የመካከለኛዉ ምስራቅ-የሰላም ድርድር | ዓለም | DW | 06.09.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የመካከለኛዉ ምስራቅ-የሰላም ድርድር

የ1993ቱ የኦስሎዉ ስምምነት-የካፕ ዴቪድ ድርድድር የዌይ ሪቨር ስምምነት፥ የታባ ጉባኤ፥ የኤሎን የሰላም እቅድ፥ የኖይሲባሕ-አይሎን ስምምነት፥ የአረብ የሰላም ሐሳብ፥ የሠላም ካርታ እያለ-አስራ ስድስት አይነት ድርድር ተደርጎበታል

default

ለሰላም ጥረት ኖቤል

06 09 10

እንደ ሥልጣኔ-እዉቀት ብልሐቱ ሑሉ ሥይጣኔ-ማይምነትና ድንቁርናም ተለይቶት አያዉቅም።እንደ ፅድቅ-ሐይማኖት ሥብከቱ ሁሉ-እኩይ አረመኒያዊነት ተፈፅምቦታል-ይፈፀምበታልም።በግጭት-ጦርነት የመዉደም-ነዋሪዎቹ የማለቃቸዉን ያሕል ሠላም ሠፍኖበት ሰዎች ሰርተዉ-በልፅገዉበታል። መካከለኛዉ ምሥራቅ።ዘንድሮም እንደ ዘመነ-ዘመናቱ ሁሉ ቦምብ ጥይት እየዘነበ፥ ነዋሪዎቹ እየተገደሉ፥ እንደተጋዙ፥ እንደታገቱ ሥለ ሠላሙ ይጣር-ይነገርለት ይዟል።ባለፈዉ ሐሙስ ዋሽግተን ዉስጥ የተጀመረዉ የፊት ለፊት ድርድር መነሻ፥ ከቅርብ ዘመናቱ አያሌ የሠላም ጥረቶች ጥቂቶቹ ማጣቀሻ፥የቀዳሚ-አሁኖቹ ተሰናስሎ መድረሻችን ነዉ-ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

በሐያሉ አለም የሚዘወረዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዩናይትድ ስቴትስና በብሪታንያ ግፊት 1947 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) መንግሥተ-እስራኤል እንዲመሠረት መወሰኑ አስወሳኞቹ ከያኔ-እስካሁን እንደሚሉት የዚያን አካባቢ ሕዝብ በጣሙን የአይሁዶችን ሥቃይ ሰቆቃ ለማስወገድ ነዉ።አይደለም ብሎ የተከራከረ ለመከራከር የደፈረና የሚደፍር ሌላ ወገን በርግጥ አልነበረም።የለምም።እራሱ ያ! ምድር ግን ሰዉ-ሰዉነቱን ካወቀበት ዘመን-ጀምሮ ከተጓዘበት ጎዳና ሊቀይር-ሊቀየርም ያለ-መፈለጉ ሐቅ መድመቁ ነዉ ዚቁ።

የሰላም-እና የጦርነት፥ የእልቂትና የድሕነት፥ የሰብቅ-ሸፍጥ ክሕደት እና የእዉነት-ርትዕት፥ የብልፅግና እና የድሕነት የተቃርኖ ጉዞ።የሰዎችን ሥቃይ-ሠቆቃ ለማስወገድ፥ ሠላምን ለማስፈን የተባለለት ዉሳኔ ከኒዮርክ በተሰማበት-በደቂቃ-አስከሬን ይታጨድበት፥ ጦርነት ይንጠዉ ያዘ።-1947።

አመቱ-የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእስራኤል መንግሥት እንዲመሠረት መወሰኑ-ሲነሳ፥የአረብ እስራኤሎች የመጀመሪያዉ ይፋ ጦርነት ሲወሳ፥ ፎልከ ቤርናንዶተን አለማንሳት-በርግጥ ስሕተት ነዉ።ሲዊድናዊዉ ዲፕሎማት ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት እንደተጀመረ የናትሴ ጀርመን እስር ቤት የታጎሩ 31 ሺሕ እስረኞቹ እንዲለቀቁ ከወቅቱ የጀርመን ባለሥልጣናት ጋር የተደራደሩ እዉቅ ሸምጋይ ነበሩ።ቤርናንዶተ ካስለቀቋቸዉ እስረኞች መካከል በርካታ አይሁዶች ነበሩበት።

የቤርናንዶተን የመሸምገል-ብቃትና ብልጠት የሚያዉቀዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዲፕሎማቱ አረብ-እስራኤሎችን እንዲሸመግሉ በዉጤቱም ሠላም በማያዉቀዉ ምድር ሠላም እንዲያሰፍኑ ወደ አካባቢዉ ላካቸዉ።እንደ ጦርነቱ ሁሉ የሠላም ድርድር-ዲፕሊማሲዉም ቀጠለ።ወደያዉ ግን የአረብ አይሁድ ደም ያጨቀየዉ የእየራሳሌም ምድር-የቤርናዶተን ደምም ጠጣ-።ፅዮናዊያን አይሁዶች ሠላም ለማዉረድ ደፋ ቀና ሲሉ የነበሩትን ሲዊድናዊ ዲፕሎማት ገደሏቸዉ።የአዲሱ ዘመን የመጀመሪያዉ አለም አቀፍ የሠላም ሙከራ-የመጀመሪያ ምዕራፍም ሞተ።1948
ያ ምድር እንደ ጥንት-ጠዋቱ ጦርነት-ሠላም፥ የሠላም ጥረት የጦርነት ዝግጅት እንተፈራረቁበት 1967 ደርሶ ሌላ ጦርነት ሲያወድም-ሲያደቀዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ሌላ የሠላም ጥረት ጀመረ።እና ከሸፈ።አመት ሔዶ አመት ሲመጣ፥ ጦርነት እየተጀመረ አስከሬን እየታጨደበት፥ሠላም ይነገር ይዘመርለትም ነበር።በ1970ዎቹ መጀመሪያ ግብፅና የእስራኤል ካደረጉት ሥምምነት ዉጪ ግን ገቢር የሆነበት ሠላም የለም።

Flash-Galerie Historische Nahostgespräche 2000 Camp David

ካምፕ ዴቪድ

በየግጭት ጦርነት እልቂቱ መሐል ፍልስጤሞችን እና እስራኤሎችን ለማስታረቅ የሚደረገዉ ጥረት ተጨባጭ ከመሰለ ዉጤት የደረሰዉ ደግሞ በ1993 ኦስሎ ላይ የተደረገዉ ሥምምነት ነበር።እንዲሕ እንደ ዘንድሮዉ ያኔም መስከረም ነበር።አስራ-ሰወስተኛዉ ቀን 1993።

ፍልስጤምና እስራኤሎች ሥለ ድርድር ያደረጉትን ድርድር የሸመገለች፥ለመደራደር ሥምምነት ያበቃችዉም በ1947 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የእስራኤል መንግሥት እንዲመሠረት ያሳለፈዉን ዉሳኔ እንዲወስን አበክራ የተሟገተችዉ ሐያል ሐገር ነበረች-ዩናይትድ ስቴትስ።የኦስሎዉ ዉልም ለያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ለቢል ክሊንተን የታሪክ ድራማ በማይለየዉ ምድር አዲስ ክስተት ነበር።

Sympolbild Nahostkonferenz Annapolis mit Iran Flagge

አናፖሊስ

ዘመን-የማይሽርነዉን ጦርነት እንደ ወታደር የተዋጉ፥ እንደ ጄኔራል ያዋጉት፥ እንደ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የመሩ-ያዘዙት የያኔዉ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ይትሳቅ ራቢን የሠላም ስምምነቱን ሲፈርሙ እንደመሰከሩት ለዚያ ምድር የታላቅ ተስፋም-የጥርጣሬ ምልክትም ነበር።እንደ እንደዚያ ምድር የዘመነ-ዘመናት እዉነት የተቃርኖ ቅይጥ።

ጦርነቱን በሌለኛዉ አንፃር እንደ ደፈጣተዋጊ ለተፋለሙት፥ እንደ ደፈጣ ተዋጊዎች መሪ-ላዋጉት፥ እንደ ፖለቲከኛ ለመሩት ለፍልስጤም ነፃ አዉጪ ድርጅት ሊቀመንበር ለያሲር አረፋትም የኦስሎ ስምምነት የአዲስ ምዕራፍ-ጅምር ነበር።አዲሱ ምዕራፍ ግን የሕዝቦች ሥቃይ ሰቆቃ-የሚያበቃበት ሠላም የሚሰፍንበት እንዲሆን አረፋት ያኔ እንዳሉ ድፍን አለም ሊተባበር ይገባዉ ነበር።
በአረፋት ቋንቋ-ሠላም ካልሰፈነበት በአለምም ሠላም የማይሰፍንበት ያ-ምድር፥ ለአይሁድ፥ ለክርስቲያን፥ ለሙስሊሞች የብርሐን ቀንዲል ተምሳሌዉ-ያ-ምድር በርግጥም ሻሎም-ሠላም ይነገር-ይዘመርበት ገባ።
የሠላም-ንግግር-መዝመሩ በቅጡ ተነግሮ-ተደምጦ ስይገባደድ ሥለ ሠላም ተናጋሪ-አናጋሪዉ፥ የሠላም መዝሙር ግንባር ቀደም-ዘማሪ-አስዘማሪዉ ልሳን ተዘጋ።ቃታ-ሲስቡ፥ ሲያስቡ የኖሩት ጣቶች-የሠላም ዉል በፈረሙ ማግስት ደረቁ።የጦርነቱም-የሰላሙም ጀግና-ይትሳቅ ራቢን ተገደሉ።ገዳይ-ፅንፈኛ አይሁዳዊ ተማሪ።ክሊንተንም «ጉድባይ» ወዳጄ ከማለት ሌላ የሚሉት አልነበረም።

የራቢን መገደል-ፈር የቀደደላቸዉ ቤንያሚን ኔትንያሁ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን ሲይዙ ብዙ የተለፋ፥ ብዙ የተደከመ ብዙ የተነገረለት የሠላም ድርድር ሥምምነትም-«ሻሎም-ጉድባይ ወይም አዲዮስ»።አረፋትና ክሊንተን በነበሩበት-ነበሩ።ራቢን-ላይ መጡ ሔደዉ የመጡት ኔታንያሁ ግን እንደ ጠቅላይ ሚንስትር ጥቂት ተቀምጠዉ ሥለ ሰላም ድርድሩ የነበረዉን-ጅምር እንዳልነበር አድርገዉ ሔዱ።

ተረኛዉ ኤሁድ ባራክ ናቸዉ።የኦስሎ ስምምነት እንደገና አንሰራርቶ ከካምፕ ዴቪዱ ድርድር አደረሰ።2000።ለሠላም ፈላጊዎች ሌላ ተስፋ ነበር።ትልቅ ተስፋ።የድርድሩ ርዕስ ሒደትም ክሊንተን ያኔ እንዳሉት ጥልቅ ደግሞም አጓጊ ነበር።

ብቻ ለዉጤት አልበቃም።ለዉጤት አለመብቃቱ ባራክን ከስልጣን አስቀግዶ-አርያል ሻሮንን አስመረጠ። እንደ ገና ግጭት፥ እንደ ገና ግድያ፥እንደገና እገታ።አረፋት ከረመላሕ ፅሕፈት ቤታቸዉ እንደታገቱ የራቢንን መንገድ ተከተሉ።የክሊንተን ዘመነ-ሥልጣንም አበቃ።ሻሮን አረፋትን ባሳገቱ፥ የተናጥል ባሉት ዉሳኔ ጦራቸዉን ካጋዛ ባስወጡ በጥቂት አመት -ታመሙ።መሞት መዳናቸዉ እስከዛሬ አይታወቅም።ብቻ ሔዱ።

የ1993ቱ የኦስሎዉ ስምምነት-የካፕ ዴቪድ ድርድር የዌይ ሪቨር ስምምነት፥ የታባ ጉባኤ፥ የኤሎን የሰላም እቅድ፥ የኖይሲባሕ-አይሎን ስምምነት፥ የአረብ የሰላም ሐሳብ፥ የሠላም ካርታ እያለ-አስራ ስድስት አይነት ድርድር ተደርጎበታል።ጠብ ያለ ነገር የለም።ሁለት ሺሕ ሰባትም ሊያበቃ ጥቂት ቀረዉ።እና ያኔ ተረኞች-ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ፥ ጠቅላይ ሚንስትር ኤሁድ ኦልሜርት እና ሊቀመንበር ማሕሙድ አባስ ነበር።አስተናጋጅ ደግሞ አና ፖሊስ።አረጌ-ግን ሌላ የሠላም ተስፋ፥ የቸከ ግን-አዲስ የድርድር ቃል-።ታሕሳስ 2007።ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊ ቡሽ።

ፕሬዝዳት ቡሽ እንዳሉት፥ኦልሜርትና አባስ እንደፈረሙት ሥምምነት ከእስራኤል ጋር በመልካም ጉርብትና በሠላም እና በመቻቻል የሚኖር የፍልስጤሞች መንግሥት እስከ 2008 ማብቂያ መመስረት ነበረበት።አሁን-2010 ነዉ።ማሕሙድ አባስ በነበረቡት አሉ።ኤሁድ ኦልሜርት በሙስና ተከሰዉ ከፍርድ ቤት ፖሊስ ጣቢያ እየተመላለሱ ነዉ።ቤንያሚን ኔትንያሁ ተመልሰዉ መጥተዋል።

ዋይት ሐዉስ አሁን የፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ነዉ።የሙሴ አስተምሕሮት-ላለፉት ሰወስት ሺሕ ዘመን የሚተረጎምበት፥ የክርስቶትስ ምግባር-ስብከት ለሁለት ሺሕ አስር አመታት የሚሰበክበት የመሐመድ ድርጊት ተልዕኮ-ከአንድ ሺሕ አራት መቶ አመት በላይ የሚዘከር-የሚወደስበት ያ-ምድር ሰዉዊዉ ቃል-ተስፋም ሲነገር-ሲደናገር፥ሲሰበክ-ሲቀጠፍ፥ ቃል-ሲገባ ሲታጠፍበት እነሆ ዘመነ- ዘመናት አስቆጠረ።

ተረኛ ግን ይንደገና ይናገር-ይሰብከዋል።ባራክ-ኦባማ እንደ አይዘናወር፥ እንደ ኒክሰን፥ እንደ ሬጋን፥ እንደ ክሊንተን-እንደ ጆርጅ ቡሽ ትልቁ-እንደ ጆርጅ ቡሽ ትንሹ-ሠላም ይጠቅማችኋል አሉ።ኔታንያሁም-ዳግም ለሁለተኛ ጊዜ እንደ ቤን ጎሪዮን፥ እንደ ጎልዳሚር፥ እንደ ሻሚር፥ እንደ ራቢን፥ እንደ ፔሬስ፥ እንደ ባራክ፥ እንደ ኦልሜርት ሁሉ «ለሠላም ዝግጁ ነኝ» ብለዉ መለሱ።ለኦባማ።ማሕሙድ አባስ-እንደ ናስር፥ እንደ ሳዳት፥ እንደ ሁሴይን፥ እንደ አረፋት ሁሉ-የሚሉት አሉ።

በክሊንተን ቋንቋ የዮርዳኖስ ወንዝን ከሜድትርን ባሕር ከፋዩ ትንሽ ምድር-በራቀዉ ዘመን ጥንት-ድሮም እንደዚያ ነበር።ዛሬም ከዋሽንግተን እንደሰማነዉ ነዉ።ነገስ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ።የነገ-ሰዉ ይበለን።

Nahost Friedensgespräche in Washington

ዋሽንግቶን

dw,Arichiv,Agenturen

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላAudios and videos on the topic