የመጀመርያዎቹ የሶርያ ስደተኞች በጀርመን | ዓለም | DW | 12.09.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የመጀመርያዎቹ የሶርያ ስደተኞች በጀርመን

ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ከሚሽን ጋር በተደረገ ስምምነት፤ ጀርመን የሶርያን 5000 ስደተኞች መቀበል ይኖርባታል።

መጓጓዣቸዉን በራሳቸዉ ወጪ የከፈሉ ወደ 300 የሚጠጉ የሶርያ ስደተኞች ከሰኔ ወር መጨረሻ አንስቶ ጀርመን መግባት ጀምረዋል። የሀገር አስተዳደር ሚንስትር ሃንስ ፔተር ፌሪድሬሽ እና የታኅታይ ሳክሰኒ መስተዳድር የዉስጥ ጉዳይ ሚንስትር ቦሪስ ፒስቶሪየስ ፣ በፊደራል ጀርመን በተዘጋጀ ልዩ በረራ ትናንት ረቡዕ ጀርመን የገቡን 107 የሶርያ ስደተኞች አቀባበል አድርገዉላቸዋል። የሀገር አስተዳደር ሚንስትሩ እንዳሉት፤ ስደተኞቹ ባለፉት ወራት ብዙ ችግር ነው ያዩት። ሶርያዊዉ ህጻን ጃን ሙስተፋ በአየር ጣብያዉ እንግዳ መቀበያ ማረፍያ ወንበር ላይ ከመቀመጥ ይልቅ ለመጫወቻነት ባገኘዉ ከሳሙና አረፋ ፊኛ መሰል ድብልብል ቅርፅ የሚያወጣ መጫወቻን ይዞ ቡልቅ ቡልቅ እያደረገ ወደ ቪዲዮ መቅረጫ አቅጣጫ እየበተነ ይጫወታል። የሁለት ዓመት ከመንፈቅ ባለድሜዉ ህጻን፤ ከብዙ ሰዓታት የአዉሮፕላን ጉዞ በኋላ፤ አዉሮፕላን ማረፍያዉ እንግዳ መቀበያ ክፍል ዉስጥ እንደልቡ መሆኑ ያስደሰተዉ ይመስላል። ከህጻኑ ጎን አባቱ ቻሊል ሙስተፋ ተቀምጠዋል፤ አቶ ቻሊል ሙስጠፋ በህይወታቸዉ ለመጀመርያ ግዜ ለጋዜጠኛ ቃለ ምልልስ መስጠታቸዉን ይናገራሉ፤

« በነፃ ሃሳቤን መግለፅ፤ መናገር መቻሌ፤ በቃላት ልገልፀዉ የማልችል ስሜትን ነዉ የፈጠረብኝ »

ቻሊል ሙስተፋ ባለቤታቸዉ እና ህጻኑ ወንድ ልጃቸዉ በሊባኖስ በሚገኝ በአንድ የስደተኞች መጠለያ ጣብያ ለስምንት ወራት ቆይተዋል። የሶርያዉ የእርስ በዕርስ ጦርነት ለረሃብ ለስደት ዳርጎአቸዋል። በአሁኑ ሰዓት ግን አቶ ቻሊል ሙስጠፋ ደህንነቱ በተረጋገጠ ቦታ ላይ ናቸዉ። የ26 ዓመትዋ ጃኔት ሙራትም በጀርመን መጠለያን በማግኘትዋ የተሰማትን ደስታ መግለጽ ተስኖአታል፤« ለረጅም ግዜ እዚህ የምደርስበትን ወራቶች በጣም ጠብቄያለሁ። አሁን ደስተኛ ነን ሁሉ ነገር ቀሎኛል»ጃኔት ሙራት እግሯ አዉሮፕላኑን እስከ ረገጠበት ግዜ ድረስ ጉዞዉ ይሳካል አይሳካም፤ በቂ የማስረጃ ወረቀት አለኝ የለኝም በሚል፤ ብዙ አስባለች ሰግታም ነበር። አሁን ግን ጀርመን አዉሮፕላን ጣብያ ደርሳለች፤ ማረፍያ ክፍል ወንበር ላይ ተቀምጣ ፈግግ ብላ አይኗን ሰበር እያደረገች የከበቧትን ጋዜጠኞች ትቃኛለች። የጀርመኑ የሀገር አስተዳደር ሚንስትር ሃንስ ፔተር ፌሪድሬሽም እዝያዉ አካባቢ ከጋዜጠኞች ጋር ቃለ ምልልስ እያደረጉ ነዉ። ፌሪድሪሽ በሶርያ ያለዉን ቀቅታዊ ሁኔታ በመጥቀስ አዉሮጳዉ ሕብረት መስራት አለበት የሚሉትን ጉዳይ ይገልጻሉ፤«በአዉሮጳ ሕብረት ደረጃ፤ በተቻለ መጠን አንድ የአዉሮጳ ሕብረት የስደተኞች ጉዳይ ስብሰባ በአስቸካይ እንዲደረግ አጥብቄ እጠይቃለሁ። የሶርያ ስደተኞች ችግር ጉዳይ የአዉሮጳ ሕብረት ችግር ይመስለኛል፤ ስለዚም የአዉሮጳ ሥራ መሆኑን አዉቀን መቀበል ይኖርብናል። በዚህም አዚህ አንድ ዉይይት እንዲካሄድ አዉሮጳን እወተዉታለሁ»

ጀርመን ተጨማሪ የሶርያን ስደተኞችን ትቀበላለች አትቀበልም የክርስትያን ዴሞክራቲክ ህብረት ፓርቲ አባሉ የሀገር አስተዳደር ሚንስትር፤ ፍሪድሪሽ የገለፁት ነገር ግን የለም፤ ምንም እንኳ የታኅታይ ሳክሰኒ መስተዳድር የዉስጥ ጉዳይ ሚንስትሩና የሶሺያል ዴሞክራት ፓርቲ አባሉ ቦሪስ ፒስቱሪዩስ ጀርመን የሶርያን ስደተኞችን በመቀጠል እንደትቀበል ቢጠይቁም

«ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ከሚሽን ጋር በተደረገ ስምምነት፤ 5000 ስደተኞችን መቀበላችን ጥሩ እና ስፈላጊ ነዉ። በርግጥም መርዳት የምንፈልግ ከሆነ ስደተኞችን መቀበሉ አስፈላጊ የሚሆንበት እና ተጨማሪ መቀበል የሚያስፈልግበት ግዜ ይመጣል፤ ይህን ማድረግ ደግሞ አንችላለን፤ ይሆናልም »ጀርመናዉያኑ ሚኒስትሮችን አዉሮፕላን ጣብያ ቃለ ምልልስ ሲሰጡ፤ ሶርያዉያኑ አዉሮፕላን ጣብያ ለመጀመርያ ቀናት የሚያስፈልጋቸዉን አነስ ባለ የጨርቅ ከረጢት የተቋጠረ ነገርን በመቀበል ስነ-ስርዓቱ ተጠምደዉ ስለነበር በርግጥም አልተከታተሉም። ሴቶች ወንዶችና ህጻናትን በጠቅላላ 107 ሶርያዉያን ያቀፈዉ የመጀመርያዉ የሶርያ ስደተኞች ቡድን ትናንት ጀርመን ሃኖቨር ከተማ አዉሮፓላን ጣብያ ሲደርስ ጉዞዉ ተጠናቀቀ እንጂ፤ ሶርያዉያኑ ሊኖሩበት ወደታቀደላቸዉ የመጀመርያ ማረፍያ ለመድረስ ገና ይጓዛሉ፤ የታኅታይ ሳክሰኒ ከተማ ወደ ሆነችዉ ፍሪድላንድ ወደተባለችው ከተማ። እዝያም እንደደረሱ በቅድምያ ለሁለት ሳምንት በመጀመርያ አስፈላጊ የመግባብያ ቋንቋን ተምረዉና ፤ የሀገሪቱን ባህል ተዋዉቀዉ ከሁለት ሳምንት በኋላ በተለያዩ የጀርመን ከተሞች እና አካባቢዎች መኖር ይጀምራሉ። ህጻን ጃን ከቤተሰቦቹ ጋር ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ኪል ከተማ እንሚኖር ቢታወቅም፤ አሁን ለህጻን ጃን ይህ አያሳስበዉም ይልቅዪ አይኑ ያረፈዉ ፤ ፉፉፉፉፉ እያለ እፍ ላይ መጫወቻዉን አስደግፎ ከሳሙና አረፋ ቡልቅ ቡልቅ እያደረገ የሚወጣዉ ድብልብል እንቁላል የሚያክል የአረፋ ኳስ ላይ ነዉ።

አዜብ ታደሰ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic