የመጀመርያ የት/ቤት ቀን በጀርመን | ባህል | DW | 20.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የመጀመርያ የት/ቤት ቀን በጀርመን

የራድዮ ጣብያችን በሚገኝበት ግዛት የሚገኙ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የአንደኛ ክፍል ተማሪዎችን ባህላዊ ሥነ-ስርዓት እንኳን ደህና መጣችሁ ሲሉ ተቀብለዋል። ልጅ በእድሉ ይደግ በማይባልበት በጀርመን የሚኖር ሕፃን ከእናቱ ማህፀን ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ መንግሥት ጤንነቱን እየተቆጣጠረ እያስተማረ ወላጆቹን እየደገፈ ለአካለ መጠን ያደርሰዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:57
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
15:57 ደቂቃ

የመጀመርያ የት/ቤት ቀን በጀርመን


ሕጻኑ ለአንደኛ ክፍል መንደርደርያ በሚሆነዉ በናት መዋያ «ኪንደር ጋርደን» ለአንደኛ ደረጃ የትምህርት ገበታ የሚያበቃዉን እዉቀት ይገበያል፤ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚረግጥበትን ቀን በጉጉት ይጠብቃል። አንደኛ ክፍልን ለመጀመር ለመጀመርያ ጊዜ ትምህርት ቤቱን በረገጠበት ዕለት ታድያ በድግሥና ባህላዊ ሥነ-ስርዓት እንኳን ለዚህ በቃህ ሲባል አቀባበል ይደረግለታል። በዚህ ዝግጅታችን በጀርመን የመጀመርያ የትምህርት ቤት ቀን ክብረ በዓልን እንቃኛለን።« ዛሬ ት/ቤት ይከፈታል፤ ዛሬ ትምህርት ጀምረሃል፤ ዛሬ መጻፍ ማስላት ትምህርት ይጀምራል» ይላል በጀርመንኛ የተደመጠዉ ሙዚቃ፤ ትምህርት የሁሉም ነገር መፍቻ ቁልፍ ነዉ።
በጀርመን አንድ ህፃን ከስድስት ዓመቱ ጀምሮ ትምህርት የመጀመር ግዴታ አለበት ይህን ህግ ያላከበረ ወላጅ በሕግ ይጠየቃል ኑም ትምህርት ቤት እንዲገባ ይደረጋል። ከህጻናት መዋያ ወጥቶ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን አንድ ሲል በመጀመርያዉ ቀን ትምህር ቤቱን ሲረግጥ በጀርባ የሚታዘለዉን ቦርሳ አንግቦ በቤተሰቦቹ የተዘጋጀዉን የስጦታ ጥቅል በጀርመንኛ መጠርያዉ «ሹል ቱተን» ይዞ በወላጅ በዘመድ አዝማድ ታጅቦ ትምህርት ቤቱ ሲገባ እንኳን ደህና መጣህ ሲባል በትምህርት ቤት አቀባበል ይደረግለታል። በቦን ነዋሪ የሆኑት አቶ አሌክስ ደምሴ የስድስት ዓመት ልጃቸዉን ሊያ ዘነበች ሲልቪያን ደምሴን አንደኛ ክፍል አስገብተዋል። በትምህርት ቤት የመጀመርያዉ ቀን አቀባበል ሥነ-ስርዓት እጅግ ደማቅ እንደነበር ተናግረዋል።
አካባቢ በትምህርት ይለወጣል፤ ማህበረሰብ በትምህርት ይነቃል ፤ ዓለምን በትምህርት ትገኛለች ይላሉ፤ ከጀርመናዊ ባለቤታቸዉ ጋር በቦን ከተማ የሚኖሩት ኢንዶኔዥያዊት ፊዲ ሌጎቮ፤ የስድስት ዓመት ልጃቸዉ ዴቪዲን አንደኛ ክፍል ካስገቡ ዛሬ አንድ ሳምንት ሆናቸዉ። የጀርመኑ የመጀመርያ ትምህርት ቤት ቀን ባህላዊ አከባበር ይላሉ ኤንዶኔዝያዊትዋ ቪዲ፤«ስለዝግጅቱ ከእህቶቼ አዉቃለሁ፤ ያደኩት ጀርመን ዉስጥ ነዉ ። የእህቴ የመጀመርያ የትምህርት ቤት ቀን ጀርመን አኸን ከተማ ዉስጥ ነበር። ዝግጅቱ ግን በጣም ትንሽ እንደነበር አስታዉሳለሁ። የነበሩት ቤተሰቦቼ ብቻ ነበሩ። እህቴም ያገኘችዉ አንድ ስጦታ ብቻ ነበር። ት/ቤት ከተዘጋጀዉ መሰናዶ ሌላ ት/ቤት ዉስጥ የተደረገ ነገርም አልነበረም። ምሥራቅ ጀርመን ያደገዉ ባለቤቴ ግን እንደነገረኝ ከሆነ በተወለደበት አካባቢ የመጀመርያ የት/ቤት ቀን በደማቅ ዝግጅት ነዉ የሚከበረዉ፤ አያት፤ አክስት፤ እህት ጎረቤት ሁሉ ይሰባሰባል። እናም የኛ ልጅ በመጀመርያዉ የትምህርት ቤት ቀን የባሌና የኔ ወላጆች አክስት፤ አጎት የቅርብ ቤተሰብ ሁሉ ተሰባስቦ ነበር። ት/ቤት ከተደረገዉ ዝግጅት በኋላ ቤት ዉስጥ ያዘጋጀነዉን ትልቅ ላይ ድግስ ላይ ተገኝተዋል። »
በኤንዶኔዥያ የመጀመርያ የትምህርት ቤት ቀን የሚደረግ ዝግጅት ይኖር ይሆን? ቪዲ ሌጎቮ እንደሚሉት ምንም አይነት ዝግጅት የለም ክፍል ገብቶ ትምህርት መቀጠል ብቻ ነዉ።
« በመጀመርያ የትምህርት ቤት ቀን ምንም የሚነገረን ወይም የምናደርገዉ ልዩ ዝግጅት የለም። ቤተሰቦች ወደ ትምህርት ቤት ያመጡሃል፤ ትምህርት ቤት ወስጥ የምታለቅስ ከሆነ እንደኔ የመጀመርያ የትምህርት ቤት ቀን እንዳረኩት ቤተሰብ ይጠብቅሃል። እኔ ስላለቀስኩ በመጀመርያዉ ዕለት የትምህርት ቀኔ እናቴ ተምሪ እስክጨርስ ድረስ ትምህርት ቤት ጊቢ ዉስጥ ሆና ጠብቃኛለች። እና እንዲህ ነዉ እኛ ጋ ። ትምርት ቤት ስለገባህ የሚሰጥ ስጦታ ምናምን የለም። እናም እኔ እዚህ ጀርመን ልጄን ትምህርት ቤት ሳስገባ እዚህ እንደሚከበረዉ አንደ ሀገሩ ባህል ቤተሰቦቼ ከኢንዶኔዥያ መጥተዉ አብረን አክብረናል »


በጀርመን ሲኖሩ 31 ዓመት የሆናቸዉ አቶ መስፍን አማረ፤ ሁለቱ ልጆቻቸዉ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ገበታን የጎበኙት እዚሁ በጀርመን ነዉ፤ የመጀመርያ ት/ ቤት ባህላዊ አከባበር ለሕጻናቱ ብቻ ሳይሆን ለወላጆችም ትልቅ ነገር ነዉ ሲሉ ገልፀዋል።

የህጻኑ ቤተሰቦች በመኖርያቸዉ አካባቢ ይስማማናል ብለዉ የመረጡት ትምህርት ቤት ልጆቻቸዉን ለማስመዝገብ ሲሄዱ የህቻኑ ሙሉ ጤንነት መጠበቁን አስፈላጊ የተባሉትን ክትባቶች ሁሉ መዉሰዱን የሚያሳይ የህክምና ወረቀት ይዘዉ ነዉ በደቡባዊ ጀርመን ኑረምበርግ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ካሱ ለገሰ የሁለት ልጆቻቸዉን የመጀመርያ ቀን የትምህርት ቤት ቀን የአከባበርና የአቀባበል ሥነ ስርዓት አይተዋል።
በጀርመን ባህል ልጆች ከህፃንነታቸዉ ጀምሮ አንድ የህይወት ምዕራፍን ሲያልፉ ይከበርላቸዋል የሚሉት አቶ መስፍን በመቀጠል፤ በሌላ በኩል በጀርመን ሃገር የትምህር ቤት መዘግያ ወቅት ከግዛት ግዛት ቀኑ የተለያየ ነዉ ይህ ለምን ይሆን አቶ መስፍን አማረ በዝርዝር አስረድተዋል።

የስድስት ዓመት ወንድ ልጅ ያላቸዉ ኢንዶኑዥያዊት ፊዲ ሌጌቮ በጀርመን የት/ቤት መጀመርያ ቀን ክብረ በአል ጥሩ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ይላሉ፤


« ሥነ-ስርዓቱ ጥሩ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ይህ የሚሰጡት ስጦታ እና መሰናዶ ከእንግዲህ ህጻናት መዋያ የምትሄድ ህጻን አይደለህም፤ ለአንደኛ ክፍል በቅተሃል በሚል ለህጻኑ ስሜታዊ ማዕረግ ምልክት መስጫ ይመስለኛል። ሹል ቱተ የሚባለዉ ስጦታ ጥቅልም ህጻኑ አዲስ የህይወት ምዕራፍን መጀመሩን የሚያሳየዉ ምልክት መሆኑ ነዉ። በጀርመን የመጀመርያ የትምህርት መጀመርያ ዕለት የስጦታ ጥቅል ማለት ሹል ቱተና በጀርባ የሚታዘል የትምህርት ቤት ቦርሳ የማይቀር ነገር ነዉ።»
በትምህርት ገበታ የመጀመርያ ቀን ያላችሁን ትዉስታ አካፍሉን፤ ያላችሁም አስተያየት አይለየን እያልን ሙሉዉን ዝግጅት የድምፅ ማድመጫዉን ማዕቀፍ በመጫን ሙሉዉን መሰናዶ እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ


ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic