1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
እምነትኢትዮጵያ

የመውሊድ በዓል በሐረር ከተማ

ረቡዕ፣ መስከረም 16 2016

1498ኛው የመውሊድ በዓል በኢትዮጵያ ዛሬ እየተከበረ ይገኛል ። በሐረር ከተማ ከዋዜማው ከትናንት ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት እየተከበረ ነው ። በበዓሉ የታደሙ የሐረር ከተማ ነዋሪ የእስልምና እምነት ተከታዮች መውሊድን የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ፣ በመተጋገዝ እና በመደጋገፍ ማክበር እንደሚገባ ገለጹ ።

https://p.dw.com/p/4WrQK
1498ኛዉ የመዉሊድ በአል ሐረር ዉስጥ በድምቀት ተከብሯል
የመዉልድ በዓል አከባበር በሐረር ከተማ በከፊልምስል Mesay Tekelu/DW

ምእመናን ድሐ ሐብታም ሳይሉ በጎሳ ሳይከፋፈሉ እያከበሩ መሆኑን ተናግረዋል

1498ኛው የመውሊድ በዓል በኢትዮጵያ ዛሬ እየተከበረ ይገኛል ። የበዓሉ ታዳሚ ከነበሩት መካከል አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ቢኒር መሀመድ በዓሉን በየዓመቱ ደስ በሚል ሁኔታ ያለ ልዩነት እያከበሩት መሆኑን ተናግረዋል ። የሀረር ከተማ ነዋሪው እና የበዓሉ ታዳሚ የሆኑት አቶ ኢብራሂም ናጂ በበኩላቸው የመውሊድ በዓል የደስታ ቀን ፣ ነብዩ የተወለዱበት ቀን  መሆኑን ገልፀው በዓሉ በአብሮነት እና በፍቅር ለማክበር ዋነኛ መሰረቱ ይኸው መሆኑን ተናግረዋል ። ምእመናኑ ድሐ ሐብታም ሳይል በጎሳ እና በሌሎች ጉዳዮች ሳይከፋፈሉ እያከበሩት መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል ።

ወጣት መሱዲን ኢብራሂም በዓሉን በደስታ እያከበሩ መሆናቸውን ገልፆ በዓሉን በስርዓት በሰከነ ሁኔታ በሰላም ማክበር አለብን ብሏል። ሌላኛው ወጣት ኢብራሂም ሰብሪ የመውሊድ በዓልን አስመልክተው ወላጅ የሌላቸውን ልጆች ለትምህርት የሚያስፈልጋቸውን ቁሳቁስ አስባስበው ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጧል።

የሐረር ከተማ ታዳጊዎች የመዉሊድ በዓልን ሲያከብሩ
የመዉሊድ በአል በሚከበርበት በዓል ልጆችም ተካፋዮች ናቸዉምስል Mesay Tekelu/DW

እንደ ሌሎች በዓላት ሁሉ መውሊድን የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ፣ በመተጋገዝ እና በመደጋገፍ ማክበር እንደሚገባ በሀረርበተከበረው በዓል የታደሙ የእስልምና እምነት ተከታዮች ገልፀዋል።

በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ ከሚከበሩ በዓላት አንዱ የሆነው የመውሊድ በዓል በምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ይከበራል።

ሀረሪዎች ግን በተለየ መልኩ በኢድ አልፈጥር ሳምንት እንደሚያከብሩት የሸዋል ዒድ ሁሉ በጉጉት እና በናፍቆት ጠብቀው የሚያከብሩት በዓል መሆኑን የበዓሉ ታዳሚዎች ገልፀዋል። 

አቶ መሀመድ ኢብራሂም የተባሉ አስተያየት ሰጭ "መውሊድ ሀረር ላይ ሲከበር እንደሚለየው ሁሉ ህዝቡም ለነብዩ ያለው ፍቅር ይለያል" ሲሉ ተናግረዋል ። ወጣት እክብራሂም ሰብሪ በበኩሉ በሀረር ከተማ "በሸዋበር አስማዲን በሪ አካባቢ የነብዩ የልደታቸውን ቀን በድምቀት እያከበርን ነው" ብሏል። 

መሳይ ተክሉ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ-እግዚአብሔር