1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካየመካከለኛው ምሥራቅ

የመካከለኛዉ ምሥራቅ ጦርነት፣ የአሜሪካ ዲፕሎማሲና የየገንዘብ መዋጮ

ዓርብ፣ ጥቅምት 15 2017

የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ኃላፊዎች፣የጦር አዛዦች፣ዲፕሎማቶችም ወደ መካከለኛዉ ምሥራቅ ይጓዛሉ።ልዩነቱ ሰዎቹ እንደ ጦር መሳሪያዉ እዚያዉ አይቀሩም።ይመለሳሉ።ዓመት አለፈዉ።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊከን ብቻ አካባቢዉን ሲጎበኙ ያሁኑ አስራ አንደኛቸዉ ነዉ።አስሩ አልተሳካም ያሁኑስ?

https://p.dw.com/p/4mFMC
ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰሞኑን በመካከለኛዉ ምሥራቅ ባደረጉት ጉብኝት ጋዛንና ሊባኖስን የሚያወድመዉ ጦርነት እንዲቆም ጠይቀዋል
ከግራ ወደ ቀኝ የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊከንና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁምስል Haim Zach/Israel Gpo/ZUMA Press Wire//picture alliance

የመካከለኛዉ ምሥራቅ ጦርነት፣ የአሜሪካ ዲፕሎማሲና የየገንዘብ መዋጮ

የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊከን ጋዛና ሊባኖስ ዉስጥ የሚደረገዉ ጦርነት እንዲቆም ለማግባባት አዲስ ዲፕሎማሲ ጀምረዋል።ብሊንከን ከአምና መስከረም 26 ወዲሕ መካከለኛዉ ምሥራቅን ሲጎበኙ ያሁኑ 11ኛቸዉ ነዉ።ፈረንሳይ ደግሞ በእስራኤል ጥቃት ለተጎዳዉ የሊባኖስ ሕዝብ ርዳታ ለማሰባሰብ የጠራችዉ ጉባኤ ትናንት ፓሪስ ዉስጥ ተደርጓል።የጋዛና የሊባኖስ ዉድመት ግን እንደቀጠለ ነዉ።

የጦር መሳሪያ አቅርቦትና የሰላም ዲፕሎማሲ

ከድምፅ የፈጠነ ቦምብ ጣይ ጄት፣ምሽግ ሰርጓጅ ቦምብ፣ ተመሪ ሚሳዬል፣ከየትኛዉም ከፍታ ላይ ሚሳዬል ቀላቢ ፀረ-ሚሳዬል ሚሳዬልና ሌላም የዘመኑ ሰዉ የሰራዉ ጦር መሳሪያ ከአሜሪካ ወደ እስራኤል ይጋዛል።ዶላርም።ከምዕራብ አዉሮጳም።ቦምብ፣ ሚሳዬል ጥይቱ ጋዛና ሊባኖስ ላይ ይራገፋል።የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ኃላፊዎች፣ የጦር አዛዦች፣ዲፕሎማቶችም ወደ መካከለኛዉ ምሥራቅ ይጓዛሉ።ልዩነቱ ሰዎቹ እንደ ጦር መሳሪያዉ እዚያዉ አይቀሩም።ይመለሳሉ።ዓመት አለፈዉ።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊከን ብቻ አካባቢዉን ሲጎበኙ ያሁኑ አስራ አንደኛቸዉ ነዉ።
አብዛኛ ጉዟቸዉ ጦርነት እንዲቆም ለማግባባት ነዉ።አስሩ አልተሳካም ያሁኑስ?
 

«ከመስከረም 26 ጀምሮ እስራኤል ጋዛን በተመለከተ ሥልታዊ አላማዋን አሳክታለች።የሐማስን ወታደራዊ አቅም ሰብራለች።አብዛኛ ጦር መሳሪያዎቹን አጥፍታለች።በቅርቡ የተገደሉትን ያሕያ ሲንዋርን ጨምሮ አብዛኛ መሪዎቹን አስወግዳለች።ይሕ በብዙ የጋዛ ሰላማዊ ፍልስጤማዉያን ኪሳራ የተገኘ ድል ነዉ።»
ብሊንከን እንዳሉት እስራኤል በከፈተችዉ ጥቃት ከ42 ሺሕ በላይ ፍልስጤማዉያን አልቀዋል።ከመቶ ሺሕ በላይ ቆስለዋል።ያልተፈናቀለ የለም።ትንሺቱ፣ ጥንታዊቱ፣ ደሐይቱ  የባሕር ዳርቻ ሠርጥ ወድማለች።

የእስራኤል ጦር ባለፈዉ ሐሙስ በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ላይ ካደረሰዉ ድብደባ አንዱ
የአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስር የሰላም ጥረት በሚያደርጉበት የ70 ሐገራት ባለሥልጣናት ፓሪስ ዉስጥ ተኩስ እንዲቆም በሚጠይቁበት መሐል የእስራኤል ጦር በዘነዘረዉ ጥቃት ቤይሩት ትጋያለችምስል Hussein Malla/AP/picture alliance

የሞት፣ጥፋት ዉድመቱ ግዝፈት

እስራኤል፣ ዩናይትድ ስቴትስ የአዉሮጳ ሕብረት፣ ብሪታንያና ተባባሪዎቻቸዉ ባሸባሪነት የሚወነጅሉት ሐማስ መስከረም 26፣ 2016 ደቡባዊ እስራኤል ላይ በከፈተዉ ጥቃት ከ1100 በላይ ሰዉ ገድሏል።በመቶ የሚቆጠሩ አግቷል።ከታጋቾቹ 100 ያሕሉ አልተለቀቁም። አሁን ግን «በቃ» አሉ-ብሊንከን።
አሜሪካዊዉ ዲፕሎማት «ይብቃ» ያሉት ግን ለተረፉት ፍልስጤሞች ወይም ለሐብት ንብረታቸዉ ደሕንነት አይደለም።የእስራኤልን ድል ዘላቂነት ለማረጋገጥ-አንድ፣ ታጋቾችን ለማስለቀቅ-ሁለት እንጂ።

«እነዚሕን ድሎች  ወደ ዘላቂ ሥልታዊ ድል መቀየሪያዉ ጊዜ አሁን ነዉ።በእዉነቱ መሰራት ያለባቸዉ ሁለት ነገሮች ይቀራሉ።ታጋቾቹን ወደየቤታቸዉ መመለስና የሚከተለዉን በመረዳት ጦርነቱን ማቆም።»
ብሊንከን ይሕን ያሉት የእስራኤልን ጠቅላይ ሚንስትር ጨምሮ የሐገሪቱን  ባለሥልጣናት ካነጋገሩ በኋላ ነዉ።ሥለተኩስ አቁሙ  ከእስራኤል በኩል እስካሁን የተሰማ የለም።

 

የገንዘብ መዋጮና የተኮስ አቁም ዉትወታ

 

ብሊንከን ትናንት ከእስራኤል ሪያድ ደርሰዉ ዶሐ ሲገቡ፣ ፓሪስ ፈረንሳይ ዉስጥ የተሰበሰቡ የ70 ሐገራት ባለሥልጣናት ደግሞ ለሊባኖስ ሕዝብ መርጃ 1 ቢሊዮን ዶላር ለማዋጣት ቃል ገብተዋል።
የሊባኖስ ጠቅላይ ሚንስትር ነጂብ ሚካቲ እንዳሉት ግን ቀዳሚዉ ጉዳይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያፀደቀዉን ተኩስ አቁም ገቢር ማድረግ መሆን ነበረበት።
                          
«እኔ የምለዉ በተለይ ዛሬ ተኩስ እንዲቆም ስንጠይቅ መፍትሔዉ መጀመር ያለበት የዉሳኔ ቁጥር 1701ድን ተግባራዊ በማድረግ ነዉ።ዉድመት ይብቃ።ጦርነት ይብቃ።ደም ማፍሰስ ይብቃ።መጨረሻ ላይ የተመድ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉሳኔ ቁጥር 1701 ድ ገቢር መሆን አለበት ብለን እናምናለን።ተጨማሪ ጥፋትና ደም መፍሰስን ለመቀነስ ዛሬዉኑ ተግባራዊ መሆን አለበት።»
የዮርዳኖሱ ዉጢ ጉዳይ ሚንስትር አይማን ሳፋዲ «ዘር ማፅዳት» ያሉት የእስራኤል ጥቃት እንዲቆም ጠይቀዋል።ሁሉም ተኩስ እንዲቆም ይጠይቃል።በሊባኖሱ ጠቅላይ ሚንስትር አገላለፅ ደም አፍሳሽ፣አጥፊ፣ገዳዮቹ ግን ጥፋት ግድያዉን እንደቀጠሉ ነዉ።

የሊባኖሱ ሞግዚት ጠቅላይ ሚንስትር ነጂብ ሚካቴ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ምክር ቤት ዉሳኔ 1701 እንዲከበር ይጠይቃሉ
ከግራ ወደቀኝ የሊባኖስ ሞግዚት ጠቅላይ ሚንስትር ነጂብ ሚካቲና የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮ ፓሪስ-ፈረንሳ ዉስጥ ምስል Julien Mattia/Le Pictorium/MAXPPP/picture alliance

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ