የመያዶች ሙግት ለከካባቢ ዓየር ጥበቃ | ዓለም | DW | 05.12.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የመያዶች ሙግት ለከካባቢ ዓየር ጥበቃ

በኪዮቶ ስምምነት መሰረት የበለፀጉ አገራት የሚለቁትን አደገኛ ጋዝ ለመቀነስ የዛሬ አስር ዓመት ግድም ቃል የገቡ ቢሆንም፤ በተግባር ግን አሁንም ድረስ አንዳች ጠብ ያለ ነገር የለም።በኢንዶኔዢያ በተያዘው ስብሰባ በርካታ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (መያዶች) መቆርቆራቸውን ለማሳየት በአንድነት መምከር ይዘዋል።

አደገኛ የከባቢ ዓየር ብክለት

አደገኛ የከባቢ ዓየር ብክለት

ስለዓለም ከባቢ ጥበቃ በርካቶች ብዙ ብለዋል፣ብዙ ተሠብስበዋል፣በተደጋጋሚም ዘምረዋል።ኢንዶኔዢያ ባሊ፤ ሰኞ ህዳር ሀያ ሶስት በተጀመረው በዚህ ጉባኤ መግቢያ በር ላይ ሁለት ደርዘን የሚሆኑ ወጣቶች ተሠብስበዋል።ለምሳ ረፍት በመሆኑም ባላቸው አጭር ጊዜ በስብሰባው ላይ ምን ምን ማንፀባረቅ እንዳለባቸው እየተወያዩ ነው።በርካታ መቅረፀ-ድምፆችና የቪዲዮ ካሜራዎችም ከፊት ለፊት ተደርድረዋል።ቶቢያስ ሙንሽማየር ጀርመንን ወክለው ከመጡት ሁለት የከባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች መካከል አንዱ ነው።መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ይላል ቶቢያስ፤የእያንዳንዱን አገር ተወካይ የሚያግባቡ፣አስፈላጊ መረጃ የሚያቀብሉ፣የሚያነቃቁና በአንድ ጉዳይ ላይ ሀሣብ የሚያፈልቁ፣ያንንም የሚተነትኑና የሚተረጉሙ ሀይላት ናቸው ማለት ይቻላል።

በጉባኤው ላይ የሚቀርቡ ውስብስብ ርዕሶችን በወረቀት ላይ ለመረዳት ይከብዳል።እናም የዓለም ከባቢ ጥበቃ ድርጅቶች ይህንን በተመለከተ እጅግ ተቀራርበው መስራት ነው ያለባቸው ሲል የገለፀው ደግሞ የስብሰባው ሌላኛው ተሳታፊ ብሪያን ቶምሶን ነው።መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በአንድ ላይ ለመስራት እንሞክራለን። አንድ ዐይነት ድምፅ እንዳለን ለማሳየትና በስብሰባው ላይም ተፅዕኖ ለማሳረፍ በዓለማችን ትልቁ የመያዶች ቅንጅት በሆነው በዚህ የከባቢ ዓየር ጥበቃ ቅንጅት ስር እንሰባሰባለን ብሏል ብሪያን።ሌላኛው ተሰብሳቢና የጀርመን ዋች ማኅበርን በመወከል የተገኘው ጀርመናዊ ክሪስፖፍ ባልስ ደግሞ ብቻችንን ምንም አንፈጥም ነው የሚለው።ኅብረተሰቡ በአንድነት ሆኖ ጫና ካልፈጠረ በስተቀር መያዶች ለብቻቸው ምንም የሚፈጥሩት ነገር የለም ብሏል።

ብዙዎች ከጉባኤው ብዙ እንደሚጠብቁ ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል።ሆኖም እ.ኤ.አ. በሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ሰባት ዓ.ም በተባበሩት መንግስታት የቀረበውን የኪዮቶ ስምምነትን በርካታ አገራት የተቀበሉት ቢሆንም፤ለተግባራዊነቱ ግን ቻይና ህንድና አሜሪካንን ጨምሮ ብዙዎች የናቴ መቀነት አደናቀፈኝ ሲሉ ታይተዋል።በተያያዘ ዜና ደግሞ እዚህ ጀርመን እ.ኤ.አ. እስከ ሁለት ሹህ ሀያ ዓ.ም ድረስ የካርቦንዳይ ኦክሳይድ መርዘኛ ጋዝን አርባ በመቶ ለመቀነስ የሚያስችል አዲስ የሀይልና የከባቢ ዓየር ጥበቃ መርሀ-ግብርን ለማስፈፀም የፌዴራሉ መንግስት ሶስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዩሮ መመደቡም ታውቓል።