የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ሥጋት ተጭኖታል | ዓለም | DW | 26.04.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ሥጋት ተጭኖታል

የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መመረጥ በኋላ ከሌላው ጊዜ በከፋ ሥጋት ውስጥ ወድቋል ተባለ።

ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች የተባለው የመገናኛ ዘዴ ነፃነት ተሟጋች ድርጅት ዛሬ ይፋ ባደረገው ዓመታዊ ዘገባ በትራምፕ የምረጡኝ ቅስቀሳ እና ብሪታኒያ ከአውሮጳ ኅብረት አባልነት እንድትወጣ በተደረገዉ  ዘመቻ መገናኛ ብዙኃንን የማጣጣል ተግባር ተስፋፍቷል ብሏል። ድርጅቱ በመገናኛ ብዙኃን ላይ የተጀመረው ዘለፋ «አሳሳቢ ደረጃ» ላይ ደርሷል ብሏልም። የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት በስለላ እና በአምባገነን መሪዎች ተጨቁኗል ያለው ድርጅቱ የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት እንዲህ የከፋ ሥጋት ውስጥ ወድቆ አያውቅም ሲል አክሏል።

ዛሬ ይፋ በተደረገው ዘገባ አሜሪካ እና ብሪታኒያ ከቀድሞ ደረጃቸው አሽቆልቁለው 43ኛ እና40ኛ ደረጃ ይዘዋል። አመታዊው ዘገባ በተለይም ዴሞክራሲያዊ በሚባሉ አገሮች ፕሮፖጋንዳ እና የነፃነት ጭቆና መስፋፋቱን አትቷል። ፖላንድ እና ሐንጋሪም ትችት የጠወለገባቸው አገራት ተብለዋል። የፕሬስ ነፃነትን በማስከበር ኖርዌይ እና ፊንላድ ከአናት ተቀምጠዋል። ከ180 አገሮች ኢትዮጵያ አምና በነበረችበት 150ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ቱርክ በፕሬዝዳንቷ ሬሴብ ጣይብ ኤርዶኻን ላይ ከተሞከረው መፈንቅለ-መንግስት በኋላ ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች 'ትልቅ እስር ቤት' ሆናለች ብሏል ዘገባው። ኤርትራ ደረጃዋን አሻሽላ 179ኛ ስትሆን ሰሜን ኮሪያ መጨረሻ ተቀምጣለች። 

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ