካሜሩን፣ ሴኔጋል፣ ጋቦን፣ ጋምቢያ፣ ግብጽ፣ ኮሞሮስ፣ አልጄሪያ፣ ዚምባብዌ፣ ይገኙበታል።

እጎአ በ2022 ኳታር በምታዘጋጀው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ተሳታፊ ለመሆን ፉክክሩ ቀጥሏል። ጀርመን ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከምታከናውናቸው 10 ግጥሚያዎች ሁለቱን ጨዋታዎችን አድርጋለች። 55 የአውሮጳ ሃገራት የእግር ኳስ ቡድኖች በማጣሪያው ይሳተፋሉ። ከአውሮጳ 13 ሃገራት ለዓለም ዋንጫ ያልፋሉ።

የጀርመን ቡድን ትናንት ከሩሜኒያን ጋር ተጫውቶ 1 ለ0 አሸንፏል። ውድድሩ ሩማንያ ዋና ከተማ  ቡካሬስት ውስጥ ነው የተከናወነው። አሰልጣኝ ዮአሒም ሎይቭ ከጨዋታው ጥቂት ቀደም ብሎ RTL በተባለው የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው ለቀረበላቸው ጥያቄ፦ «በአሁኑ ወቅት የቡድኑ ስሜት ጥሩ ነው» ብለዋል። አሰልጣኙ ብሔራዊ ቡድኑ ላይ በርካታ ለየት ያሉ ነገሮችን በመሞከር ይታወቃሉ። ለአብነት ያህል ዮሱዋ ኪሚሽን በአውሮጳ ዋንጫ ወቅት ተከላካይ ማድረግ ይፈልጋሉ። አማካይ ላይ እጅግ በጣም ድንቅ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ልጅ ነው።

ባለፈው ሳምንት ሐሙስ አይስላንድን 3 ለ0 ባሸነፉበት ግጥሚያ ሁለት ግቦችን ያመቻቸው ዮሱዋ ኪሚሽ ነው። በ3ኛው ደቂቃ ሌዎን ጎሬትስካ፤ በ7ኛው ደግሞ ካይ ሓቫርትስ ከመረብ ያሳረፉትን ኳሶች አመቻችቶ የላከው ዮሲዋ ኪሚሽ ነው። ኢካይ ጉንዶዋን በ56ኛው ደቂቃ ላይ ሦስተኛዋን ከመረብ አሳርፏል። በእርግጥ ዮሱዋ ኪሚሽ ቀደም ሲል ማለትም በ2019/20 የጨዋታ ዘመን የአውሮጳ እግር ኳስ ዋንጫ ምርጥ ተከላካይ ተብሎ ተመርጦ ነበር። ዮአሒም ሎይቭ ተጨዋቾችን ቀደም ሲል ከሚጫወቱበት መስመር እየቀያየሩ ሙከራ ማድረግ ይወዳሉ። አንዳንድ ጊዜ ይኼ ድፍረታቸው ቡድናቸው ውጤት አልባ እንዲሆን ሲያደርገውም ታይቷል።

ኤምሬ ቻን ግራ ተከላካይ ቢሆንም በክንፍ ወደተቃራኒ ግብ ክልል እየተጠጋ ብቃቱን ሲያሳይ ነበር። ኒክላስ ሱሌይ በጉዳት አልተሰለፈም። ፊሊፕስ ማክስ ተቀያሪ ነበር። ካይ ሓቫርትስ በቀኝ በኩል ጥሩ ተንቀሳቅሷል። ኾኖም 9ኛው ደቂቃ ላይ ከበረኛው ጋር ተገናኝቶ ግብ ሊሆን የሚችል ኳስ ግብ ጠባቂው አጨናግፎበታል።

16ኛው ደቂቃ ላይ ሩዲገር የላከለትን ኳስ ሐቫርትስ በቀኝ በኩል በሚገባ ተቆጣጥሮ ለሰርጌይ ግናብሬ አቀብሎታል። ግናብሬም ተረጋግቶ ከመረብ አሳርፎታል። ኪሚሽ 18ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ወደ ግብ ልኮ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ለሩሜንያ አስደንጋጭ ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ግቧ ከተቆጠረችበት ስኬት ውጪ የጀርመን ቡድን አጋጣሚዎችን ቢያገኝም ያን ያህል አስጊ አልነበረም።

አሰልጣኝ ዮአኺም ሎይቭ 77ኛው ደቂቃ ላይ ካይ ሓቫርትስን በ ቲሞ ቬርነርን የመቀየር ሙከራ አድርገዋል። አስፈላጊነቱ ግን ዐልታየም። የሩሜኒያ ቡድን ከአይስላንድ አንጻር ከባድ መሆኑን አሰልጣኙ ተናግረዋል። ዕድላችን አለመጠቀማችን ሊተች ይገባልም ብለዋል። ቢያንስ 2 ለ0 ጨዋታው መጠናቀቅ እንደነበረበት ተናግረዋል። ያ ደግሞ ለተጨዋቾቹ ሞራል ግንባት መልካም ነበር ሲሉ አክለዋል። ብሔራ ቡድኑ የፊታችን ረቡዕ ከሰሜን ሜቄዶኒያ ጋር ይጋጠማል።

የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የዓለም ዋንጫ የምታዘጋጀው ኳታር የሰብአዊ መብቶች ጉዳይዋን እንድስታስተካክል ጠይቋል። ቡድኑ ከኔዘርላንድ ጋር በይፋ ስዊድን የጀመረችውን ዘመቻም ተቀላቅሏል። ውድድሩ ሁለት ዓመት ቢቀረውም በግንባታ የተሰማሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች መሞታቸው እና የኳታር የሰብአዊ መብቶች አያያዝ አጠያያቂ ነው በሚል ውድድሩ ኳታር ውስጥ መካኼድ አለበት ወይ የሚል ጥያቄም አጭረዋል።

የኖርዌዩ አጥቂ ኧርሊንግ ኦላንድ  (Human rights, on and off the pitch) የሚል መልእክት ባለፈው ረቡዕ ካናቴራው ላይ ካሰፈረ በኋላ የጀርመን ቡድንም ተቀራራቢ መልእክት ይዞ ቀርቧል። ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪዎች ስታዲየም ግንባታ ላይ የሚሳተፉ ስደተኞች ሞት እንደሚያሳስባቸው በተደጋጋሚ ገልጠዋል። የባየር ሙይንሽን ደጋፊዎችም ብርቱ ትችት ቢሰነዝሩም የባየርን ዋና ኃላፊ ካርል ኃይንትስ ሩሜኒጋ ግን፦ ከኳታር ጋር መሥራት ትክክለኛ ነገር ብሏል። ኳታር የ2022 የዓለም ዋንጫን እንደምታዘጋጅ በ2010 ከተነገረባት ጊዜ አንስቶ ዘ ጋርዲያን የተባለው የብሪታንያ ጋዜጣ እንደዘገበው፦ ስታዲየም ግንባታ ላይ የተሳተፉ 6,500 ሠራተኞች ሞተዋል።  

በዓለም ዋንጫ ሌሎች ግጥሚያዎች፦ ፖርቹጋል አቻ በወጣበት ውድድር የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ሮናልዶ ግብ ተሽሮበታል። የሊቨርፑሉ ዲዮጎ ጆታ በ11ኛው እና 36ኛው ደቂቃ ላይ ሁለት ግቦችን ከመረብ አሳርፏል።  ክሪስቲያኖ ሮናልዶ 93ኛው ደቂቃ ላይ ቡድኑን አሸናፊ ልታደርግ ትችል የነበረችው ግብ ዳኛው ከመስመር ማለፏን ባለማየታቸው ሳያጸድቁት ቀርተዋል። በዚህም የተበሳጨው ሮናልዶ ክርኑ ላይ ያሰረውን የአምበል መለያ ጨርቅ መሬት ላይ በመወርወር በንዴት ከሜዳ ወጥቷል።

ትናንት ከነበሩ በርካታ ግጥሚያዎች፦ ስዊድን ኮሶቮን 3 ለ0፣ ሰሜን መቄዶኒያ ሌሽተንሽታይንን 5 ለ0 አሸንፈዋል። ጣሊያን ቡልጋሪያን 2 ለ0፣ ሐንጋሪ ሳን ማሪኖን 3 ለ0 ያሸነፉትም ትናንት ነበር። ፈረንሳይ፣ ካዛክስታንን እንዲሁም እንግሊዝ አልባንያን 2 ለ0 ድል አድርገዋል። አርሜኒያ አይስላንድን 2 ለ0 ስታሸንፍ ኦስትሪያ ፋራዎ ደሴቶችን 3 ለ1 አሸንፋለች። ከትናንት ግጥሚያዎች የግብ ጎተራ ኾና የጨረሰችው ማልዶባ ናት። በዴንማርክ 8 ለ0 ተንኮታኩታለች።

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ብሪታንያዊው አሽከርካሪ ሌዎስ ሐሚልተን ባህሬን ውስጥ ውድድሩን በድል ጀምሯል። ምናልባትም በተከታታይ ለሦስተኛ ጊዜ ዋንጫውን ሊያነሳም ይችል ይሆናል። በባህሬኑ ውድድር ሌዊስ ሐሚልተንን ተከትሎ የሬድ ቡል አሽከርካሪው ማክስ ፈርሽታፐን ሁለተኛ  ወጥቷል። የሌዊስ ሐሚልተን የመርሴዲስ ቡድን አባል ቫለሪ ቦታስ የሦተኛ ደረጃውን ይዟል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic