የመኖሪያ ቤቶች ግንባታና የውጭ ኩባንያዎች | ኢትዮጵያ | DW | 22.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የመኖሪያ ቤቶች ግንባታና የውጭ ኩባንያዎች

በአዲስ አበባ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት የውጭ ኩባንያዎች ሊሳተፉ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግስት አስታወቀ። የውጭ ኩባንያዎቹ የሚሰሯቸው የመኖሪያ ቤቶች ከከተማዋ ነዋሪ የመክፈል አቅም በላይ ሊሆን የሚችልበት እድል መኖሩን የኢኮኖሚ ባለሙያ ተናግረዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰዎችን የመኖሪያ አካባቢዎችና ሁኔታዎች የሚከታተለው ዩ.ኤን. ሃቢታት የተሰኘው ተቋም (The United Nations Human Settlements Programme (UN–Habitat) የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ብዛት 4 ሚሊዮን እንደሚደርስ ይገምታል። በዚህ ተቋም ዘገባ መሰረት ከኢትዮጵያ የከተማ ነዋሪዎች 30 በመቶው በአዲስ አበባ ይኖራሉ።ይሁንና መንግስት እና የግል የግንባታ ኩባንያዎች የነዋሪዎቹን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማሟላትም አልቻሉም።

ችግሩን ለመቅረፍ የውጭ ሃገራት የግንባታ ኩባንያዎች ለማሳተፍ የኢትዮጵያ መንግስት ያወጣውን የጨረታ ሰነድ ከገዙ 77 ኩባንያዎች መካከል 28 ለቅድመ-ብቃት ምዘና መድረሳቸውን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት አቶ ዝናቡ ቱኖ ተናግረዋል።እንደ አቶ ዝናቡ ቱኖ ከሆነ «ከውጭ ሃገር የሚመጡ ኩባንያዎች ከሃገራቸው በአነስተኛ ወለድ በረጅም ጊዜ የሚመለስ ብድር ይዘው እንዲመጡ ይጠበቃል።»

የቻይናና የአውሮፓን ጨምሮ ከመላው ዓለም በግንባታ ስራ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ላይ በተናጠልና በሽርክና ለመሳተፍ በጨረታው መካፈላቸውን አቶ ዝናቡ ቱኖ ተናግረዋል።

የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተ/ማርያም በአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ውስጥ የውጭ ኩባንያዎች ተሳትፎ ጥሩም መጥፎም ጎን እንደሚኖረው ያስረዳሉ። ኩባንያዎቹ ዋና አላማቸው ትርፍ በመሆኑ የሚገነቧቸው ቤቶች ዋጋ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን የመክፈል አቅም ያገናዘብ እንዲሆን መንግስት በአግባቡ መደራደር እንዳለበት አቶ ጌታቸው ያምናሉ።

«ራሳቸው ፋይናንስ ይዘው የሚመጡ ከሆነና የብድር መጠናቸው መንግስት በሃገር ውስጥ ከንግድ ባንክ ተበድሮ ይሰራበት ከነበረው የብድር ሁኔታ የተለየ ካልሆነ ወደ ከፋዮች(የመኖሪያ ቤት ገዢዎች) የሚተላለፍ ጭማሪ ላይኖር ይችላል።»

እንደ የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተ/ማርያም ከሆነ የውጪዎቹ ኩባንያዎች ባላቸው ከፍ ያለ የፋይናንስ እና የመደራደር አቅም፤ለግንባታ የሚያስፈልጓቸውን ግብዓቶች በሌሎች ሃገራት ከሚኖራቸው ስራዎች ጋር በአንድነት መግዛት ስለሚችሉ የቤቶች ዋጋ ቅናሽ ሊኖራቸው ይችላል።በሌላ በኩል የመኖሪያ ቤቶች ዋጋ ውድ የመሆን እድልም አላቸው።

«እነዚህ ኩባንያዎች የግል በመሆናቸው ትርፍ ፈልገው የሚመጡ ናቸው። በመሆኑም አሁን መንግስት በሚሰራበት የፋይናንስ መዋቅር ላይሰሩ ይችላሉ።አሁን መንግስት ራሱ ከሚያስተዳድረው ባንክ ተበድሮ፤ግዢዎችን በራሱ ፈጽሞ ራሱ በሚያወጣቸው የስራ ውሎች ስር ነው ፕሮጀክቶችን እያስፈጸመ ያለው። እነዚህ የውጭ ኩባንያዎች ሲመጡ ግን ትርፋቸው፤የብድር ወለድ እና የግንባታ ወጪው በሙሉ ተደምሮ የቤቶቹ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል።» ሲሉ አቶ ጌታቸው ተ/ማርያም ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው አቶ ዝናቡ ቱኖ አሁን የተካሄደው ጨረታ የመጀመሪያ ዙር በመሆኑ ኩባንያዎቹ ያቀረቡት የገንዘብ መጠን በግልጽ እንደማይታወቅ አስረድተዋል።

አቶ ዝናቡ ቱኖም ሆኑ የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተ/ማርያም የሃገር ውስጥ ኩባንያዎች ከውጭዎቹ ጋራ በሽርክና መስራት ከቻሉ ከፍ ያለ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ይናገራሉ። በገንዘብ እና የግንባታ ፕሮጀክቶችን የማስተዳደር አቅም ውስንነት የሚተቹት የግል ኩባንያዎች ከውጪዎቹ ጋር በሽርክና በመስራት የእውቀትና የገንዘብ አቅማቸውን ማዳበር ይችላሉ።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰዎችን የመኖሪያ አካባቢዎችና ሁኔታዎች የሚከታተለው ዩኤን ሃቢታት የተሰኘው ተቋም አዲስ አበባ ባለፉት አስርት አመታት 10 በመቶ እየሰፋች መሄዷን እና የከተማዋ የህዝብ ቁጥር እ.ኤ.አ. በ2040 8.1 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ያትታል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic