የመጋረጃ ጀርባው ትብብር  | ኤኮኖሚ | DW | 26.07.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

የመጋረጃ ጀርባው ትብብር 

የጀርመናውያን የኩራት ምልክት የሆኑት የመኪና አምራች ኩባንዮች ለበርካታ አመታት ከመጋረጃ ጀርባ እየተገናኙ ስለ በካይ ጋዝ ልቀት፤የመኪና ዋጋ እና ስለ ግብዓት አቅርቦት ያሴሩ ነበር የሚል ውንጀላ ተሰምቷል።ኩባንያዎቹ ውንጀላውን አሉባልታ ይበሉ እንጂ የጀርመን ባለሥልጣናት እና የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ምርመራ መጀመራቸውን አስታውቀዋል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:29

የጀርመን መኪና አምራቾች የመጋረጃ ጀርባው ትብብር

በአንድ ወቅት ለጀርመን የተሽከርካሪ ምኅንድስና የማዕዘን ድንጋይ የነበረው ናፍጣ ከመኪና ባለቤቶች፤ሕግ አውጪዎች እና ከተሞች የከፋ ወቀሳ እየገጠመው ነው። ምን አልባትም የአውሮጳ መኪኖችን ለዘመናት ያሽከረከረው ናፍጣ ኅልውናው ያበቃ ይሆናል። ተሽከርካሪ አምራቾች የበካይ ጋዝ ልቀት ገደብን በቴክኖሎጂ ማጭበርበራቸው ላለፉት ሁለት አመታት ለጀርመናውያን ራስ ምታት የነበረ ቅሌት ነው። 

የበካይ ጋዝ ልቀት ቅሌት ከጀርመን ሰማይ እንዲህ በቀላሉ ገሸሽ የሚል አይመስልም።ባለፈው ሳምንት ዴር ሽፒግል የተባለው የጀርመን መፅሔት የሐገሪቱ መኪና አምራቾች ኩባንዮች እንደ ጎርጎሮሳዊው ከ1990ዎቹ ጀምሮ «በምሥጢር ስለ በካይ ጋዝ ልቀታቸው ሲመክሩ ነበር» የሚል አስደንጋጭ ዘገባ አስነብቧል። ፎልክስቫገን፤አውዲ፤ቢ ኤም ደብሊው፤ ፖርሼ እና ዳይምለር በምስጢር እየተገናኙ ፈታኝ የሆነባቸውን የበካይ ጋዝ ልቀት ገደብ እንዴት ማክበር እንደሚችሉ ይነጋገሩ ነበር ብሏል ሳምንታዊው መፅሔት። ኩባንያዎቹ "ሕገ-ወጥ" በተባለው ምክክራቸው ስለ መኪኖች ዋጋ፤ የግብዓት አቅርቦት እና ቴክኖሎጂ ያወጉ ነበር ተብሏል። መፅሔቱ እንደሚለው ከመጋረጃ ጀርባ በተፈጸሙት ድርድሮች የመኪና አምራቾቹ ደንበኞች እንዲሁም የግብዓት አቅራቢዎች ጉዳት ላይ ወድቀዋል። የጀርመን የአካባቢ ጥበቃ ድርጅት ኃላፊ ዩርገን ሬስሽ ግን ጉዳዩ አዲስ አልሆነባቸውም። 

"የጀርመን የአካባቢ ጥበቃ ድርጅት የተለያዩ ተሽከርካሪ አምራቾች ወደ አየር የሚለቁት የበካይ ጋዝ ማረጋገጫ መመሳሰል በአጋጣሚ የተፈጠረ ሳይሆን ታስቦበት የተደረገ መሆኑን የሚጠቁሙ ጠንካራ ማስረጃ የያዙ በርካታ ሰነዶች በእጁ ይገኛሉ።"

ለግዙፉ መኪና አምራች ፎልክስቫገን የበካይ ጋዝ ልቀት ቅሌት አዲስ አይደለም። ክስ እና ቅጣት የበረከተበት ይሕ ኩባንያ ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ አጥቷል።  

የሜርሴዲስ ቤንዝ አምራቹ ዳይምለር ከቅጣት ለማምለጥ ከመጋረጃ ጀርባ ይደረጉ ስለነበሩት ድርድሮች ለገበያ ውድድር ጥበቃ ሹማምንት አስቀድሞ ማሳወቁ ተሰምቷል። መቀመጫውን ቮልፍስቡርግ ያደረገው ፎልክስቫገን በበኩሉ አስቸኳይ የቦርድ ስብሰባ ጠርቷል።  በመኪኖቹ ላይ የገጠመው የበካይ ጋዝ ልቀት መቆጣጠሪያ ብቁ መሆኑን የገለጠው ቢ ኤም ደብሊው ከሌሎች አምራቾች ጋር ይደረግ የነበረው ውይይት በመላው አውሮጳ ወጥ አሰራር ለመዘርጋት የሚደረግ ነበር ሲል ክሱን አስተባብሏል። የመኪና አምራች ኢንዱስትሪውን በቅርበት የሚያውቁት ፈርዲናንድ ዱደንሆፈር በጋራ መስራት በኩባንያዎች ዘንድ አዲስ ነገር እንዳልሆነ ይናገራሉ። የአሁኑ ግን ለእርሳቸውም ቢሆን አስደንግጧቸዋል።

"በመኪና አምራች ኢንዱስትሪው ዘንድ ሕግ አውጪዎችን ለማባበል/ለማሳመን በቡድን መሥራት የተለመደ ነው። ነገር ግን ዴር ሽፒግል የዘገበው እውነት ከሆነ የገበያ ውድድሩ ላይ ተፅዕኖ የሚፍጥር እና የከባቢ አየርን የሚጎዳ በመሆኑ አብሮ መስራቱ ከሚጠበቀው በላይ ሄዷል። ይህ ሊወገዝ የሚገባው ፈፅሞም ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው። ገደብ የተጣሰ ይመስላል።"

የአውሮጳ ኅብረት እና የጀርመን መንግሥት ጉዳዩን በጥሞና እየመረመርን ነው ብለዋል። የጉዳዩ ውስጠ ምስጢር እንዲህ በፍጥነት የሚታወቅ አይመስልም። የሁለቱ ተቋማት የምርመራ ውጤት እና ቅጣት ግን ኩባንያዎቹ የሚከተሉትን የአሰራር ስልት እስከ ማስቀየር ሊደርስ ይችላል። 

ዳይምለር ባለፈው ዓመት ከተፎካካሪዎቹ ጋር የጭነት ተሽከርካሪዎችን ዋጋ በድርድር ተምኗል በሚል ተከሶ 1.1 ቢሊዮን ዩሮ ተቀጥቶ ነበር። ኩባንያዎቹ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ በአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን አሊያም በጀርመን መንግሥት የገበያ ውድድር ጥበቃ ተቋም ካለፈው አመት ሽያጫቸው አስር በመቶ ሊቀጡ እንደሚችሉ ሬውተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል። በኩባንያዎቹ የጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም. ሽያጭ መሰረት ቅጣቱ እስከ 50 ቢሊዮን ዩሮ ሊደርስ አንደሚችል የዜና ወኪሉ ጨምሮ አትቷል። ይኸ ግን በመሰረተ ኃሳብ ደረጃ ነው። ፈርዲናንድ ዱደንሆፈር እንደሚሉት የጀርመን የመኪና አምራቾችን የሚያሰጋቸው በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠረው ቅጣት ብቻ አይደለም። በደንበኞቻቸው ዘንድ ያላቸው እምነት ጭምር እንጂ። 

"እነዚህ የሕገ-ወጥ ትብብር ውንጀላዎች እውነት ሆነው ከተገኙ መኪና አምራቾቹን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ያሳጣቸዋል። ይህ በአንድ ጊዜ የሚፈጸም ከፍተኛ ክፍያ ነው። ይጎዳል ቢሆንም ሊቋቋሙት የሚችሉት ነው። የከፋው የእምነት እጦት ይሆናል። ከማያምኑት ላይ በ100,000 ዩሮ መኪና የሚገዛው ማነው?"

አውዲ የበካይ ጋዝ ልቀት ቁጥጥርን ለማሳደግ ለ850, 000 ደንበኞቹ መኪኖች በነፃ ሶፍትዌሮቻቸውን ከፍ ለማድረግ ጥሪ አቅርቧል። ዳይምለር በበኩሉ ለ3 ሚሊዮን መኪኖች ተመሳሳይ እገዛ ሊያቀርብ ተስማምቷል። ይህ ግን የመኪና አምራቾቹን የአክሲዮን ድርሻ ለገዙ ባለወረቶች በቂ አይመስልም። የኩባንያዎቹ የአክሲን ዋጋ ባለፈው አርብ እስከ 5 በመቶ አሽቆልቁሎ ነበር። 

ፖለቲከኞቹ ከጀርመን ሰማይ ገለል ማለት ለተሳነው የበካይ ጋዝ ልቀት መፍትሔ ፍለጋ እያማተሩ ነው። ናፍጣ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን ከጀርመን አውራጎዳናዎች ፈፅሞ ማገድ በፖለቲከኞቹ ዘንድ እንደ አማራጭ እየታየ ነው። የጀርመን መኪና አምራቾች ሰብሰብ ብለው በከተሙባት ሽቱትጋርት ይኸንንው እርምጃ ተግባራዊ ለማድረግ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ጉዳዩን ፍርድ ቤት አድርሰውታል። አምራቾቹ የሽቱትጋርትን እርምጃ በጥንቃቄ እየተከታተሉ ነው። በጀርመን ከሚመረቱ ተሽከርካሪዎች መካከል 50 በመቶው በናፍጣ የሚሽከረከሩ ናቸው። የዓለም አቀፉ የንጹህ ትራንስፖርት ድርጅት የአውሮጳ ቢሮ ኃላፊ ፒተር ሞክ የናፍጣ ተሽከርካሪዎች እጣ ፈንታ አዋጪ አይደለም ሲሉ ይናገራሉ።

"ናፍጣ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች ጉዳይ ከዚህ በኋላ አዋጪ አይደለም። በብቃት ረገድ ከዚህ ቀደም ጠቀሜታ ነበረው። የናፍጣ ቀረጥ አነስተኛ የነበረ በመሆኑ በመንግሥት ድጎማ ይደረግለት ነበር። ይህ ሁሉ እየቀረ ነው። ናፍጣ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች ከፍተኛ ግፊት እና ከፍተኛ ሙቀት ስላላቸው ቴክኖሎጂው በአንፃራዊነት እየተወደደ ነው። ናፍጣ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች ሞተር ሲሰራ ቤንዚን ከሚጠቀሙት አኳያ 1500 ዩሮ ተጨማሪ ወጪ አለው። ስለዚህ አዋጪ አይደለም። ቴክኖሎጂውን ንጹህ ማድረግ ቢቻል እንኳ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪኖች ዋጋ ርካሽ እየሆነ ነው። እናም የናፍጣ ተሽከርካሪዎች የነበራቸውን ብልጫ በማጣታቸው ከጥቅም ውጪ መሆናቸው አይቀርም። 

ጀርመናውያን በፎልክስቫገን፤ቢኤምደብሊው እና ሜርሴዲስ መኪኖቻቸው አብዝተው ኩራት ይሰማቸው ነበር። የኩራታቸው ምንጭ ግን በገዛ ጎዳናዎቻቸውም ይሁን በዓለም አቀፍ ገበያ ፈተና በዝቶባቸዋል። የዶይቼ ቬለው የቢዝነስ ዘገባ አርታኢ ሔንሪክ ቦሕመ "በአጭበርባሪ ማን ሊኮራ ይችላል?" ሲል አሳሳቢነቱን ይገልጣል።  

የፎልክስቫገን የበካይ ጋዝ ልቀት ቅሌት ሲሰማ የጀርመን የመኪና አምራቾች በደንበኞቻቸው ዘንድ የነበራቸው ከበሬታ እጅጉን አሽቆልቁሏል። አሜሪካንን ጨምሮ በተለያዩ ገበያዎች የበካይ ጋዝ ልቀታቸውን የሚደብቁ ተሽከርካሪዎች ሸጧል የሚል ክስ የቀረበበት ፎልክስቫገን ጥፋተኝነቱን ቢቀበልም አመራሮቹ ተጠያቂነትን ገሸሽ ማድረግ ችለዋል የሚል ወቀሳ ይደመጣል። እስካሁን በይፋ ክስ የተመሰረተባቸው በዩናይትድ ስቴትስ የኩባንያው ሥራ አስፈፃሚ የነበሩት ኦሊቨር ሽሚት ብቻ ናቸው። ጀርመን በበካይ ጋዝ ልቀት ቅሌቱ እጃቸው አለበት አሊያም ተጠያቂ ናቸው ከተባሉ ግለሰቦች መካከል በቁጥጥር ስር ያዋለችው አንድ ሰው ብቻ ነው። ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ እንደዘገበው በአሜሪካ ፌድራል የምርመራ ቢሮ ባለፈው ጥር ወር በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሽሚት በቀረበባቸው ክስ በጠበቃቸው በኩል ጥፋተኛ ነኝ ብለው ለመቀበል ተስማምተዋል። ዳይምለር እና ሉፍታንዛን በመሳሰሉ ኩባንያዎች ውስጥ ያገለገሉት ቶማስ ዛትልበርገር ጀርመን ተጠያቂዎችን ለፍትኅ ለማቅረብ ዳተኛ ናት ሲሉ ይወቅሳሉ።

"ዩናይትድ ስቴትስ በንግድ ሥራ ውስጥ የሚፈጸሙ የማጭበርበር የወንጀል ድርጊቶችን የመከታተል ልምድ አላት ብዬ አምናለሁ። በጀርመን ፍትኅ ዳተኛ እና ሰነፍ ነው። እንዲህ አይነት ድርጊቶችንም በጥብቅ አይከታተልም።  በዚህ ረገድ የአሜሪካ የፍትኅ ስርዓትን አደንቃለሁ።"

የዴር ሽፒል ዘገባ የጀርመን ፖለቲከኞች በመኪና አምራቾቻቸው ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ ለመውሰድ ቸልተኛ ናቸው የሚል ወቀሳም አዝሏል። የመራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ቃል-አቀባይት ጉዳዩ በጥልቀት ሊመረመር እንደሚገባ ተናግረዋል። የጀርመን የተሽከርካሪ አምራቾች ማኅበር ኃላፊ ማቲያስ ቪዝማን በበኩላቸው ሰዎች አሁን በተሰማው ቅሌት ብቻ ስለ ጠቅላላው የሚና ማምረቻ ዘርፍ ድምዳሜ ላይ ሊደርሱ አይገባም ሲሉ ተናግረዋል። በባደር ባንክ የካፒታል ትንታኔ ኃላፊው ሮበርት ሐልቨር ግን የተለi አቋም አላቸው። ሐልቨር እንደሚሉት ከመጋረጃ ጀርባ ይደረግ ነበር የተባለው ትብብር እውነትነት ከተረጋገጠ ጉዳቱ የከፋ ነው።"የትብብሩ ጭምጭምታ አንዳች የእውነት መሰረት ካለው የከፋ ችግር ይገጥመናል። በርካታ ሥራዎች እና የጀርመን ምርቶች ኅልውና አደጋ ላይ ይወድቃል። በእነዚህ ኩባንያዎች ውስጥ የቦርድ አመራር ሆነው የተቀመጡ ሁሉ በፍጥነት አስፈላጊውን መረጃ ያቀርባሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ከተሰናቸው ሌላ ሥራ ይፈልጉ።'' 
የጀርመን የመኪና ማምረቻ ዘርፍ ከአጠቃላይ የኢንዱስትሪው የገቢ መጠን የ20 በመቶ ድርሻ አለው። በጀርመን ብቻ 800,000 ሰዎች በዚሁ ዘርፍ ተቀጥረው ይሰራሉ። 

እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ 

Audios and videos on the topic