የመካከለኛዉ ምስራቅ ሰላም | ዓለም | DW | 31.08.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የመካከለኛዉ ምስራቅ ሰላም

ባራክ ኦባማ፤ ማሕሙድ አባስና ኔትንያሁም ፊት ለፊት ተገናኝተዉ ለመደራደር ለመስከረም ቀጠሮ አላቸዉ።ሰላም ያወርዱ-ይሆን ብሎ ጥያቄ ግን-ያዉ ገና ጥያቄ ነዉ

default

ኔታንያሁና ሜርክል

31 08 09
ኢራኖችን ከቃላት-ዉዝግብ፣ እስከ ሰልፍ-ቁርቁስ፤ ከግጭት-እስከ ሞት ያላጋዉ ምርጫ የቴሕራን ቤተ-መንግሥትን ከአክራሪዎቹ እጅ አፅንቶ፤ ለዘብተኞቹን ወሕኒ አስዱሎ ፍርድ ቤት ሲያሟግት-የግብፁ ፕሬዝዳት ሆስኒ ሙባረክ ዋሽግተን ገቡ።ሙባረክ ካይሮ በተመለሱ በሳምንቱ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔትንያሁ ለንደንና በርሊንን ጎበኙ።በመሐሉ ከቴሕራን እስከ ዶሐ፣ ከረመላሕ እስከየሩሳሌም፣ ከብራስልስ እስከ ኒዮርክ ብዙዎች ብዙ ብለዋል።የብዙዎቹ ብዙ ብሒል፣ የሁለቱ መሪዎች ተልዕኮ፣የየስተናጋጆቻቸዉ ፍላጎት-የፍልስጤም-እስራኤሎች ድርድር-አንድ፣የኢራን ኑክሌር ሁለት-የሚባል ግን አንድ ነዉ።የሁለቱ አንድነት ዳራ፣ ያሁን እንዴትነት፣ የብሒል፤ ተልዕኮ፣ ትኩረቱ ጥልቀት ያፍታ ቅኝታን ሰበብ ነዉ አብራችሁኝ ቆዩ።--------------

እርግጥ ነዉ-ሰዉ ሰዉነቱን ካወቀበት ጀምሮ ሰዉ ያልተለየዉ ያ ምድር በጎ-እየተዘራ-እኩይ የሚታጨድበት የወለፊንድ ጉዞ እንጂ ያንድ አቅጣጫ እርምጃ ኖሮት አያዉቅም።

የሃያ-አንደኛዉ ክፍለ ዘመን ሃያላን ደካሞችን-የማስገበር፤ የመዝረፍ፤ የመርገጡ፣ ሰብአዊ ፍጥሩን የመሸጥ መለወጡ፣ በዘር-የመታበይ፤ አናሳዎችን፣ የሌላ ሐይማኖት ተከታዮችን የማጥፋቱን-የዘመናት አኩይ ልምድን ለማስቆም አለምን ባንድ ማሕበር አደራጅተዉ «እርም» ሲያሰኙት-አዲሱ አስተሳሰብ ሕግ-ደንባቸዉ ከዚያ ምድር በፊት የሚሰርፅበት ሥፍራ ይኖራል ብሎ ማሰብ በርግጥ ከባድ ነበር።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔትንያሁ ባለፈዉ ሳምንት በርሊን ላይ እንዳሉት ግን የመካከለኛዉ ሥምራቅ የሰልሳ-ዘመን አዲስ ጉዞ ወደፊትም ከጥንቱም እስከዛሬዉ በባሳ እልቅት-ፍጅት ድባብ የታጀበ ነዉ።

«በቅርቡ ኢራን ዉስጥ በተደረገዉ ምርጫ ትክክለኛ ባሕሪዉ ገሐድ የወጣዉ የኢራን ሥርዓት የኑክሌር ጦር መሳሪያ ለመስራት ማቀዱ እስራኤልን፥ የሚያሰጋ፥ አካባቢዉን የሚያሰጋ፥ የአለምን ሠላም ላደጋ የሚያጋልጥ ነዉ።ይሕ እኔ እንደሚመስለኝ እኛን ሁላችንንም የሚያሳስብ ነዉ።እስራኤል ሐላፊነት ከሚሰማቸዉ የአለም አቀፉ ማሕበረሰብ አባላት በሙሉ ለዚሕ ሥጋት መወገድ ሁነኛ ምላሽ ትጠብቃለች።ጀርመን ለዚሕ ሥጋት መወገድ ሐላፊነት ባለዉ መንገድ አፃፋ እንደምትሰጥ ከመራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በመስማቴ ተደስቻለሁ።ብዙ ጊዜ (ግን) የለም።»

ከዘመናት እልቂት-ፍጅት ብዙ ተምረዉ- የልቂት-ፍጁትን ዑደት በዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ሰብረዉ፣ ከድንቁርና ጥፋት ብዙ አዉቀዉ-፣ድሕነት-ኋላ ቀርነትን ድል የነሱት ሐይላት፣ሁለት አስከፊ ተከታታይ ጦርነቶችን ባሸነፉ ማግስት ሥለዚያ ምድር የወሰኑት ዛሬ እና እስከ ዛሬ የሆነና የሚሆነዉ እንዲሚሆን አስበዉ ነበር-ማለት በርግጥ ያሳስታል።

በሃያላኑ ዉሳኔ በ1948 (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) እስራኤል መመስረቷ ለዘመናት የሰዉ ሥልጣኔ ትሩፋት በሥይጣኔዉ እኩይ-የሚጨቀይበት፣ የእዉቀት ብልሐቱ ፀጋ በድቁርናዉ የሚወሰክበት፣የሐይማኖቱ ሰናይ፣ በአረመኔ ግብሩ የሚረክስበት፣ርሕራሔዉ-በጭካኔዉ፣ ጀግንነቱ-በእብሪቱ፣ የሚጎድፍበት-ያ ምድር አዲሱ ዘመን የፈቀደዉን አዲስ እዉነት የመቀበሉ ምልክት በሆነ ነበር።

US-Präsident Barack Obama und der ägyptische Präsident Hosni Mubarak

ሙባረክና ኦባማ

የአዲሱ ዘመን አዲስ እዉነት-አሮጌዉን እኩይ ድርጊት፣ ካሮጌዉም ዘመን በከፋ ሥልት ለመድገም-ወራት አለመቆየቱ ነዉ ሰቀቀኑ።ባዲሱ ዘመን የነዳዊት፤ የነሰለሞን፤ የፈርኦኖች፤ የናቡከደናፁር፣ የነሙሴ፣ የነክርስቶስ፤ የነመሐመድ ጥበብ-ብልሐት፤ ትዕግስት-ደግነት የግልብጥ ተተርጉሞበት ያ-ምድር ሰላሳ-አመት ባልሞላ የአንድ ትዉልድ ገሚስ እድሜ አራት ትላልቅ፣ ብዙ ትናንሽ ጦርነቶችን ለማስተናገድ ተገድዷል።

ከዚያ በሕዋ በተቆጠረዉ ሰላሳ አመትም ብዙ የተለወጠ ነገር የለም።የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በቀደም እንዳሉት ግን የስልሳ-አመቱን የእልቂት ፍጅት ዑደት ለመቀየር አሁን ጥሩ ወቅት ነዉ።

«የሆነ (የሰላም) ሒደት ለመጀመር ወቅቱ በጣም፥ በጣም ጥሩ ነዉ የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ።አዲስ የእስራኤል መንግሥት፥ አዲስ የአሜሪካ ፕሬዝዳት (ሥልጣን የያዙበት) በአዉሮጳ ሕብረትና በዩናይትድ ስቴትስ መካካል ጠንካራ ትብብር ያለበት እና ለመርዳትና ለመተባበር እዉነተኛ ፍቃደኝነቱ የታየበት፥ ዉጤት የሚገኝበት ታሪካዊ ወቅት ነዉ።»

ማብቂያ ያጣዉ የሕዝብ እልቂት ፍጅት እስራኤልን የማትደፈር ሃያል-ግን ሁሌም በስጋት የምትባንን ሐገር-አድርጓል።የአረብ ብሔረተኞችን፤ የጦር መኮንኖችን፤ ነገስታት-አሚሮችን ከየአብያተ-መንግሥታቱ ዶሏል።መሳጂዶችን የፖለቲካ መድረክ፤ የሐይማኖት መሪዎችን ፖለቲካ ሰባኪ፣ ወጣቶችን አክራሪ-አሸባሪዎች አድርጓቸዋል።

የኢራን እስላማዊ አብዮተኞች በ1979 በሙስና የጋሸበዉን የንጉስ ፓሕሌቪን ዘዉዳዊ አገዛዝ አስወግደዉ የቴሕራንን ቤተ-መንግሥት የመቆጣጠራቸዉ ሰበብ’ የዚያ ምድር-የአዲስ ዘመን አሮጌ ድርጊት መሆኑን አለመቀበል-በርግጥ ሥሕተት ነዉ።

የቴሕራኑ አብዮት የመካከለኛዉ ምሥራቅን የሠላሳ ዘመን ሒደት ቀይሮታል። እስራኤል በጦር ሐይል የማትደፈር ግን ሥጋት ያልተለያት ሐገር እንደሆነች አልቀጠለችም።

የአረብ ገዢዎች ተቃዋሚዎቻቸዉን ሲሻቸዉ የአይሁድ ቅጥረኛ፣ ሲላቸዉ አሸባሪ እያሉ እያጠፉ፤ ሕዝባቸዉን እንደረገጡ፤ሐብቱን እንደመመዘበሩ እድሜ ልክ-ተንደላቀዉ ዙፋን፥ ወይም ዙፋን አከል መንበራቸዉን ለልጆቻዉ እያወረሱ ቢቀጥሉ-እንኳን የፋርስ-ሺዓች አብዮት ባነቃቃዉ ሐይል ሥልጣን-ዙፋናችንን እንቀማለን በሚል ሥጋት ይሸማቀቁ ገብተዋል።

የምዕራብ-ምሥራቅ ሐያላንም ሰላሳ ዘመን የዘለቁበትን የማደራደር-ማዋጋት ሥልት መቀየር ግድ ነበረባቸዉ።በ1978 ማብቂያ ሜናሕን ቤጌን፥ አንዋር አሳዳት እና ጂሚ ካርተር ካፕዴቪድ ላይ የሰላም ታሪክ የሰሩት-የኢራን እስላማዊ አብዮተኞች የቴሕራንን ቤተ-መንግሥትን ሲንኳኩ ነበር።

ዘንድሮ የኢራን የኑክሌር ቦምብ ትሰራለች የሚለዉ ጥርጣሬ ማየሉ፥የቴሕራንን አክራሪ ገዢዎች ለመተካት ለዘብተኛ ሐይላት ያደረጉት ሙከራ መክሸፉ፥ወይዘሮ አንጌላ ሜርክል የጠቀሷቸዉ ሐይላት የዛሬ ሰላሳ አመቱን ታሪክ እንዲደግሞ ምክንያት መሠረት ሳይሆናቸዉ አልቀረም።

ግን እንዴት ነዉ-ጥያቄዉ።የፕሬዝዳት ሁስኒ ሙባረክ መልስ የግድ የሚል አይነት ነዉ።
«ሁለቱን ወገኖች ለማገናኘት የምንችለዉን ሁሉ ማድረግ አለብን።ወደዱም ጠሉ (ለድርድር) መቀመጥ አለባቸዉ።መፍትሔ ማግኘትና ዑደቱን መስበር አለብን።በአሜሪካኞች፣ በግብፅና በሌሎች ሐገራት ድጋፍ ቁጭ ብለዉ በመደራደር አመለካከታቸዉን መቀየር አለባቸዉ።ከዚሕ ዉጪ ሌላ መንገድ የለም።»


እስካሁን በርግጥ የተጨበጠ ነገርም-የለም።ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ግን በትክክለኛዉ አቅጣጫ-እንቅስቃሴዉ ቀጥሏል ባይ ናቸዉ።

«ወደትክክለኛዉ አቅጣጫ የሚያጉዙ እንቅስቃሴዎች አሉ።እንቅስቃሴዉ የእስራኤል ብቻ አይሆንም የሚል ተስፋ አለኝ።»

ግብፅና እስራኤል የሰላም ዉል ለማዉረድ የወሰኑት መስከረም ነዉ።ዮርዳኖስና እስራኤል የሰላም ዉል የተፈረራሙት መስከረም ነዉ።ያሲር አረፋትና ይትሳቅ ራቢን የሰላም ዉል የፈረሙት መስከረም ነዉ።ባራክ ኦባማ፤ ማሕሙድ አባስና ኔትንያሁም ፊት ለፊት ተገናኝተዉ ለመደራደር ለመስከረም ቀጠሮ አላቸዉ።ሰላም ያወርዱ-ይሆን ብሎ ጥያቄ ግን-ያዉ ገና ጥያቄ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

dw,Agenturen

Negash Mohammed


Audios and videos on the topic