የመድረክ ተውኔት በዶቼቬለ-የባህል መድረክ | ባህል | DW | 28.06.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ባህል

የመድረክ ተውኔት በዶቼቬለ-የባህል መድረክ

ቴአትር የተለያዩ ባህሎችን በማቀራረብ የሚያበረክተው ድርሻ ላቅ ያለ ነው። እዚህ ጀርመን ሐገር ቦን ከተማ ውስጥ ዶቼ ቬለ ሬዲዮ ጣቢያ ባዘጋጀው ዓለምአቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ጉባኤ ላይ የታየውም ይህንኑ አባባል ያስረግጣል። ረቡዕ ዕለት

default

ተዋንያኑ

ሰኔ 20 ቀን 2004 ዓ.ም. በተጠናቀቀው የ3 ቀናቱ ጉባኤ መክፈቻ የዶቼቬለ የአፍሪቃው ክፍል ባልደረቦች «የካሬምቦ ህልም» በሚል አጠር ያለ የመድረክ ተውኔት በእንግሊዘኛ ቋንቋ አቅርበው ነበር። ተውኔቱ አንዲት የ16 ዓመት ታዳጊ በሆነች አፍሪቃዊት ተማሪ ህልም ዙሪያ ያጠነጥናል።

Learning by Ear Workshop GMF 2012

ካሬምቦ

በመጠነኛ ቁሳቁስ አፍሪቃዊ ድባብ የተላበሰው መድረክ ላይ ካሬምቦ ከወላጆቿ በስተግራ ሲል በተነጠፈ ምንጣፍ ላይ ተኝታለች። እናቷ እና አባቷ ደግሞ ከመድረኩ በስተቀኝ በተመሳሳይ ሁኔታ ተጋደመው እያለሙ ነው። ከመድረኩ በተቃራኒ አቅጣጫ፣ ከታዳሚያኑ ጀርባ ከሚገኘው ኮምፒውተር በፕሮጀክተር የተለቀቀ የአንድ ቤት ምስልም ግድግዳው ላይ ይታያል። ኮረብታው ላይ ለብቻው ጉብ ያለ የሳር ክዳን የተላበሰ ጎጆ ነው። ታሪኩ የሚከናወነው እዚህ ጉብታ ላይ በብቸኝነት በተቀለሰው ጎጆ ቤት ውስጥ ነው ለማለት የታቀደ ይመስላል። ከመድረኩ በስተግራ በክብ ቅርፅ ተፈልፍሎ የተሰራ የእንጨት ጌጥ በድጋፍ ቆሟል። ጌጡ በነጭ ቀለም ተዥጎርጎሯል። በኋላ ላይ የአካባቢው ባለውቃቢ የሚያተኩርበት ምስል ነው። መድረኩ መሀል ላይ ደግሞ ከእንጨት ተፈልፍሎ የተሰራ ባለረዥም መደገፊያ ወንበር ተሰድሯል። የድራማው ደራሲ ኬኒያዊው ክሪስፒን ሙዋኪዲዮ ትዕይንቱን ለምን ከደቡብ አፍሪቃ በተገኘ የሕዝብ መዝሙር መጀመር እንደፈለገ በዚህ መልኩ ይገልፃል።

«መዝሙሩን ዝም ብዬ አይደለም የመረጥኩት። በመጀመሪያ ደረጃ የመዝሙሩ ዓላማ ሰዉ ጉባኤው ላይ በንግግር ብቻ ሊሰላች ስለሚችል እንዲነቃቃ ለማድረግ ነው። በመዝሙሩ ደግሞ ተውኔታችንን በቀላሉ ሊያስታውሰው ይችላል። እንደነዚህ አይነት መዝሙሮች በቀላሉ ከአዕምሮ የሚወጡ አይደሉም። ይህ በራሱ በተውኔቱ ውስጥ ሙዚቃ ለመጠቀሜ ሌላኛው ምክንያት ነው።»

ክሪስፒን አያይዞም ይህ የዚምባብዌ ሕዝባዊ መዝሙር ወንዶች ወደ ጦርነት ሲሄዱ ድል አድርገው በሠላም እንዲመለሱ ሴቶች ምኞታቸውን የሚገልፁበት ነው ብሏል። በተውኔቱ ውስጥ ከተሳተፉት ተዋንያን ከሁለቱ በስተቀር ሌሎቹ በአጠቃላይ መድረክ የመጀመሪያቸው በመሆኑ እንዲበረታቱ ለማድረግም እንደተጠቀመበት አክሏል። ተዋንያኑ ቀደም ሲል ያደመጥነውን ሕዝባዊ መዝሙር እየዘመሩ እና ከመሀከላቸው አንዱ ከበሮ እየደለቀ ወደ መድረኩ ብቅ ሲሉ ታዳሚያኑ በአግራሞት መመልከታቸውን ቀጠሉ። እናም አምስቱ ጋዜጠኛ ተዋንያን ወደ መድረኩ ተጠግተው «የበማድመጥ ድራማ የካሬምቦ ህልምን ያቀርብላችኋል፤ እንኳን ደህና መጣችሁ!» ሲሉ ታዳሚው በጭብጨባ ነበር የተቀበሏቸው።

Learning by Ear Workshop GMF 2012

አባትየው

ድምፅ ጭብጨባ፥

ካሬምቦ እና ወላጆቿ ወለሉ ላይ ግራ እና ቀኝ ተጋድመዋል። ካሬምቦ ቀድማ ድንገት ከእንቅልፏ ትነቃና ወደ አባቷ ትጠጋለች። እናም ፈራ ተባ እያለች «አባዬ ለምንድን ነው ትምህርቴን እንድቀጥል የማታደርገኝ?» ስትል አባቷ አቶ ዳሩን ትጠይቃቸዋለች። አባትየው ከእንቅልፋቸው በመባነናቸው ተናደው «አንቺ ልጅ! በቂ ትምህርት አግኝተሻል። አሁን እንደውም እናትሽን መርዳት ነው ያለብሽ፤ በይ ወደ እንቅልፍሽ ተመለሺ» ሲሉ ይቆጧታል። ቁጣቸውን ተከትሎ ህፃን ልጃቸው ማልቀስ ይጀምራል። እናት ወ/ሮ ሊፒ ህፃኑን ሲያባብሉ አቶ ዱሩ ፊታቸውን በኬሻ ባርኔጣ ሸፍነው ተመልሰው በመተኛት ማንኮራፋት ይጀምራሉ። እናትየው ህፃኑን እያባበሉ ነው።

Hygiene LBE

ከአፍታ በኋላ ከበሮው በድንገት እና በፍጥነት መደለቅ ሲጀምር ህፃኑ ማልቀሱን ይቀጥላል፤ እናት፣ አባት እና ካሬምቦ ከመኝታቸው ተነስተው ይቆማሉ። ካሬምቦ አስተማሪዎቼ የመከሩኝ ህፃን ልጅ ሲታመም ወደ ሐኪም ቤት በፍጥነት መውሰድ እንዳለብን ነው፤ ስለዚህ ህፃኑን ሐኪም ዘንድ ማቅረብ ይኖርብናል ስትል እናቷን ትማፀናለች። አባትየው ልጃቸው ምክር ልትለግሳቸው መጣሯን «ልጅ ለእናቷ ምጥ አስተማረች» ከሚለው ብሂል ጋር ያዛመዱት ይመስላል። እናም አሁን በቁጣ ተውጠው ሆስፒታሉ ሩቅ መሆኑን በመግለፅ እንደውም ህፃኑን አዲስ ወደ መጡት ባለውቃቢ መውሰድ እንዳለባቸው አስረግጠው ይናገራሉ። ልጅ አሁንም አስተማሪያችን ያሉን ማለቷን ቀጥላለች። አባት የበለጠ ይናደዳሉ። እናም ወደ መድረኩ ግራ እና ቀኝ በፍጥነት እየተመላለሱ «በቃሽ! አስተማሪዬ ይህን አለ፣ አስተማሪዬ ያን አለ፤ ሴትዮ ተነሽ ወደ ባለውቃቢው ዘንድ እንሂድ» ይላሉ። የተውኔቱ ደራሲ እና ተባባሪ አዘጋጅ ኬኒያዊው ክሪስፒን ሙዋኪዲዮ ተውኔቱ በመክፈቻው ላይ ከሰማነው መዝሙር ባሻገር ሌሎች ባህላዊ አላባዎችን አካቷል ይለናል።

«በድራማው ውስጥ ሌሎች በርካታ ባህላዊ አላባዎች አሉ። ለምሳሌ አፍሪቃዊ ቤተሰብን ብንመለከት አብዛኛውን ጊዜ ባል እውጪ ውሎ አስፈላጊ ነገር አቅራቢ፤ ሚስት ደግሞ ዝም ብላ ቤት ተንከባካቢ ተደርጋ ነው የምትታየው። ይህ የተለመደ አፍሪቃዊ ባህል ነው። ሌላ ደግሞ አባትየው ሴት ልጁ ከትምህርት ቤት ቀርታ ቤት ውስጥ እንድትወሰን የመፈለጉ ሁኔታ አለ። ይህ በእርግጥ እየተቀየረ ቢሆንም በአብዛኛው የአፍሪቃ ገጠሮች አሁንም ድረስ ያለ ነገር ነው። የባለውቃቢው ሁኔታንም መመልከት ይቻላል። ደሀዎች አረ እንደውም ሀብታሞች ጭምር ከሳይንስ እና ዘመናዊ ህክምና ይልቅ በባለውቃቢ እና በጥንቆላ የማመን ሁኔታ ይታይባቸዋል።»

በእርግጥም የካሬምቦ ወላጆች የታመመ ህፃን ልጃቸውን ይዘው ወደ ባለውቃቢው ቤት ሲያመሩ ይታያል። በከበሮው ምት መሀል ባለውቃቢው ከእንጨት ተፈልፍሎ የተሰራው ዥንጉርጉር ጌጥ ላይ አተኩሮ ግራ በሚያጋባ ቋንቋ ማውራት ይጀምራል። የባለውቃቢው አንድ አይን ዙሪያውን ነጭ ቀለም ተቀብቷል፤ ከምንጭሩ በላይ እና ከለምቦጩ በታች የሚገኘው የአፉ ዙሪያ እንዲሁም ግራ እና ቀኝ ክንዶቹ ነጭ ቀለም ተሰምሮባቸዋል። «እኔ ሚዛንጃ ነኝ! የማላም ሰባተኛው ትውልድ!» በማለት መናገሩን ይቀጥላል።

Learning by Ear Workshop GMF 2012

ተዋንያኑ

ከመድረኩ በስተግራ በድጋፍ የቆመችው ክብ የእንጨት ፍልፍል፣ ዥንጉርጉር ምስልን ዙሪያዋን እየተሽከረከረ ነው የሚያወራው። ባለቀይ እና ጥቁር ቀለም ሽርጥ አገልድሟል። በእጁ ጭራ ቢጤም ይዟል። በየመሀከሉ ይህንኑ ጭራ ሄድ መለስ እያለ ክቧ እንጨት ላይ ነስነስ ያደርጋል። ለካሬምቦ ወላጆች ጀርባውን እንደሰጠ «ሁለት ሰዎች ይታዩኛል እንደውም ህፃን ልጅ ይዘዋል» ይላል። በእርግጥ የካሬምቦ ወላጆችን ቀደም ብሎ ቢያያቸውም ሳይመለከታቸው እንደተገለፀለት አድርጎ ነው ለማስመሰል የሞከረው። አባትዬው ጉሮሮዋቸውን ስለው በመሽቆጥቆጥ «ታላቁ ሚዛንጃ» ሲሉ አጎንብሰው ይጣራሉ። ሚዛንጃ «ባለህበት ቁም! የማም ግዛት ውስጥ ጥልቅ አትበል። አንዲት ጋት ፈቅ ትልና ወደ አሳማነት ነው የምቀይርህ!» ሲል ያስፈራራዋል።

አባትየው አሁንም አቀርቅረው «ታላቁ ሚዛንጃ ልጃችን ለምን የሆድ ቁርጠት እንደያዘው ሊነግሩን ይችላሉ?» ሲሉ ይጠይቃሉ። ባለውቃቢውም ልጃቸው የታመመው ወንድ ልጅ በመውለዳቸው ጎረቤታቸው ቅናት ስለያዘው እንደሆነ ይጠቅሳል። እናት በአካባቢያቸው ማንም እንደማይኖር፤ የቅርብ ጎረቤቴ የሚሉት ሰው እንኳን የሚገኘው ከኮረብታዎቹ ባሻገር 50 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ እንደሆነ እና ግራ እንደተጋቡ ሳይሸሽጉ ግን ፈራ ተባ እያሉ ይገልፃሉ። በዚህ ጊዜ ባለውቃቢው ሚዛንጃ ታዳሚውን ሳቅ በሳቅ ያደረገ ያልተጠበቀ ጥያቄ ያቀርባል። «ለመሆኑ ስለ ጎግል አርዝ ሰምታችኋል?» ሲል። ነገርየው በአሁኑ ጊዜ ምንም ያህል ሰዉ በርቀት ተለያይቶ ቢኖርም በኢንተርኔት በቀላሉ መገናኘት ይችላል፤ ጎረቤታችሁም ኢንተርኔት ውስጥ በጎግል አርዝ አይቷችሁ ልጃችሁን በቡዳ ስለበላው ነው የታመመው አይነት ነው ሀሳቡ። እዚህ ላይ ተውኔቱ አፍሪቃ ውስጥ ጎጂ ልማዶችና እምነቶች ኅብረተሰቡን ምን ያህል እየጎዱት እንደሆነ ለማሳያነት የተጠቀመበት ነው። በእርግጥም የበማድመጥ መማር የሬዲዮ ድራምን ለማስተዋወቅ የቀረበው ይህ የመድረክ ተውኔት ምን ያህል ጎጂ ልማዶች እና እምነቶች ከሰሀራ በታች በሚገኙ ሀገራት ተመሳሳይነት እንዳላቸው ጠቋሚ ነው። ክሪስፒን ይቀጥላል።

«ልክ እንደሌላው የጥበብ ዘርፍ ሁሉ ተውኔትም የተለያዩ ማኅበረሰቦችን ለማገናኘት ታላቅ ሚና ይጫወታል። እንደ ጭፈራ፣ ሽለላ፣ ቀረርቶ፣ ዘፈን የመሳሰሉትን የተውኔት አላባዎች ማየት ይቻላል። በእርግጥ ተውኔት አፍሪቃ ውስጥ ያን ያህል በተገቢው ሁኔታ ጥቅም ላይ አልዋለም። ሆኖም የተለያዩ ማኅበረሰቦችን በማገናኘት ከፍተኛ አቅም ነው ያለው። ለአብነት ያህል አሁን በናይጀሪያ አለያም በደቡብ አፍሪቃ ሀገራት የሚሰሩ ፊልሞችን ብንወስድ በርካታ ተዋንያን ፊልም ውስጥ ለመሳተፍ ከአንዱ ሐገር ወደሌላው ሲሻገሩ ይታያል። ይህ ራሱ የተውኔትን ዕምቅ ሀይል ያሳያል።»

ይህ የበማድመጥ መማር የሬዲዮ ድራማን በዶቼ ቬሌ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ላይ ለማስተዋወቅ የቀረበው ተውኔት የተፃፈውም ሆነ የቀረበው በእንግሊዘኛ ቋንቋ ነው። በማድመጥ መማር የሬዲዮ ድራማም እንደዛው በመጀመሪያ የሚፃፈው በእንግሊዘኛ ሲሆን በኋላ ላይ ወደ አምስት የተለያዩ ቋንቋዎች ይተረጎማል። ቋንቋዎቹም አማርኛ፣ሃውሳ፣ኪስዋሂሊ፣ፈረንሳይኛናፓርቱጋልኛ ናቸው። የበማድመጥ መማር መርሀ ግብር ትምህርት ለአፍሪቃእድገትቁልፍሚናእንዳለው በማመን ኅብረተሰቡን እያዝናና ማስተማርን ዓላማው አድርጎ የተነሳ ነው። በማዳመጥመማር በሁሉምየአህጉሪቱክፍሎችእውቀትንለማዳረስይጥራል። ልክ በመድረክ ተውኔቱ እንደታየው መልዕክት ማለት ነው። «የካሬምቦ ህልም» የተሰኘው የመድረክ ተውኔት ንፅህና አጠባበቅ እና ያለአቻ ጋብቻን አብይ ጭብጡ አድርጎ በመነሳት ውቃቢ፣ ቡዳ የመሳሰሉትን ጎጂ ባህሎችንም ለመነካካት ሞክሯል።

የካሬምቦ ወላጆች ባለውቃቢው ምንም የማያውቅ መሆኑ የገባቸው በኋላ ላይ እንደሆነ በመጥቀስ ይሳሳቃሉ። ልጃችሁ እንዲድን ሶስት እግር ያለው እባብ፣ ነጥፌያለሁ ወተት አልሰጥም የምትል ላም እና ከሰሀራ በረሃ በረዶ አምጡ ብሎ እንዴት ሊያጃጅለን ይሞክራል ሲሉ ሳቃቸውን ይቀጥላሉ። ካሬምቦ በትምህርት ቤት የተማረችውን ለማብራራት ትሞክራለች። ወላጆቿ ጀመራት እንግዲህ ሲሉ በመሰላቸት ፊት ይነሷታል። ግን ካሬምቦ ከትምህርት ቤት የተማረችውን ማስረዳቷን ትቀጥላለች። ህፃኑ ወንድሜ የታመመው ባልታጠበ እጅ ስንነካው ባክቴሪያ እና ጀርሞች ወደ ሆዱ ገብተው ነው ትላቸዋለች። አባት እንግዲያውስ ማንም ሰው ቢሆን ልጄን ከእንግዲህ እጁን ሳይታጠብ እንዳይነካ ሲሉ በማስጠንቀቅ ጎመን በጤና ከእንግዲህ ባክቴሪያ አልፈልግም ሲሉ ይሄዳሉ። ከአፍታ በኃላ ግን ከአንድ ባለፀጋ ጋር በስካር መንፈስ ተውጠው እየተወዛወዙ ወደ ጎጆው ይገባሉ።

Learning by Ear Workshop GMF 2012

የካሬምቦ አባት እና ወዳጃቸው

ባል በስካር መንፈስ እንደተዋጡ ወዳጃቸውን ይዘው ወደ ቤት ሲገቡ የታመመ ህፃን ልጃቸውን የሚያባብሉት እናት ባልየው ድምፃቸውን እንዲቀንሱ ይጠይቃሉ። በጣም ወሳኝ ሰው ይዤ መጥቻለሁ፣ አታፍጪብኝ ሂጂና ምግብ አምጪ ሲሉ ይጮሃሉ። እናትየው ገንዘብ እንዳልተሰጣቸው በመጥቀስ ያማርራሉ። እንግዳው ገንዘብ ችግር ሊሆን አይችልም፤ ችግር ሴቶች ናቸው ሲሉ ይሳለቃሉ። በማከልም ካሬምቦን ለማግባት ለባለቤትዎ ገንዘብ ሰጥቼዋለሁ ሲሉ እየተንተባተቡ ለማብራራት ይሞክራሉ። እናት ይናደዳሉ፤ ከትምህርት ቤት በጥሩ ውጤት በማለፏ ደስ ብሏት የመጣችው ካሬምቦ የሰማችውን ነገር ማመን አቅቷት ትጮሃለች። እናት አባት እና ካሬምቦ ከእንቅልፋቸው ሲነቁ የሆነው ነገር ሁሉ ለካ ህልም ነበር። አባት ልጄ ትምህርቷን መቀጠል አለባት ብለው ቃል ሲገቡ «የካሬምቦ ህልም» የተሰኘው አጠር ያለ የመድረክ ተውኔትም ይፈጸማል።

ዶቼ ቬለ ባዘጋጀው ዓለም አቀፍ የሚዲያ ጉባኤ መድረክ ላይ «የካሬምቦ ህልም» በሚል የቀረበ አጭር የመድረክ ተውኔትን አስመልክተን ያቀረብንላችሁ ጥንቅር እዚህ ላይ ይጠናቀቃል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 28.06.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15NYU
 • ቀን 28.06.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15NYU