የመጀመሪያው የአቶሚክ ቦምብ ፍንዳታ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 22.07.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የመጀመሪያው የአቶሚክ ቦምብ ፍንዳታ

የመጀመሪያው የአቶሚክ ቦምብ ሙከራ። የዛሬ 70 ዓመት ነበር። ኒው ሜክሲኮ ውስጥ በሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ በረሃ ውስጥ ነበር ሙከራው የተኪያሄደው። ከዚያን ጊዜ አንስቶም የአቶሚክ ቦምብ ለዓለማችን ነዋሪዎች እና ተፈጥሮ ስጋት ሆኖ ቀጥሏል። ክርር ባለው ፀሓይ የሚዥበረበረው የኒው ሜክሲኮ የበረሃ አሸዋ የሠማዩ ነጎድጓድ አጅቦታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:35
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
11:35 ደቂቃ

የመጀመሪያው የአቶሚክ ቦምብ ፍንዳታ

በጎርጎሪዮሣዊው አቆጣጠር ሐምሌ 16 ቀን 1945 ዓ.ም. ልክ ከማለዳው 11 ሰአት፤ ከ29 ደቂቃ፤ ከ45 ሠከንድ። የመጀመሪያው የአቶሚክ ቦምብ ሙከራ በዩናይትድ ስቴትሷ ግዛት ኒው ሜክሲኮ ውስጥ ተደረገ። ይኽ ሙከራ በተፈጸመ በ21ኛው ቀን በሌላኛው የዓለም ጥግ፤ በሩቅ ምሥራቋ ጃፓን በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት በዚሁ እጅግ አደገኛ ግዙፍ ቦንብ በቅፅበት ውስጥ ጠፍቷል። የአቶሚክ ቦምብ የመጀመሪያው ሙከራ የተደረገበት 70ኛ ዓመት።

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጫፍ የደረሰበት ወቅት ነው። የዩናይትድ ጦር ሠራዊት ቀደም ሲል ሙሉ ለሙሉ ያልሞከረው የአቶሚክ ቦንብ ፍንዳታ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ፣ አለያም ጥፋት ለማጤን በኒው ሜክሲኮ በረሃ ሣይንቲስቱ ተሰባስበዋል። የሙከራ ፍንዳታው ሊኪያሄድ የታቀደው ሰው ከማይደርስበት እዚሁ በረሃ ውስጥ ነው።

የመጀመሪያው የአቶሚክቦንብ የፈነዳበት ቦታ መታሰቢያ

የመጀመሪያው የአቶሚክቦንብ የፈነዳበት ቦታ መታሰቢያ

በሮበርት ኦፐንሃይመር እና ጄነራል ሌስሊ ግሮብስ አመራር ስር የነበረው የጥናት ቡድን ለሙከራ የተፈለገውን የአቶሚክ ቦንብ ሲቀምር እና ሲያቀናብር ሦስት ዓመት ከሰባት ወራት ፈጅቶበታል። ይኽ የሁለተኛው የዓለም ጦርነትን በማያዳግም መልኩ ለመቋጨት ታስቦ የተሰናዳ ግዙፍ ቦምብ «መሣሪያው» የሚል የምሥጢር ስም ተሰጥቶታል። ቦምቡ እጅግ ግዙፍ እና መጠነ-ሠፊ ጥፋት የሚያስከትል ነው።

ዶ/ር ዳዊት ሰለሞን ወርቁ በደቡብ አፍሪቃ ኬፕታውን ከተማ፤ በኬፕ ፔኒዙዌላ የስነ-ቴክኒክ ዩኒቨርሲቲ፤ በፊዚክስ ዲፓርትመንት ውስጥ መምህር እና ተመራማሪ ናቸው። በኒውክሊየር ፊዚክስ የፒኤች ዲ ዲግሪም አላቸው። ስለአተም እና አቶሚክ ቦምብ ምንነት ያብራራሉ።

እነዚህ በአጉልቶ በሚያሳይ ልዩ መነፅር ካልሆነ በሌጣ ዓይን የማይታዩ እጅግ ደቃቃ ቁሶች በሚያደርጉት የርስ በርስ ግጭት የሚፈጠረው ፍንዳታ እና ያን የሚከተለው ሙቀት በጣም ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል። ወደ ኋላ የዛሬ 70 ዓመት በእግረ-ኅሊና እንመለስ። በኒው ሜክሲኮ በረሃ ሣይንቲስቶቹ የመጀመሪመሪውን የአቶሚክ ቦንብ ሙከራቸውን አድርገው ውጤቱን እስኪያዩ ቸኩለዋል።

ከመጀመሪያው የአቶሚክ ቦንብ ፍንዳታ ሙከራ ቅሪት

ከመጀመሪያው የአቶሚክ ቦንብ ፍንዳታ ሙከራ ቅሪት

ለመጀመሪያ ጊዜ የፍንዳታ ሙከራ ወደ ኒው ሜክሲኮ በረሃ የተወሰደው ግዙፉ የአቶሚክ ቦንብ የተዋቀረው ፕሉቶኒየም ከተሰኘው ንጥረ-ነገር ነው። እጅግ ደቃቅ የሆነው ፕሉቶኒየም በባሕሪው ተፈረካካሽ ሲሆን ዙሪያውን እጅግ በርካታ በሆኑ ተቀጣጣይ ቁሶች የተከበበ ነው። ተቀጣጣይ ቁሶቹ ከውስጥ ሲጫሩ ፕሉቶኒየሞቹ ውስጥ ለውስጥ በፍጥነት እና በኃይል እርስ በርስ እንዲላተሙ ያደርጋል፤ በዚያ ግጭትም አቶሚክ ቦንቡ ፈንድቶ ኃያል ነውጥ ይፈጥራል።

የአቶሚክ ቦንቡ የመጀመሪያ ሙከራ በኒው ሜክሲኮ በረሃ በምሥጢር ሊደረግ ታቅዶ የነበረው ከንጋቱ 10 ሰአት ላይ ነበር። በወቅቱ በረሃማው አካባቢ ከፍተኛ ነጎድጓድ እና መብረቅ ስለተደጋገመበት ሣይንቲስቶቹ አቶሚክ ቦንቡን 30 ሜትር ከፍ ወዳለ የብረት ፍርግር ላይ አውጥተው ወደየማደሪያቸው ይሰማራሉ። እናም ለሙከራ የተሰቀለውን ቦንብ ከጥቂት ቀናት በኋላ ከሣይንቲስቶቹ ቀድሞ መብረቅ ይመታዋል። አንዳች ነውጥ እና ኃያል ብርሃን ከበረሃማዋ ኒው ሜክሲኮ አልፎ ከብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይም ታየ። የአቶሚክ ቦንቡ ፍንዳታ በፈጠረው ከፍተኛ ሙቀት የተነሳ የበረሃው አሸዋ ቀልጦ ፈሷል።

የመጀመሪያውን የፍንዳታ ሙከራ ለማከናወን በእርግጥ ሣይንቲስቶቹ ከሁለት ሰአት ቀደም ብለው ከሌሊቱ ስምንት ሰአት ላይ ተሰባስበው ነበር። የተሰባሰቡበት ቦታ የሙከራ ፍንዳታው ከተደረገበት ስፍራ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነበር። ቦታው «ነጥብ ዜሮ» ይሰኝል። በመጥፎ የአየር ጠባይ የተነሳ የሙከራ ፍንዳታው ለአንድ ሰአት ተኩል ያኽል ቢሸጋሸም ባልተጠበቀ ሰአት ሙከራውን ያስጀመረው መብረቅ ነው።

ከፊል የሔሮሺማ ከተማ በፍንዳታው ጠፍቶ እጎአ 1945

ከፊል የሔሮሺማ ከተማ በፍንዳታው ጠፍቶ እጎአ 1945

በፍንዳታው የተፈጠረው ከፍተኛ ብልጭታ ከ300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ለመታየት ችሏል። ፍንዳታው ወደ ሰማይ 14 ኪሎ ሜትር ከፍታ ቡልቅ ሲል ታይቷል። ወደ ምድር ደግሞ ሦስት ሜትር ጠልቆ መሬቱን ገምሷል። 330 ሜትር ክብ ጉድጓድ ፈጥሯል። የአቶሚክ ቦንቡ የመጀመሪያ የሙከራ ፍንዳታ ከተከናወነበት ሥፍራ አንድ ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሕይወት ያለው ፍጡርን በአጠቃላይ አጥፍቷል።

ከዚህ የመጀመሪያ የአቶሚክ ቦንብ የሙከራ ፍንዳታ ሦስት ሣምንት በኋላ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ሠራዊት የአቶሚክ ቦንቦቹን እንደ ጎርጎሪዮሣዊው አቆጣጠር ነሐሴ 6 ቀን 1945 በሔሮሺማ ከተማ፣ በሣልስቱ ደግሞ በሌላኛዋ የጃፓን ከተማ በናጋሳኪላይ ከB 29 ቦንብ ጣይ አውሮፕላን ወረውራል። በጦሩ ዕቅድ መሠረትም ያለምንም ማወላወል ሁለቱ የአቶሚክ ቦንቦች ፍንዳታ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዲያከትም አድርገዋል። በጦርነቱ ግን ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች አልቀዋል። 90 በመቶ ሁለቱ የጃፓን ከተሞች በግዙፎቹ ቦምቦች ወድመዋል። 98 በመቶ ያህል የከተሞቹ ነዋሪዎችም በፍንዳታው ቅጽበት አለያም ዘግየት ብሎ አልቀዋል። ከፍንዳታው ያፈተለከው ጨረር የጉድጓድ ውኃ እና መስኮች ላይ ሰርጎ በመግባት በሰው ልጆች፣ በተፈጥሮ፣ እና ሕይወት ባላቸው ነገሮች ላይ ለረዥም ጊዜ ጉዳት ማስከተሉም ይነገርለታል።

የውቅያኖስ ንጣፍ ላይ በአቶሚክ ፍንዳታ የተፈጠረ ጉድጓድ፤ ጠቆር ያለው

የውቅያኖስ ንጣፍ ላይ በአቶሚክ ፍንዳታ የተፈጠረ ጉድጓድ፤ ጠቆር ያለው

የአቶሚክ ቦንብ ፍንዳታ ሰበብ በእርግጥም እንዲህ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ጣጣው ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ ነው። ለአብነት ያኽል ከመላው የጃፓን ከተሞች ውስጥ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የአጥንት መቅኒን ካንሰር የተመዘገበው የአቶሚክ ቦንብ በተጣለባት የጃፓኗ ሔሮሺማ ከተማ ውስጥ እንደሆነ ይነገራል።

የኒውክሊየር ሳይንስ ተመራማሪው ዶ/ር ዳዊት ሰለሞን ወርቁ የኑክሊየር ቦንብ በዓለም ኃያላን እጅ መገኘቱ ስጋት ቢፈጥርም፤ ኒውክሌር ጠቃሚ ጎን እንዳለውም ገልጠዋል።

የአቶሚክ ቦንብ የመጀመሪያ ሙከራ ከተደረገ 70 ዓመት አልፏል። በዚህ 70 ዓመታት ውስጥ ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ በሠላማዊ ውቅያኖስ ላይ 20 የአቶሚክ ቦንብ ፍንዳታ ሙከራዎችን አከናውናለች። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በተከሰተው የቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት ወቅትም የአቶሚክ ቦንብ ስጋት ሆኖ ቆይቷል። በዓለማችን በአሁኑ ወቅት 11 ሃገራት የአቶም ቦንብ አላቸው፤ አለያም ቁልፍን በእጃቸው የማስገባት አቅሙ አላቸው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic